ኢቲቪ የሥርጭት ሰዓቱን ሊጨምር ነው
ክልሎች ፕሮግራማቸውን በየክልላቸው ያደርጋሉ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2000 ዓ.ም. September 09, 2008)፦ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና ራዲዮ ድርጅት ከመስከረም 1 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ከጧቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ድረስ ሥርጭቱን ሊያራዝም መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገለፁ። የትግሪኛ እና የኦሮምኛ ፕሮግራሞች ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በየክልላቸው ይደረጋሉ መባሉ ተቃውሞ አስነስቷል።
በኢ.ቲ.ቪ. የሚገኙ ምንጮች እንደገለፁት፣ ባለፈው ሣምንት የአማርኛ፣ ትግርኛ እና ኦሮምኛ ማስተባበሪያዎች ለየብቻቸው በአንድ የሥራ ኃላፊ ስብሰባ ተጠርተው ከመስከረም 1 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ የሥርጭታቸውን ጊዜ በማሳደግ ከጧቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ጧቱ 3፡00 ሰዓት፣ ከቀኑ 6፡00 ሰዓት እስከ ለሊቱ 6፡00 ሰዓት የሚራዘም መሆኑን ተነግሯቸዋል።
በሚራዘመው ፕሮግራም ጣልቃም ኢ.ቲ.ቪ. በቅርቡ አውጥቶ በነበረው ጨረታ ተወዳድረው የነበሩ አሸናፊ ፕሮግራሞች ይተላለፉበታል ተብሏል።
በተጨማሪም በየክልላቸው ተቀርጸው የሚላኩ የትግርኛ፣ ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ደቡብ፣ ቤንሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ፣ ... ክልል ፕሮግራሞች በሚሰጣቸው የሰዓት ድልድል መሠረት ያስተላልፋሉ ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የእንግሊዘኛ፣ የዐረቢኛ፣ የፈረንሣይኛ፣ ... ቋንቋ ፕሮግራሞች ይጀመራሉ በሚል ከኃላፊዎቻቸው እንደተገለፀላቸው ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በዚህ ስብሰባ ላይ ከሐምሌ 1 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ በሚኖረው አዲስ በጀት የትግርኛና የኦሮምኛ ፕሮግራሞች ከኢ.ቲ.ቪ. አስተዳደር ወጥተው በየክልላቸው ሊላኩ እንደሚችሉ ጥቆማ እንደተሰጣቸው ምንጮቻችን ገልፀዋል።
ለረዥም ዓመታት ቤተሰቦቻቸውን እንደመሰረቱ የሚናገሩት የትግርኛ እና የኦሮምኛ ፕሮግራም ዝግጅት ክፍል ባልደረቦች የፕሮግራሙን ዝውውር በሚመለከት ተቃውሞ ያነሱ መሆኑ ታውቋል። በተለይ የኦሮምኛ ፕሮግራም ባልደረቦች ፊንፊኔ የኦሮሚያ ከተማ እስከሆነች ከአዲስ አበባ ልንዛወር አይገባም ሲሉ ተደምጠዋል።



