ዳግማዊ አልአዛር

ይድረስ ለፓርላማ

”መልካም አስተዳደር ሽታው እየጠፋ፣

ሙስና ያነቀዘው ሲታይ ሲከረፋ።

በደከሙት ጀርባ ተሸላለሙ አሉ፣

ፓርላማው ይፍረደን … ቦርዶች ዝም ሲሉ።”

”ለኢትዮጵያ ኅዳሴ እተጋለሁ” የሚል አታሞ ከከበሮ እያስደመጠ ባለው ኢቲቪ (የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን) አይሰማ የለም፤ የጽሑፉ መግቢያ የሆነችው ስንኝም የተቃረመችው ከዚያ መሆኑን አስምሩበት።

 

እሁድ ጥቅምት 9/2001 ዓ.ም. ከቀኑ 6፡30 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚገኘው የኤግዚቢሽን ማዕከል በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሠራተኞች ተሞልቷል። ምግብ ቢጤዋ ከሞቀ ቢራና ለስላሳ ጋር እንደ ወጉ ቀርቦ ተወሳስዷል። ለተሃድሶ በብዙዎቻችን እምነት ግን “ለተሃሽጎ” መሆኑ ነው።

 

ለተሃድሶው /ተሃሽጎ በሉልኝ/ ማድመቂያ እንዲሆኑ ግን የተከበሩ አቶ በረከት ስምዖን የጠ/ሚኒስትሩ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ ሚኒስትር ተገኝተዋል። በ2000 ዓ.ም. ጥሩ የሥራ አፈፃፀም ነበራቸው ለተባሉ 96 የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ሠራተኞች 1 ሺህ ብር፣ የምስክር ወረቀትና የኅዳሴው ዋዜማ ዶክመንተሪ ፊልምን የያዘ ዲቪዲ ተሸልመዋል።

 

ዳሩ ምን ያደርጋል? አዲስ አበባ ከተማ እንደነበሩ የምናረጋግጥላቸው የማስታወቂያ ሚኒስትሩና የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አልነበሩም። ኢ.ራ.ቴ.ድ.ን (የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅትን) በበላይነት እንዲመሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) አደራና ኃላፊነት ከሠጣቸው የቦርድ አባላት አንዳቸው እንኳ አልተገኙም። … ይቅር ግዴለም። ... ወትሮንስ ማን ነግሯቸው? ለዘመናት የበደል ድምፅ ሲሰማ መች ቀርበው ለማነጋገርና ለመወሰን ዕድሉን አግኝተው?

 

በ1998 ዓ.ም. ይፋ በሆነው የኢ.ራ.ቴ.ድ. መዋቅር በደልዳይ ኮሚቴው ተመድበው ሳለ ”አልተመደባችሁም” ተብለው ከ14 ወራት በላይ ሳይሠሩ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ የመንግሥት ደመወዝ ሲከፈል፣ ሕገወጥ ዝውውር ሲፈፀምና በቅጥር ላይ ቅጥር ሲካሄድ መፍትሔ ያልሰጡ የቦርድ አባላት ድግሥ ላይ ባይገኙ ምን ያስደንቃል? የሚያስደንቀው ቢገኙ ነበር እንጂ።

 

ያም ሆነ ይህ የተሃድሶው /የተሃሽጎው/ ዓላማ መስከረም 21 ቀን 2001 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ በየክፍሉ ተጠርቶ ገምጋሚ የተመረጠበትና በነጋታው የመገምገሚያው መስፈርት በቃል ተነግሮ ከተራ ሠራተኛ እስከ ላይኞቹ አለቆች የ2000 ዓ.ም. የሥራ አፈፃፀም የተገመገመበትን መሠረት አድርጎ ሽልማት ለመስጠት ነው። ልብ በሉ ”ግምገማ በሩጫ፤ ሽልማት በአቋራጭ” መፈፀሙን። እነርሱ ግምገማውን ከታች ወደ አለቆች በመሄድ ነው የፈፀሙት፤ እኔ ግን ከላይ ከሹመኞቹ ልነሳና ባስቀመጡት መስፈርት መሠረት ዋቢ እየጠቀስሁ ልዘርዝርላችሁ።

 

ከግምገማው መስፈርት አንዱ ”የመንግሥትን ንብረትና ገንዘብ በአግባቡ መጠቀም …” ይላል። የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የማስተባበሪያ፣ የመምሪያና የክፍል አለቆች በተሰበሰቡበት ወቅት የሀብትና ፕሮሞሽን አስተዳደር የሥራ ዕንቅፋት ሆኗል፤ አስፈላጊነቱ አይታየንም ሲሉ ነበር። ለመሆኑ ከየትኛውም ማስተባበሪያና መምሪያ ያልተጠየቀ ከ100 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ 10 ካዝናዎች ተገዝተው ለ7 ወራት ፀኃይና ዝናም እንዲፈራረቅባቸው እያደረገ መሆኑን ለምን ሸፋፍናችሁ ወጣችሁ? ማውዝ የሌለውና ሶፍት ዌር የመንግሥትን ገንዘብ በግልፅ ያባከነ ይህ አካል እያለ ጋዜጠኛው በምን ጎኑ ትገመግማላችሁ?

 

ለህዝቦች መረጃን በአግባቡ ያደርሳል በተባለ አንጋፋ ድርጅት የተቀመጠው የሀብትና ፕሮሞሽን አስተዳደር መልካም አስተዳደርን እንዲያሰፍን የተቋቋመ ተቋም፤ ያያቸውንና ያረጋገጣቸውን ማስረጃዎች መረጃ መከልከሉንስ አጥታችሁት ይሆን?

 

ዝውውር በሚል ሽፋን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ 6 ደረጃ ለሂሳብ ሠራተኛነት አምጥቶ ሣምንት ሳይሞላው የፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አድርጎ ሌሎች የውስጥ ሠራተኞች እንዳያድጉ ቦታ ማስያዙስ ከእናንተ ተሰውሮ ነው? ምን ታደርጉ? በ2000 ዓመት አጋማሽ ላይ የመጣውን ይህን ግለሰብ ጭርሱን ተሸላሚ አድርጋችሁታል። እናም የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ለፓርላማው) ነውና … ይድረስ ለፓርላማ ግምገማውም ሽልማቱም ተጭበርብሯል ማለት ምን ያስከፋል?

 

መንግሥት ከ50 ሺህ እስከ 90 ሺህ ብር ወጪ ያደረገበት DV.7 የተሰኘ ካሜራ መጥፋቱ በካሜራ ክፍል ሠራተኞች ስብሰባ ላይ ተነስቶ የት ደረሰ? የሚለው ተገቢ ማጣራት ሳይካሄድበት ጉዳዩን ሸፋፍኖ ወደ ሽልማት መግባቱንስ ምን ይሉታል?

 

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ካሜራ ከኋላ ደቅነው መሬት ስጡን እያሉ የተደራደሩና የመሬት ወረራ የፈፀሙ ጋዜጠኞችና ኃላፊዎች ጉዳይም በግምገማው ነጥሮ ወጥቷል። ለአብነትም የወቅታዊ ዝግጅትና ዶክመንተሪ ፕሮግራም ኃላፊው የድሬደዋ 105ኛ ዓመት በዓል ሲከበር ለሥራ ሄዶ መሬት ጠይቆ እንደተሰጠው ተገልጿል። እርሱ ቤጂንግ እንደሄዱት ሯጮችና ጋዜጠኞች በሽልማት ተሰጠኝ በማለት ቢሸፋፍነውም።

 

የፕሮግራሞች መምሪያ ኃላፊው አዲስ አበባ ዙሪያ በመሬት ወረራ እንደሚጠረጠሩ ግልፅ ሲሆን፣ እርሳቸው በዚህ ግምገማ ላይ የመልካም አስተዳደርና ፖለቲካ ፕሮግራም ኃላፊው ሱሉልታ ለዐይናችን ፕሮግራም የሄደን ካሜራ ተልዕኮ አስቀይሮ ከተሞቻችን የተሰኘ ፕሮግራም ማሠራቱንና ለዚህም ውለታ ሱሉልታ ከተማ ቦታ እንደተሰጠው በቂ መረጃ እንዳላቸው ገልፀው ነበር። ሰበታ ደግሞ የኮንስትራክሽን ሥራ እያካሄድክ ነው ተብሎ በበላይ አለቃው ሪፖርት ቀርቧል። በእርግጥ ሐሰት ነው ብሎ ኃላፊው ተከራክሯል፤ እውነት ሳይወጣ በሥራ አፈፃፀሙ ከፍተኛ ተብሎ ለሽልማት መብቃቱን ለሰማ እንዴት በሽልማቱና በግምገማው ላይ ጥርጣሬ አይኖረውም?

 

ሰንሻይን ለተባለው ኮንስትራክሽን ፕሮግራም እንዲሠራ ቀረፃ ተካሄዶ ወር ሙሉ ሳይተላለፍ ቆይቶ በግምገማው ላይ እንደተገለፀው ይህን ሥራ የሠሩት በሕብረት ነበር። ሦስት ከዜና ማዕከል አንድ ከፕሮግራም ክፍል ሪፖርተር ዘምቶበታል።

 

በፕሮግራም እንዲለቀቅለት ግፊት ሲያደርግ የቆየው የዜና ማዕከል ኃላፊ አልሳካልህ ቢለው በዓለም እንዴት ሰነበተች ላይ ሥልጣኑ ነውና አስተላለፈው። ድርድሩ ካበቃ በኋላ መደበኛው የወጣቶች ፕሮግራም ተሰርዞ የሰንሻይን ፕሮግራም ተላለፈ። በሚያስገርም ሁኔታ ደግሞ ቢደገምም በቀኑ ክፍለ ጊዜ መደገም ሲገባው ሣምንት ባልሞላ ጊዜ ባለቤቱ ስላላዩት ተብሎ ተደገመ። ይህቺ ናት ጨዋታ አያሰኝም? …

 

በግምገማው ወቅት በዜና ማዕከሉም በፕሮግራም ማስተባበሪያውም ጉዳዩ ሙስና እንዳለበት የተወሳ ሲሆን፣ በተለይ ከዜና ማዕከል ተመድባ የሠራችው ሪፖርተር 3 ሺህ ብር የሚያወጣ ሞባይልና ገንዘብ እንደተሰጣት አምናለች። በዜና ማዕከል የመሸገውን አለቃዋን እኔ ሞባይሉን አንተ ብሩን ወስደሃል ነው ያለችው።

 

እናንተ ሆዬ! ይሄ የዜና ማዕከል ኃላፊ ግን ውጤቱ ከፍተኛ ተብሎ ተሸልሟል። ቡድን እያሰማራ ጥቅም ያለበት ቦታ ላይ መድቦ እንደሚካፈል በግልፅ የሚታወቅ በስነ ምግባር ቢገመገም ቢሮ በ4 ሰዓት ቢገባ ”ተመስገን በጊዜ ገባ” የሚባል ሞገደኛ ሲሸለም ከማፈር ሌላ ምን ልንል እንችላለን?

 

የተፈፀመው ሽልማት ሠራተኛውን የሚያነቃቃ፤ ለበለጠ የሥራ ተነሳሽነት የሚጋብዝ በመሆኑ በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ታሪክ ከ1987 ዓ.ም. ወዲህ ተደርጎ የማይታወቅ በመሆኑ ይበል ይጠናከር እንላለን።

 

ከተሸለሙት አብዛኛዎቹም የደከሙና የለፉ ቢያንስ የአቅማቸውን የሠሩ ባልደረቦቻችን መሆናቸውን ልባችን ያውቀዋል። ነገር ግን የግምገማው ሂደት ባልጠራበት በተቻኮለ ሁኔታ ሽልማት ተብሎ ሙስና ሙስና የሚሸቱ፤ በሙስና የተዘፈቁ፣ በመልካም አስተዳደር መጥፋት ተጠያቂ የሚሆኑ፤ በደከሙት ጀርባ ተፈናጥጠው መወገዝ ሲገባቸው ተሸልመዋል። ይህ ደግሞ በነገው የድርጅቱና የሠራተኞች የሥራ ውጤት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል።

 

ክቡር አቶ በረከት ስምዖንም እንዲሸልሟቸው ከቀረቡልዎት ስንዴዎች መሃከል እንክርዳዶች እንዳሉ ይረዱት፤ ፍሬሰንበት የተሰኘ ሪል ስቴት ያላቸው አንድ ባለሀብት ፕሮግራም ለማሠራት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ባልደረባ ለሆነ ግለሰብ ገንዘብ በመስጠታቸው ካሴቱ ተያዘ፤ እኛን ለማሠራት ቢሞክሩ እስከ ሚኒስትሩ አሳውቀናል በሚሉት የፕሮግራም ክፍል ኃላፊዎች እነርሱ የፀዱ ለመሆናቸው ገንዘብ ሰጥቻለሁ የሚሉትና ባለሀብቱን ዋቢ በማድረግ ያስወሰዱት እርምጃ ያለመኖሩ በራሱ መነካካት ለመኖሩ መገለጫ ነው።

 

የተጭበረበረው ግምገማና ሽልማት መነሻ ሆኖን ከብዙ በጥቂቱ አልን እንጂ ዛሬ በኢቴቪ የተቀረፀ አድባራትና ገዳማት ታሪካዊ ቦታዎችና የቆዩ ፊልሞች ከነ ዲቪ ካሴታቸው እየተሰረቁ፤ ክሊፕ ተሰርቶባቸው በራሱ በቴሌቪዥን እንደሚተላለፍ ክሊፓችን ቁጭ ብሎ ማየት በቂ መረጃ ነው።

 

የሽልማት አሰጣጡ በራሱ በችግር የተተበተበ፤ መንግሥት እየታገለለት ባለው የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ማስፈን ሂደት ውስጥ ግልፅነትና ተጠያቂነት የጎደለው ነው። እስቲ የፓርላማው የማስታወቂያና ባህል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲህ ብለው ይጠይቋቸው፤ የሽልማት ኮሚቴው አባላት እነማን ናቸው? ለሽልማት ያበቃቸው መስፈርት ምን ነበር? ያስከትሉናም ከእንግሊዝኛ ፕሮግራም ማስተባበሪያ ለምን አንድ ሰው እንኳ አልተሸለመም? በ2000 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንግሊዝኛ ዜናና ፕሮግራም አልተላለፈም ወይንስ የእነርሱ ሽልማት በእንግሊዝኛ ስለሆነ ነው?

 

ግምገማው በሩጫ፤ ሽልማቱ በአቋራጭ ለመሆኑ ደግሞ ሌላ ዋቢ እናስቀምጥ፤ ግምገማው ተጠናቆ በጥቅምት 9/2001 ሽልማት ሲሰጥ፤ በግምገማው ያልታሰቡት የሕግ ክፍል፣ የፕላንና ጥናት፣ ሥነ ምግባር ክፍል እና የክልል ትራንስሚተር ሽልማቱ በተከናወነ በሠልስቱ ግምገማ ለመጀመር በጥቅምት 11/2001 አስገምጋሚ መርጠዋል። ሽልማቱ ባለቀ በሠልስቱ ለግምገማ ደርሰዋል፤ ሽልማቱን በአርባ (በተዝካር) ያገኙት ይሆን?

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ