የኢቲቪ 32 ጋዜጠኞች ንብረት አስረክቡ ተባሉ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ኅዳር 6 ቀን 2001 ዓ.ም. November 15, 2008)፦ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የቴሌቪዥን ዘርፍ፣ አዲስ በጀመረው የሰዓት ጭማሪና በጣቢያው ስር ይተዳደሩ የነበሩ የኦሮምኛና የትግርኛ ፕሮግራሞች ወደ ክልሎቻቸው እንዲሄዱ በተወሰነው መሰረት 32 የሚሆኑ የኦሮምኛ ፕሮግራም ሠራተኞች ንብረት አስረክባችሁ ክሊራንስ አስፈርሙ መባላቸውን ገለጹ። ክሊራንሱ ላይ ”በገዛ ፍቃዴ ለቅቄያለሁ የሚል ስላለው አንፈርም ብለናል” ሲሉ ሠራተኞቹ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከመስከረም 1 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ፣ የአየር ሰዓቱን ማሳደጉንና የሥርጭት ሰዓት መጨመሩን፣ የኦሮምኛና የትግርኛ ፕሮግራም ክፍሎች የቀረፃ ሥራቸውን በክልላቸው እንዲያደርጉ፣ በስብሰባ ላይ በሥራ ኃላፊዎቻቸው አማካኝነት ከተነገራቸው በኋላ ምንም ሥራ ሳይሠሩ ደምወዝ እየተከፈላቸው እስከ ጥቅምት 30 መቆየታቸውን ይገልጻሉ።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሠራተኞች እንደሚሉት፣ መመሪያው በስብሰባ ላይ ከተላለፈልን ከመስከረም 1 ቀን በኋላ ምንም ሥራና የሚያነጋግረንም ኃላፊ ሳይኖር ጠዋት ገብተን ፊርማ ከፈረሙ በኋላ ግቢ ውስጥ ቆይተው ማታ ወደ ቤታቸው እንደሚሄዱ ገልጸው፣ ረቡዕ ዕለት ግን ሥራ እንዲያቆሙ ከተደረጉት 52 ሠራተኞች ውስጥ ለ32ቱ ከኅዳር 1 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ንብረት እንዲያረስክቡ የሚያዝ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
እነዚሁ ሠራተኞች እንደገለጹት፤ “ቀደም ሲል የተነገረን የኦሮምኛ ፕሮግራም በክልሉ በኩል ስለሚተላለፍ ወደዚያ ትላካለችሁ እንጂ፣ እንዲህ በአንድ መስመር ደብዳቤ ዕቃ አስረክቡ ትባላላችሁ ያለን አልነበረም፤ የደረሰን ደብዳቤ በእጃችሁ የሚገኝ ማንኛውንም ንብረት አስረክቡ የሚልና ክሊራንስ እንድናስፈርም፣ የሚጠይቅ ነው። ይህ ከሥራ ተባራችኋል እንደ ማለት ነው፤ ደብዳቤው በሚያዝዘው መሠረት ንብረት አስረክበን ክሊራንስ ካስፈረምን ሥራችንን ለቀናል ማለት ነው፤ ማንንም የምንጠይቀው አካል አይኖርም፤ የኦሮሚያ ክልል መገናኛ ብዙኀንም አያውቀንም። የምንጠይቀውም አካል አይኖርም።” ብለዋል።
እንኳን የመንግሥት መስሪያ ቤት ይቅርና የግል ድርጅትም ቢሆን ሠራተኛን ሲያዘዋውርም ሆነ ሲያሰናብት ሕጋዊ የሆነ አካሄድ እንዳለው የገለጹት ሠራተኞቹ፤ “ድርጅቱ እያደረገ ያለው በርካታ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ የድርጅቱ ቋሚ ሠራተኞችን ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ማሰናበት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ሠራተኞቹ ቀደም ሲል ተቃውሟቸውንም ለጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፣ ለፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት፣ ለኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህልና ማስታወቂያ ኮሚቴ፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሃያ ቀናት በፊት ደብዳቤ ቢያስገቡም እስካሁን ግን ምንም ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ሠራተኞቹ እንደሚሉት፣ የኦሮሚያ ቴሌቭዥን ፕሮግራም ዜና፣ መዝናኛ፣ ስፖርት፣ የልጆች ፕሮግራም አዘጋጆችና ፀሐፊዎች በአጠቃላይ ወደ 60 የሚጠጉ የዝግጅት ክፍል ሠራተኞች አሉት። የቴሌቪዥን ፕሮግራሙም ከሰኞ እስከ እሁድ ማታ ማታ ለአንድ ሰዓት፣ ቅዳሜ ጠዋት ለ30 ደቂቃ የልጆች ፕሮግራምና ከሰዓት ”ዳንጋ” የተባለው የመዝናኛ ፕሮግራም ይቀርብ ነበር።
በኦሮሚያ ክልል ተዘጋጅቶ ”የኦሮሚያ ቴሌቪዥን ፕሮግራም” (ሳታቫኦ) በሚል ከሰኞ እስከ ዓርብ ከቀኑ ስድስት ሰዓት እስከ ሰባት ሰዓትና ቅዳሜ ማታ ለ45 ደቂቃ ክልሉ ከቴሌቪዥን ጣቢያው በገዛው የአየር ሰዓት ይተላለፍ እንደነበር ይገልፃሉ።
ቅሬታችንን ያስታወቅናቸው የመንግሥት አካላትም ሆኑ በፌደራል ደረጃ እንድንሠራ የቀጠረንን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን ቀና ምላሽ በሚጠብቁበት ወቅት እንዲህ አይነት ደብዳቤ ሲደርሳቸው ማዘናቸውን ተናግረዋል።



