"አስፈረምናት" አሉ?

ፓራጎን (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

ስሟን እንኳን መጥራት እያሳቀቃቸው

‘ሴትዮዋ’ እያሉ ሁሌ ማንሳታቸው

ግልጽ ነበር እኮ በእኛዋ ሳን ሱቺ መጨናነቃቸው

ጀግናዋ ብርቱካን እንቅልፍ አሳጥታ እንዳስቃዠቻቸው።

 

‘ያከተመለት ነው የሴትዮዋ ነገር’

‘ፍጹም አትፈታም’ አላሉንም ነበር?

ታዲያ ዛሬ ለምን ለቀቋት ቢባሉ

‘እኛ ጀግናዎቹ አስፈረምናት’ አሉ

ዘፈኑብን አሉ ’አስፈረምናት’ ብለው

እነሱ እንዳዋቂ እኛን ቂል አድርገው።

 

ሞኛችሁን ብሉ ብሏችኋል ህዝቡ

አያችሁት እኮ ከማን ጋር እንዳለ ከነሙሉ ልቡ

አበባ በትኖ ጎዝጉዞ ቄጤማ

ጉሮወሸባየን ጃሎን እያሰማ

ሽ ከፊት ከኋላ አጅቧት በኩራት

ከቤቷ ገብታለች ብርቱ የኛ እመቤት።

 

እናማ ሰውየው ምንም ቢሉ ምንም

ሚልዮን ወረቀት በቲቪ ቢያሳዩም

የግዳጅ ንግግር ሲደረግ ቢሰማም

ቀድሞት ስለሄደ ህዝቡ በውቀት ብዛት

ፊርማ ገለመሌ ንግስቱን ጎትቶ ከልቡ አያወጣት

ያበራዋል እንጅ የለኮሰችውን የትግል ፍም እሳት።

 

ጠፍትዎት አይደለም የፍቺው መነሻ

ቢጨንቅዎት እንጅ ቢያጡ ፊት ማበሻ

ነገሩ ወዲህ ነው ዋነኛው ምክንያት

መች ፊርማ ሆነና ምን ያደርጋል ውሸት?

 

እውነተኛ መሪ ታግላ ምታታግል

ኣርያ የሆነች ካዛውንት እስከ ጉብል

መምራት ስትጀምር ፖለቲካን በእውቀት

ታሰበዎትና የማይቀረው ውድቀት

ከመንገድ ላይ አፍሰው ከርቸሌ ቢጥሏት

በሁላችንም ልብ ቦታ ስለያዘች

ታስራም ፖለቲካን በመንፈስ ሰበከች።

 

እናማ ...

የሀገሬውን ህዝብ በጡንቻ ቢይዙም

እየቀጠቀጡ አንገት ቢያስደፉትም

ላፍታ እንኳን ካገር ቤት በድብቅ ቢወጡ

ለዚያው ለልመና ወይ ሊቀላውጡ

ካናዳ ቢሄዱ አውሮፓ አሜሪካ

በሚስጥር ቢያዝም የጉዞው ትረካ

ሚሊዮን ዶላሮች ቢፈሱም ለማፈን

መቸ ተበገረ በውጭ የሚገኘው እውነተኛው ወገን

አሳዶ አሳዶ ማረፊያውን ሲያጡ

በዚህ ከቀጠለ እንደሚቀር ሲያውቁ እርጥባን ቅልውጡ

ሞነጫጨሩና በብጣሽ ወረቀት

‘አስፈረምናት’ አሉ የኛው ሊቀ ሊቃውንት።

 

አሁን ምን እናድርግ እንግዲህ ለእርስዎ?

የወሰዱብንን ስለመለሱልን እንስገድልዎ?

አምላክ ናቸው ብለን ውዳሴ እናሰማ?

ወይስ ኃውልት ይቁም እንደነፍስ አባትዎ በሸገር ከተማ?

በጭራሽ አይስጉ ይህ አይደረግም

እርስዎም ያውቃሉ ያ አይገባዎትም

ለሰይጣኑ ውላጅ ያው ገሀነም እንጂ ገነት አትሰጥም።

 

ህዝቡ ምን እንዳለ አልሰሙትም ይሆን?

ወረቀቱን አይቶ ንግግሩን ሰምቶ የተላለፈውን

‘እና ምን ይጠበስ አዎ ፈርማለች፣

ከትንሹ እስር ቤት በነፃ ወጥታለች፣

ከኛ ጋር በአንድነት ወደ ትልቁ እስር በሠላም ገብታለች።

ይህንን ስላሉ እኛ ተደናግረን

ጀግናችንን ጥለን ጀርባችንን ሠጥተን

የምንሄድ ግብዞች መስለን ከታየንዎ

አሁን ይመርመሩ የጭንቅላት ሕመም በሽታ አለብዎ’

እያለ ነው አሉ የሚያፌዝብዎ።

 

ኧረ! ሌላም አለ ህዝቡስ የሚያወራው

በተግባር ሊያውለው የሚያብሰለስለው

’አንዷ ጥያቄያችን ብርቱካን ብትሆንም

ያልተመለሰልን ሚሊዮን አለ አሁንም

ትግሉ አልተወሰነም ከትንሽ ከርቸሌ ወገንን በማውጣት

ለመፈታት እንጂ ከትልቁ እስር ቤት

እናም ይቀጥላል ትግላችን ወደፊት። ...’

 

’አስፈረምናት አሉ እነዚህ ግብዞች

ውሸት ቀለባቸው የሰይጣን ውላጆች

እንግድያ ምን አለ በነካው እጃቸው

ለኛ ለሁላችን ወረቀቱን ጽፈው

ያስፈርሙንና እኛም እንፈታ

ከትልቁ እስር ቤት ከገሀነም ቦታ። ...’

 

’ያስፈርሙንና ይትነኑ ከሀገር

ሰልችቶናልና የመላ ህዝብ እስር’

እያለ ነው አሉ የሚሳለቅ ሀገር።


ፓራጎን (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ