ዛሬም "ቃሌን" ብለሽ (አሥራደው)
ዛሬም ”ቃሌን” ብለሽ
አሥራደው (ከፈረንሣይ)
ሞትን አትጠብቂ ባልጋ ላይ ተኝተሽ፤
ሜዳ ላይ ግጠሚው ፈረስሽን ’ቼ!’ ብለሽ፤
አጉል መደበቂያ አትፈልፍይ ዋሻ፤
ድንገት መሸሸጊያ አትፈልጊ ጢሻ፤
አትስበሪ አንገትሽን ግንባርሽ ዞር አይበል፤
ክንድሽ አይታጠፍ ጉልበትሽ አይዛል፤
ጠብቂው አትፍሪ ደረትሽን ነፍተሽ፤
በኩራት በድፍረት አንገትሽን አቅንተሽ፤
ቆመሽ እንደምትሞች አሁንም ንገሪው፤
ጀግና የጀግና ልጅ መሆንሽን ይወቀው፤
ትናንት ቆመሽ ነበር ወሕኒ የገባሽው፤
ዛሬም ቆመሽ ሙቺ ቃልሽን ሳታጥፊው።
በ’ንባ አትታጠቢ አታልቅሽ ቁጭ ብለሽ፤
አትንበርከኪለት ጉልበትሽን አጣጥፈሽ፤
እሱን አትጠብቂ ወዳንቺ እስቲመጣ፤
አንቺ ወደሱ ሂጅ ወዳንቺ እንዳይመጣ፤
ኩራትሽን ይረዳው ድፍረትሽን ይወቀው፤
የጀግና ልጅ ጀግና መሆንሽን ይረዳው፤
ትናንት ቆመሽ ነበር ወሕኒ የከተቱሽ፤
ዛሬም ቆመሽ ሙቺ ቃልሽን ጠብቀሽ።
አትለምኚ እነሱን ዕድሜ እንዲለግሱሽ፤
የአፍ መለጎሚያ ሥልጣን እንዲሰጡሽ፤
በንቅዘት የመጣ ሀብት እንዲያካፍሉሽ፤
ጭራሹን ተመልከች በጠራራ ፀሐይ፤
የህዝብሽን ብሶት የወገንሽን ስቃይ፤
መሃላሽን አርገሽ ቃል ለምድር ለሰማይ።
ትናንት ቆመሽ ነበር ወሕኒ ቤት ያሰሩሽ፤
ዳግም ቆመሽ ሙቺ ዛሬም ”ቃሌን” ብለሽ።
ለወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ወሕኒ ቤት በነበረች ጊዜ፤ ለእሷ እና ለሌሎች የሕሊና እስረኞች ”ቆሜ ነው እምሞተው” በሚል ርዕስ ጽፌው ከነበረ ግጥም የተደቀለ
አሥራደው (ከፈረንሣይ)
ጥቅምት 4 ቀን 2003 ዓ.ም. (October 14፣ 2010)



