ኢቴቪ የስድስት አሸናፊ ተጫራቾችን ውል ሰረዘ
Ethiopia Zare (ዓርብ ታህሳስ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. December 26, 2008)፦ የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት፣ የተለያዩ ዝግጅቶችን በስፖንሰሮች አሠርቶ ለማስተላለፍ አውጥቶት በነበረው ጨረታ፣ የመጨረሻ አሸናፊ ካደረጋቸው 11 ድርጅቶች ውስጥ፣ የስድስቱን በበጀት እጥረት ምክንያት መሰረዙን እንዳስታወቃቸው ምንጮች ጠቆሙ። ኢቴቪ ድርጅቶቹ ለሥራ ያወጡትን ወጪ በድርድር ካሣ ለመክፈል ጠይቋል።
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ፤ የመጨረሻውን መሥፈርት አሟልተው ውል የተፈራረሙ፣ ደብዳቤ ተሰጥቷቸው የተፈራረሙት ውል ቀሪ እስኪሰጣቸው እየጠበቁ ያሉና ሥራ የጀመሩ ምንጮች፤ ስለ ጉዳዩ እንደገለጹት፣ ጨረታው ከወጣበት ጊዜ አንስቶ የመጨረሻ የተባለው ደረጃ ለመድረስ ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ መውሰዱን ነው።
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት፣ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በሞያው ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች በመስጠት (Out Source) ለማሠራት እንደሚፈልግ ላወጣው ጨረታ፣ በርካታ ድርጅቶች የተወዳደሩ ሲሆን፣ የተለያዩ ማጣሪያዎች ሲደረግ ቆይቶ ወደ 20 የሚጠጉ ድርጅቶች ማለፋቸው ይነገራቸዋል።
እነዚህን 20 ድርጅቶች ለሁለት በመክፈልም ወደ 11 ለሚሆኑት ድርጅቶች፣ መስከረም 7 ቀን 2001 ዓ.ም. ደብዳቤው ከተሰጣቸው ዕለት ጀምሮ ባሉት ተከታታይ አምስት ቀናት፣ ከድርጅቱ ጋር ተፈራርመው በአስቸኳይ ሥራ እንዲጀምሩ የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሷቸዋል።
በቀጣዩም ድርጅቶቹ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና ሬዲዮ ድርጅት ጋር ውል ለመዋዋል ሲጠይቁ፣ ለሚያደርጉት ውል ማስተማመኛ እንዲሆን የውሉን ገንዘብ 10 በመቶ በሲፒኦ እንዲያስገቡ በመጠየቃቸውና አንዳንዶቹ ያሸነፉበት ገንዘብ በጣም በርካታ በመሆኑ፣ ማስተማመኛው በ”ፐርፎርማንስ ቦንድ” እንዲሆንላቸው ጠይቀው ስምምነት ላይ መደረሱን እነኚሁ ምንጮች ያስረዳሉ።
ነገር ግን “ፐርፈሮማንስ ቦንዱ”ን ለማምጣት የግዴታ የኮንትራት ውል መፈራረም ስለሚጠይቅ፣ ድርጅቶቹ የተሰጣቸውን ውሎች ሞልተውና የድርጅታቸውን ማሕተም አድርገው ለኢቴቪ መልሰው ይሰጣሉ።
ኢቴቪም ውሉን ፈርሞና ማሕተም እያደረገ፣ ለተወሰኑት መልሶ ሲሰጥ ለተወሰኑት ከውሉ ጋር መያያዝ ያለበት ቀሪ ነገር በመኖሩ እንዲጠባበቁ ተነግሯቸው እንደነበር ይጠቁማሉ።
ነገር ግን ከዚሁ ጎን ለጎን በአንድ ዓመት ለተዋዋሉት የ40 ሣምንት ፕሮግራሞች፣ ቅድሚያ የ10 ሣምንት ፕሮግራሞችን ሠርተው እንዲያስረክቡ ስለተነገራቸው፣ ሁሉም ድርጅቶች ቢሮ ተከራይተው፣ ሠራተኛ ቀጥረውና አስፈላጊ የተባሉ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ሥራ ውስጥ መግባታቸውን ይናገራሉ።
ይሁንና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (IT) ላይ ለመሥራት ጨረታ አሸንፎ የነበረው “ፊልሞን ፕሬስ”፣ የምግብ ዝግጅት ለማቅረብ ያሸነፈው “ካሬም የምግብ ዝግጅት”፣ የሕፃናት ፕሮግራም ለማዘጋጀት አሸንፎ የነበረው “ቀንዲል ቤተ-ተውኔት”፣ ድራማዎችን ለማቅረብ አሸንፎ የነበረው “ኢሳግ ስቱዲዩ”፣ ብሉካም የተባለ ድርጅት እና የትግሪኛ ፕሮግራም በራዲዮ ለማቅረብ አሸንፎ የነበረ አንድ ድርጅት፣ በአጠቃላይ የስድስት ድርጅቶች ባለቤቶች ወይም ሕጋዊ ወኪሎቻቸው ባለፈው ዓርብ ተጠርተው፣ በበጀት እጥረት ምክንያት ፕሮግራሞቹ መሰረዛቸው ተገልጾላቸዋል።
እንደ ምንጮቻችን ገለፃ ከሆነ፣ ድርጅቶቹ ጨረታው ከወጣና ፕሮፖዛል ከማቅረብ ጀምሮ ሥራ መጀመራቸውን በመግለጽ፣ በተለይ ማለፋቸውና ሥራ እንዲጀምሩ በደብዳቤ ከተገለጸላቸው መስከረም ወር አንስቶ፣ የቀረፃ ሥራውን ለማከናወን በርካታ ገንዘብ ወጪ ማድረግ መጀመራቸው በመግለጽ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ያለ አንድ ትልቅ የሚዲያ ተቋም እንዲህ ዓይነት ድርጊት መፈፀሙ አግባብ አለመሆኑን እንደገለጹላቸው ተናግረዋል።
የኢቴቪ የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ ድርጅቱ ሥራውን ማሠራት እንደሚፈልግ፤ ነገር ግን ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ስላለበት ማሠራት እንደማይችል በመግለጽ፣ ድርጅቶቹ ላወጡት ወጪ በድርድር ካሣ እንደሚከፍላቸው ተገልጾላቸዋል።
አንዳንዶቹ ድርጅቶች ጉዳዩ የገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ተመልካች ግንዛቤውን ሊያዳብርበት የሚችል በተለያዩ ባለሙያዎች የተሠሩ ፕሮግራሞችን መመልከት እንዲችል ለማድረግም ሥራው የግድ መሠራት አለበት ሲሉ መወትወታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል።
ነገር ግን ኃላፊዎቹ ድርጅቱ የገንዘብ እጥረት ስላጋጠመው፣ ጉዳዩን ወደፊት የሚመለከተው መሆኑን ደጋግመው በመግለፃቸውና አሸናፊ የነበሩ ድርጅቶችም ከስረናል ለሚሉት በድርድር ካሣ መክፈል እንደሚችል በቃል በማስረዳቱ፣ ይህንኑ በደብዳቤ እንዲገልጽላቸው ጠይቀው ውይይታቸውን ጨርሰዋል።



