ሕብረቱን እናጥብቅ! (ወለላዬ)
ሕብረቱን እናጥብቅ!
ወለላዬ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
ማሳጠር እንድንችል የወያኔን ዕድሜ፣
ምን ማድረግ አለብን? ተናገር ወንድሜ?
እህቴም ድምፅሽን አሰሚ እንማከር፣
ምንድነው ሃሳብሽ ለገጠመን ችግር?
ይህንን የምለው የሀገሬ ጉዳይ፣
ስላሳሰበኝ ነው ከምንግዜም በላይ።
ቃላት በማሳመር በመደርደር ግጥም፣
ሰውን ማሰላቸት ማዳከም ባልወድም፣
ሃሳቤን ማስረዳት ይገባኛል የግድ፣
በትግሉ እንድንገፋ ባንድነት እንድንሄድ።
መጀመሪያ በደንብ ሁሉን ነገር ሳናውቅ፣
ግለሰብ ድርጅት በደፈና አንናቅ።
እኔ ነኝ አዋቂው በዚህ ጉዳይ ዙሪያ፣
ብዙ ቅርበት አለኝ ለናት ኢትዮጵያ፣
በማለት ሌላውን አሳንሰን አንይ፣
ጥፋቱን ልማቱን በግልጽ እንወያይ፣
በውይይት መድረክ በቡድን በግንባር፣
ያልጠራ ጥላቻ ጋርደን ትልቅ አጥር፣
በዘረኛ ቢታ በወያኔ ወጥመድ፣
ተወታትበን ታስረን ገብተን አንሽመድመድ።
በአፋችን ትግል በልባችን ጥቅም፣
ይዘን አንነሳ የውሸት አናዝግም፣
መናገር ሳንችል መጠየቅ ፊት ለፊት፣
ጓሮ ተደብቀን አንደር በሃሜት።
ጥቅም አስተሳስሮን አነካክቶን ገንዘብ፣
ከልብ የሌለንን በአፍ በመሳደብ፣
እውነተኛ ታጋይ ለሚሠራው ሥራ፣
ፊት ለፊቱ ቆመን አንሁን ደንቃራ።
እንዲሁም በመለስ የጎሣ ስንጠቃ፣
መከፋፈል ፈጥረን በከንቱ አንዋቃ።
ጠልተን እንዲጠላ ስም ሰጥተን በመንቀፍ፣
ለራሳችን ትግል አናሳጣ ድጋፍ።
የጠላታችን ፀር እንዲሆነን ወዳጅ፣
መንገዱን እንክፈት ብዙ ጊዜ ሳንፈጅ።
ወዳጅ እያራቅን ጠላት ማግበስበሱ፣
እኛን እየጎዳን ብዙ ጠቅሟል ለሱ።
የዘላለም ጠላት የዘላለም ወዳጅ፣
የለም ብሎ ካለን ብዙ ቆየ ፈረንጅ።
ደግሞም አንድ ጥፋት ግለሰብ ቢሠራ፣
ብዙ ነገር ቢጭር ለግዜው ቢያቅራራ፣
ትልቅ ጠላት አድርገን አብረን አንለፍልፍ፣
አውቀነዋል አንዴ በትዕግስት እንለፍ።
ሌላውን ደፍጥጠን ሥልጣን ለመጨበጥ፣
አንችልም ጨርሶ ሌት ከቀን አንሩጥ።
ካልሄደ በስተቀር ማንም ሐቅን ይዞ፣
አይቀርም ማምጣቱ ሌላ ጥፋት መዞ።
ቃላት በመሰንጠቅ በከንቱ ልፈፋ፣
እንኳንስ ወር ዓመት ደቂቃም አናጥፋ።
ብዙ ከመደነቅ በጽሑፍ በግጥም፣
እውስጡ ያለውን ቁምነገር እንልቀም።
ከሁሉም ንግግር ጠቃሚ ሃሳብ ወስደን፣
ካለው ሁኔታ ጋር አንድ ላይ አስማምተን፣
ግማሹን በይፋ ከፊሉን በሚስጥር፣
በደንብ የተብላላ አርገንበት ምክር፣
ለመጓዝ ከቻልን በእንዲህ ያለ መንገድ፣
ሦስት ወራትም አንፈጅ ወያኔን ለማውረድ።
እንኳንስ በሰው ደም የናወዘን መሪ፣
ታጥቆ የመጣውን የውጪ ወራሪ፣
በተደጋጋሚ ቋንጃውን በመስበር፣
ማስወጣት ችለናል አስቆጥረን አሳር።
ሆኖም ለዚህ ሁሉ ቋሚ መሰረቱ፣
እስትንፋሱ ጭምር ደምና አጥንቱ፣
ሕብረት ስለሆነ እንቁም በጋራ፣
ንዝንዝ ጭቅጭቅ ይብቃን አተካራ።
በትንሽ ትልቁ ሳንሆን አኩራፊ፣
ችግር ቢገጥመንም ሆነን ሆደ ሰፊ፣
ከትግሉ ጎዳና ሳንሸሽ ሳንርቅ፣
አብረን መሥራት እንቻል ሕብረቱን እናጥብቅ!
ወለላዬ ከስዊድን
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



