በመብራት መቋረጥ ምሬት እየጨመረ ነው
Ethiopia Zare (ረቡዕ መጋቢት 1 ቀን 2002 ዓ.ም. March 10, 2010)፦ የግልገል ግቤ ቁጥር ሁለት ከተመረቀና ሥራ ከጀመረ በሁለት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ከተማና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመብራት መቋረጥ ህዝብ እየተማረረ መሆኑ ታወቀ።
በአዲስ አበባ ከተማ ሰሞኑን የጄኔተሮች ጩኸት ሲሰማ ከመዋሉም በላይ የአላቂ ዕቃዎች አምራች ካምፓኒዎች በቂ የሆነ ምርት ለህዝቡ ማቅረብ አለመቻላቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ከአዲስ አበባ ገልጸዋል።
የመብራት መቋረጥ የገበያ ግሽበቶችን ከማባባሱም በላይ አለመረጋጋትን እንደፈጠረ ለማወቅ ችለናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ግድቦች መመረቃቸው ብስራት በተሰማ በተለይም በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነውና 44 ሜትር ጥልቀት ያለው የተከዜ ኃይድሮ ፓወር ፕሮጀክት 75 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው አራት ተርባይነሮች ያሉት ኃይድሮ ፓወር የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት እንደሚያቃልል የተነገረለት ግዙፍና ከ300 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችለው የተከዜ ኃይድሮ ማመንጫ ተመርቆ ባለበት ሁኔታ ሀገሪቱ የመብራት ችግር መታየት አነጋጋሪ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።



