ኩችዬ  ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

“ላም እሳት ወለደችና እንዳትልሰው እሳት፣ እንዳትተው ልጇ ሆነ!” - አበው

ይህ አባባል ግለሰቦችም ማኅበረሰቦችም በኑሮ ሂደት ውስጥ አስጨናቂ ምርጫ እንዲያደርጉ የሚገደዱባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን የሚያመለክት ነው። እነዚህ ሁኔታዎች ብንዘጋቸው የማይዘጉ፤ መልስ እስካላገኙ ድረስ ከፊታችን ዞር የማይሉ ችኰ ነገሮች ናቸው። 3ኛው የግልገል ግቤ ፕሮጀክት እንዲህ ሆኖብን ስለከረመ እንደልማዴ የማውቀውንና የሚሰማኝን ላካፍላችሁ መረጥሁ።

 

ስለ ግቤ

 

ግቤ የተንጣለለውን የኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ ክፍል እያካለለ መልኩን አሳምሮ ወደ ኬንያ ዳርቻ የሚነጉድ ወንዝ ነው። ታዲያ እርባና ያለው ሕይወት ሳይኖር ቆይቶ በደርጉ ዘመን ሠርተህ ብላ ተባለ። ከዚያ በኋላ “ግቤ አንድ” እና “ግቤ ሁለት” የሚባሉ ፕሮጀችቶች ተከናውነው 400 ሜጋዋት ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ተገንብቷል። “ግቤ 2” ፍጻሜ ያገኘው በኢህአዲግ ዘመነ መንግሥት መሆኑን መግለጽ ተገቢ ይመስለኛል።

 

“ግልገል ግቤ ሦስት”

 

የግልገል ግቤ-3 ፕሮጀክት ፅንሰ-ሃሳብ በአፍሪካ ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም በመገንባት ላይ የተመሠረተ ነው። እንደ ግብጹ “አስዋን” ግድብ (ዳም) ለኢትዮጵያ የልማት ሞተር ሊሆን የሚችል ኃይል መፍጠር ማለት ነው። የፕሮጀክቱ ሥራ ሦስት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚፈጅ ሲገመት በሚጠናቀቅበት ጊዜ 1870 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል። ለንጽጽር እንዲረዳችሁ ያሁኑ የኢትዮጵያ አቅም የሚያሳዝን 600 ሜጋዋት ብቻ ነው። ለዚህ ነው ሀገራችን በኩራዝ የምትኖረው። ለዚህም ነው ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ሳትቀር በሣምንት ለሦስት ቀን የኮረንቲ ራሽን የተዳረገችው። “ግልገል ግቤ-3” ካገራችን ተርፎ ለጎረቤት ሀገሮችም የመሸጥ አቅም እንደሚያስገኝ ይነገራል።

 

ታዲያ ከባድ ችግር ተፈጥሮላችኋል! የግቤ ወንዝ ውልደቱም ጉልምስናውም እርጅናውም ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ እያለ፤ ኢትዮጵያ በዚህ ወንዝ እንዳሻት ልትጠቀም አትችልም የሚሉ ጉዶች ፈልተዋል። “በገዛ ዳቦዬ ልብ-ልቡን አጣሁት” ዓይነት ነገር መሆኑ ነው። እንዳሸን መፍላት ብቻ ሳይሆን ለዚህ ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ኢትዮጵያ እናዳትበደር እያከላከሉም ነው። ግብጽና ሱዳን በግልገል ግቤ-3 ታላቅነት ተደናግጠዋል፤ ኬንያም እንዲሁ። ኤንቫይሮሜንታሊስቶች የሚያናፍሱት አጀንዳና የሚያፍሱት ዶላር በማግኘታቸው ፈንድቀዋል፤ እኛ ደግሞ በነገሩ ግራ ተጋብተን የላሟን ዓይነት ሆነናል። ሦስቱንም በየተራ ላስረዳ።

 

ግብጽና ሱዳን

 

በምናውቀው ምክንያት ግብጽና ሱዳን የኢትዮጵያን መጎልበት አይፈልጉም። ጠንካራ ኢትዮጵያ ማለት ከአባይ ወንዝ ላይ ድርሻዋን የምትጠይቅ ኢትዮጵያ ትሆንባቸዋለችና ወደ ሠላምና ወደ ብልጽግና የሚወስዳትን ጎዳናዎች ሁሉ በፈንጂ ከማጠር አይቦዝኑም። የአባይ ወንዝ መነሻውን እስካልለወጠ ድረስ ከነዚህ ሀገሮች ጋር ያለን ባላንጣነት ይቀጥላል። ይህ ያጉል ተጠራጣሪ አመለካከት ሳይሆን (ኮንስፒረሲ ቲዎሪስት አለመሆኔን ታውቃላችሁና) ግብጦችም ደርቡሾችም በሰነዘሩብን ተደጋጋሚ ጦርነትና ባሴሩብን ሴራ መጎዳታችን በታሪክ የተመሰከረ ነው።

 

ግብጾች የግቤ-3ን ፕሮጀክት ለማሰናከል ጥድፊያ ላይ ናቸው ይባላል። በውሃ አጠቃቀም ሕግ የተራቀቁ ናቸው የሚባልላቸው ድርጅቶቻቸው፣ ምሁራኖቻቸውና የዲፕሎማቲክ ጡንቻቸው የግቤ-3 ፕሮጀክትን “ጐጅነት” በማስተጋባት ላይ ይገኛሉ። የአውሮፓ ኢንቬስትመንት ባንክ፣ ዓለም ባንክና አሁን ደግሞ ያፍሪካ ልማት ባንክ ለግቤ-3 ገንዘብ እንዳያበድሩ ከኤንቫይሮሜንታሊስቶች ጀርባ ሆነው ዘመቻ እያካሄዱ ነው። ዘመዶቼ! ግብጽ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተደማጭነት ቀላል እንዳልሆነ ምንጊዜም መዘንጋት የለብንም።

 

የኤንቫይሮሜንታሊስቶች ጫጫታ

 

ኤንቫይሮሜንታሊስቶች ጥሩ ጎን ያላቸውን ያህል አንዳንዱ ባሕርያቸው አስቂኝ ነው። ግቤ-3ን በሚመለከት ግድቡ ከተሠራ ያካባቢው ነዋሪ ህዝብ ኑሮ ይበላሻል ይላሉ። ኢኮሎጂ ይናጋል ይላሉ። እስኪ በፈጠራችሁ የትኛው የኑሮ ዓይነት ነው የሚበላሸው? መለ-መላ የሚኬድበት? ከንፈር የሚተለተልበት? ረሃብ፣ ድንቁርና፣ መኃይምነትና በሽታ የነገሡበት? ወይንስ ደግሞ ጥቂት ቱሪስቶች የፎቶ አጋጣሚ አግኝተው የበላይነት ስሜት የሚገዙበት?

 

ቢማሮ አምደልካር የተባለው ከጋንዲ የሚተካከል የሕንድ አባት፤ “ምሁሩ በገጠሩ ላይ ያለው ፍቅር ማለቂያ የሌለው ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ነው” ይልና “በሐቅ ከተመለከትነው ገጠሩ የድንቁርናና የበሽታ ጉሮኖ፣ የጎሠኝነት ኩሬ፣ የጠባብ አመለካከት ጎተራ ነው” ብሎ ይደመድማል። እኔ ደግሞ “ኋላቀር የኑሮ ዘይቤዎችን አላግባብ የሚያወድሱና ከዘመናችን የኑሮ ዘይቤ ጋር መሳ-ለመሳ ለማስቀመጥ የሚሞክሩ እነርሱ ጤነኞች አይደሉም ደህና ሐኪም ያስፈልጋቸዋል” እላለሁ።

 

ስለ ኤንቫይሮሜንት ካነሳን ዘንድ የዓለም ሥልጣኔ አስቸጋሪና አስቸጋሪ ያልሆኑ ምርጫዎችን እያደረገ ነው እዚህ የደረሰው። አሜሪካ፣ አውሮፓና እስያ የተገነቡት ኤንቫይሮሜንት ሳይቀየር አይደለም። ሁቨር፣ አስዋን፣ ሜርዌ፣ ያንግቴዝና ሌሎችም እርቆ መሳፍርት የሌላቸው ግድቦችና ልማቶች ሲከናወኑ ሰፋፊ መሬቶች በውሃ መጥለቅልቅ ነበረባቸው። የታሪክ ቅርሶችና ማዕድኖች ሳይቀሩ በሐይቆቹ ሥር ማቅረታቸው አማራጭ አልነበረውም። እነዚህ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በመለወጥ በኩል ያደረጉት አስተዋጽዖ ግዙፍ ነውና ክርክር እንኳ አይጠይቅም።

 

የመኖር-ያለመኖር ጥያቄ በተነሳ ቁጥር ኤንቫይሮሜንት የሚያገኘው ትኩረት ሁለተኛ ደረጃን ነው። በኔ ግምት ግቤ-3 ለኢትዮጵያ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው። የሚያወላዳ ሀብት ለሌላትና በመጨረሻው የድህነት እርከን ላይ ለምትገኝ ኢትዮጵያ “ኤሌክትሪፊኬሽን” አማራጭ የሌለው የልማት እርምጃ ስለሆነ የትኛውም መንግሥት ሥልጣን ላይ ቢሆን ወደኋላ የሚባልበት ጉዳይ አይሆንም። የምናዘገየው ጉዳይም አይደለም።

 

ታዲያ ምኑ ነው እኛን ግራ ያጋባን?

 

እኛን ግራ ያጋባን የኢህአዲግ ጉዳይ ነው። ኢህአዲግ በላሟ ልጅ ይመሰላል። ከጎኑ እንዳንቆምና የዓለም ባንኮችን ሎቢ እንዳናደርግ የኢህአዲግ ደጋፊ ልንመስል ነው። አይተን እንዳላየን እንዳንሆን ደግሞ ያገር ህልውና ጥያቄ አለበት። የቅርብ ዘመን ታሪካችንን እንኳን መለስ ብለን ብናይ ይህ ትውልድ ሁለት ተመሳሳይ ፈተናዎች ገጥመውት እንደነበር ማስታወስ እንችላለን። አንደኛው በ1969ኙ የሶማሌ ጦርነት ጊዜ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በኤርትራው ጦርነት ጊዜ ነበር። ህዝባችን ያደረገው ምርጫ ከመንግሥቶቹ ጋር የነበረውን ቅራኔ ለጊዜውም ቢሆን ወደጎን አድርጎ በሀገር ጉዳይ ላይ ተረባረበ። የግቤን ጉዳይ በዚያ ትይዩ የማስቀምጥበት ምክንያት አለኝ። ይኸውም የታሪክ ጠባሳና መጥፎ “ፕሬሲደንስ” ፈጥረን እንዳናልፍ ከመስጋት ነው።

 

የምን ፕሪሲደንስ ነው ደሞ?

 

ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ ሳትጠቀም ለዘመናት ኖራለች። በአንፃሩ ደግሞ የሱዳንና የግብጽ ሕልውና የተመሠረተው በዚህ ወንዝ ላይ ነው። ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የረባ የባለቤትነት መብትና ያጠቃቀም ፕሪሲደንስ አልመሠረተችምና በወንዙ ላይ ሁነኛ ፕሮጀክት እጀምራለሁ ብትል የሱዳንንና የግብጽን ስምምነት ማግኘት ያስፈልጋታል። የዓለም ሕግ እነሱን ይደግፋልና። ህልውናቸውን ለማስጠበቅ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እስከማወጅ የሚያደርስ መብት ይኖራቸዋል። ሰዶ ማሳደድ ይሏችኋል ይሄ ነው።

 

አባይ ጥሩ አስተምሮናልና ግቤ ወንዝን ሰደን ማሳደድ አንችልም። ስለሆነም ያለንን የባለቤትነትና የመብት ጥያቄ በማያወላዳ ሁኔታ የማረጋገጡ ጉዳይ ወሳኝ ነው። ለኤንቫይሮሜንታሊስቶችና ለአሳዳሪዎቻቸው ግፊት ከተፈታንና መብታችንን አሳልፈን ከሰጠን ሀገራችን ሁነኛ ልማት ማካሄድ የምትችልበትን የመጨረሻ ዕድል አባከነች ማለት ይሆናል። ከመጨረሻው የድህነት እርከን ፈቅ ለማለት እንኳ ላንችል ነው። ዛሬም ጎጅ ፕሪሲደንስ ላለመክፈት እንጠንቀቅ። የውጭ ባላንጣዎቻችን ማለፍ የማይችሉትን መስመር ዛሬውኑ እናስምር።

 

ይህን ስናደርግ ዲሞክራሲንና የሕግ የበላይነትን በሀገራችን ለማስፈን ከኢህአዲግ ጋር የምናደርገውን ትግል እየቀጠልን መሆኑ አነጋጋሪ እንኳ አይደለም። በኔ ግምት ሁለቱ እንቅስቃሴዎች አይጻረሩም። እንዴትና በምን መልኩ የሚለውን ልንወያይበት እንችላለን። የቱን ያህል አስጨናቂ ቢመስልም በጉዳዩ ላይ ጨዋ ውይይት ማድረግን ልንሸሸው አንችልም።

 

አቶ ፀጋዬ ሙሉሸዋ በዚህ ጉዳይ ላይ Uneasy choice: Where do we stand on Gibe III dam? ጥሩ ጽፏል። 


 

ኩችዬ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. / www.kuchiye.blogspot.com )

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ