የኢ.ቲ.ቪን አሠራር የተቃወሙ ጋዜጠኞች ለጠ/ሚሩ አቤቱታ አቀረቡ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ መስከረም ፲፯ /17 ቀን ፳፻፩/2001 ዓ.ም. September 27, 2008)፦ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት የቴሌቭዥን ዘርፍ፣ አዲስ በጀመረው የሰዓት ጭማሪና በጣቢያው ስር ይተዳደሩ የነበሩ የኦሮምኛና የትግርኛ ፕሮግራሞች ወደ ክልሎቻቸው እንዲሄዱ መደረጉን በመቃወም፣ የኦሮምኛ ፕሮግራም ክፍል ሠራተኞች ለጠ/ሚ መለስ እና ለተለያዩ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች ደብዳቤ አስገቡ። ሠራተኞቹ ጣቢያው ከእነርሱ ጋር ውይይትና አስፈላጊ ዝግጅት ሳያደርግ የጀመረው እንደሆነ ሲገልጹ፣ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በበኩሉ ፕሮግራሙን የማሳደግና የማስፋፋት ሥራ እየሠራሁ ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከመስከረም 1 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ፣ የአየር ሰዓቱን ማሳደጉንና የሥርጭት ሰዓት መጨመሩን፣ የኦሮምኛና የትግርኛ ፕሮግራም ክፍሎች የቀረፃ ሥራቸውን በክልላቸው እንዲያደርጉ፣ በስብሰባ ላይ በሥራ ኃላፊዎቻቸው አማካኝነት እንደተነገራቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኦሮምኛ ፕሮግራም አዘጋጆች ይገልፃሉ።
እነዚሁ ሠራተኞች እንደሚሉት መመሪያው በስብሰባ ላይ ከተላለፈልን ከመስከረም 1 ቀን በኋላ ምንም ሥራ የለንም፣ የሚያነጋግረንም ኃላፊ አላገኘንም፣ ጠዋት ገብተን እንፈርማለን፣ በግቢው ስንዟዟር ውለን ማታ ወደየቤታችን እንሄዳለን ብለዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ “የኛ ጥያቄ ለምን ተቀነስን አይደለም፣ በብሔራዊ ደረጃ ዝግጅት ተደርጎበት የሚተላለፈው ፕሮግራም ለምን ይታጠፋል? ሰዓቱስ ለምን ይቀነሳል?” ባዮች ናቸው።
አያይዘውም “ጣቢያው ሠራተኞቹ መሆናችንን ተገንዝቦና አወያይቶ፣ በጋራ እንድንወስን ማድረግ ሲገባው፣ እንደ አንድ ተራ መሥሪያ ቤት፣ ውሳኔውን ለመተግበር 11 ቀናት ሲቀሩት ሠራተኛ ሰብስቦ እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰዱ ፍፁም አግባብነት የሌለው ነው” ሲሉ አማረዋል።
ይኸንኑ ተቃውሟቸውንም ለጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፣ ለፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት፣ ለኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህልና ማስታወቂያ ኮሚቴ፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሃያ ቀናት በፊት ደብዳቤ ማስገባታቸውንና እስካሁን ግን ምንም ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ሠራተኞቹ እንደሚሉት የኦሮሚያ ቴሌቭዥን ፕሮግራም ዜና፣ መዝናኛ፣ ስፖርት፣ የልጆች ፕሮግራም አዘጋጆችና ፀሐፊዎች በአጠቃላይ ወደ 60 የሚጠጉ የዝግጅት ክፍል ሠራተኞች አሉት። የቴሌቭዥን ፕሮግራሙም ከሰኞ እስከ እሁድ ማታ ማታ ለአንድ ሰዓት፣ ቅዳሜ ጠዋት ለ30 ደቂቃ የልጆች ፕሮግራምና ከሰዓት “ዳንጋ” የተባለው የመዝናኛ ፕሮግራም ይቀርብ ነበር።
በኦሮሚያ ክልል ተዘጋጅቶ “የኦሮሚያ ቴሌቭዥን ፕሮግራም” (ሳታቫኦ) በሚል ከሰኞ እስከ ዓርብ ከቀኑ ስድስት ሰዓት እስከ ሰባት ሰዓትና ቅዳሜ ማታ ለ45 ደቂቃ ክልሉ ከቴሌቭዥን ጣቢያው በገዛው የአየር ሰዓት ይተላለፍ እንደነበር ይገልፃሉ።
ከመስከረም 1 ቀን በወጣው አዲስ መመሪያ ግን በብሔራዊ ደረጃ ዝግጅት ተደርጎበት የሚተላለፈው ፕሮግራም ቀርቶ፣ በክልል የተዘጋጁ ፕሮግራሞች እንዲቀጥሉ መደረጉን ገልጸው፣ ሥራ ያቆሙትን ሠራተኞች በሚመለከት የተባሉት ወይም በደብዳቤ የተገለፀላቸው ነገር እንደሌለ አስረድተዋል።
ሠራተኞቹ የሚሉትም ቅሬታችንን ያስታወቅናቸው የመንግሥት አካላትም ሆኑ በፌደራል ደረጃ ለማሠራት የቀጠረንን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅትን ምላሽ እየጠበቅን እንገኛለን በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል።
በሌላ በኩል በተመሳሳይ ጊዜ ወደ ክልል እንዲዛወሩ የታዘዙት የትግርኛ ፕሮግራም አዘጋጆች የሚያነሱት ቅሬታ አለ።
በርግጥ ወደ ክልል እንደሚዛወሩ ከተነገራቸው በኋላ፣ የትግራይ ክልል ቴሌቭዥን ጣቢያ በመሣሪያም ሆነ በሰው ኃይል የተደራጀ ባለመሆኑ ለጊዜው የክልሉን ፕሮግራም እዚሁ ሆነው እንዲቀርጹ የተነገራቸው ቢሆንም “የወሰኑት ጊዜ ሲደርስ እንድንሄድ ማስገደዳቸው አይቀርም፤ ይህ ደግሞ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው። እኛን የቀጠረን ብሔራዊ ጣቢያው ነው። ቤተሰብ አፍርተን፣ ቤት ሠርተን፣ ልጆቻችንን ትምህርት ቤት አስገብተን፣ እኛም ተጨማሪ ትምህርት ጀምረን በአጠቃላይ የኑሮአችን መሠረት የገነባንበትን ከተማ ጥለን ወደ ሌላ ከተማ እንድንሄድ ሳንጠየቅና ሳንወያይበት መወሰኑ ፍፁም አግባብ አይደለም” ይላሉ።
በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ይተላለፍ የነበረው የትግርኛ ፕሮግራም ከሰኞ እስከ እሁድ ማታ፣ እሁድ ቀን “ሰንበት ምሳና” የተባለ መዝናኛ ፕሮግራምና ረቡዕ ማታ “ተሃድሶ” የተባለ የኅብረ ትርኢት ፕሮግራም ሲሆን፣ ክልሉ ከጣቢያው ላይ በገዛው የአየር ሰዓት በሣምንት ሁለት ቀን ለአንድ ሰዓት ያስተላልፍ ነበር። አዘጋጆቹ እንደሚሉት “ሰንበት ምሳና” ሁለት እሁድ አለመተላለፉንና ከትናንት ባሳለፍነው ረቡዕ መቅረብ የነበረበት “ተሃድሶ” አለመተላለፉን ነው። “እስካሁን ክልሎቹ ሠርተው የሚልኩትና ከዚሁ ከስቱዲዮ የሚሠራው ዜና “የትግራይ ክልል ቴሌቭዥን” የሚል ዓርማ ተለጥፎበት እየተላለፈ ነበር፤ አሁን ደግሞ የመስቀል በዓል ልዩ ፕሮግራም እንዲሠራ ታዟል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አጠቃላይ የጣቢያው ሁኔታ በሚመለከት አስተያየት የሰጡ አንድ የጣቢያው ሠራተኛ በሌሎች ሀገራት ያሉ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ሥርጭታቸው 24 ሰዓት ነው (ያውም እኛ ሀገር አንድ ጣቢያ ነው ያለው)፤ በዚህ ሁኔታ የሥርጭት ሰዓቱን በቀን ወደ 19 ሰዓት ማሳደጉ ሊበረታታ የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ነገር ግን ይላሉ እኚህ አስተያየት ሰጪ፣ የአየር ሰዓቱ በቀን ወደ 19 ሰዓት ቢያድግም ጧት ላይ የሦስት ሰዓት ክፍተት አለ፣ ከዚያ ከሚተርፈው 16 ሰዓት ላይ ደግሞ ቀደም ሲል ጣቢያውን ለትችት ዳርገው የተቋረጡ በመሣሪያ የተቀነባበሩ ሙዚቃ ማጀቢያ የገባላቸው ተፈጥሮዓዊ አካባቢዎች ይታዩበታል። ይኼ የሚያመለክተው ደግሞ ጣቢያው ፕሮግራም ማሳደጉን ሳያስብ በድንገት የወሰነው መሆኑን ነው ይላሉ።
አያይዘውም የአየር ሰዓት ሲጨመር ቅድመ-ዝግጅት ተደርጎ፣ መጠባበቂያ ፕሮግራም ተሠርቶና በሠራተኛው ልክ የፕሮግራም ድልድል ተደርጎ ነው። በተጨማሪም በቂ የዝግጅት መሣሪያ (ካሜራና የኤዲቲንግ ማሽን) ተዘጋጅቶ መሆን ነበረበት። ከዚህ አኳያ ድርጅቱ የማስፋፊያ ሥራ እየሠራሁ ነው ቢልም ከተወቃሽነት አያመልጥም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ የኦሮምኛና የትግርኛ ፕሮግራሞች በየክልሎቻቸው ስር እንዲሆኑ መወሰኑን፣ ጣቢያው በማስፋፊያ ሥራው የሥርጭት ሰዓቱን ወደ 15 ሰዓት ማሳደጉን፣ ያላደጉ ክልሎች ፕሮግራም ቀርፀው እንዲያስተላልፉ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ማድረጉንና የማሠራጫ ጣቢያዎቹን ከ30 ወደ 52 አካባቢ ማሳደጉን ሰሞኑን አስታውቋል።
ተቋሙ አዲስ በጀመረው አደረጃጀቱ ላይ ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ለማሳደግ የሚረዳቸውን ፍትሃዊ የአየር ሰዓት ማድረጉን አስታውቋል። የሥርጭት ጥራቱን በማሻሻልም አማራጭ ቻናሎችን ለማቅረብ ሦስት መካከለኛ ሞገድ ሬዲዩ፣ ሰባት ኤፍ.ኤም. ሬዲዮ እና 54 የቴሌቭዥን የሥርጭት ጣቢያዎችን ተክሎ የሥርጭት አድማሱን ለማስፋፋት በዝግጅት ላይ ነው። ፕሮጀክቱ ከአንድ ዓመት በኋላ ሲጠናቀቅ የሬዲዮ ሥርጭቱ ሽፋን ወደ 90 በመቶ፣ የቴሌቭዥን ሀገራዊ ሥርጭት አድማሱ ደግሞ 85 በመቶ ያደርሰዋል።
በመሆኑም ከመስከረም 1 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ለፌደራልና ለክልሎች የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች አዲስ የሙከራ ሥርጭትና የአየር ሰዓት ድልድል ማድረጉን ገልጿል።



