Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2001 ዓ.ም. June 23, 2009)፦ በአራት የተለያዩ አካላት አጨቃጫቂ እየሆነ በመጣው የግልገል ግቤን የኃይድሮኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ላይ “አሉባልታዎችና ውዥንብሮችን የሚነዛ በህዝብና በሀገር ጥቅም ላይ የተነሳ ነው” ሲል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አሳወቀ።

 

ጽ/ቤቱ ባወጣው መግለጫ ”ፕሮጀክቱን አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ሚዲያዎች በጭፍን ሲቃወሙት ቆይተዋል፤ ይህም ብቻ ሳይሆን ለፕሮጀክቱ ማሳኪያ የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ገንዘብ እንዳይረዱ ሲሯሯጡ ታየተዋል፤ በኦሞ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢ የሚገኙ የኢትዮጵያና የኬንያ አርብቶ አደሮች ሕልውናና በአካባቢው ሥነ-ምሕዳር እንዲሁም በቱርካና ኃይቅ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያስከትላል በማለት ላይ ይገኛሉ” በሚሉ ነቀፌታዎች ላይ የሚያትተው ይኸው የመንግሥት መግለጫ፤ ”ይህ ሁሉ ተግባር የሽብር ተግባር ነው” ብሏል።

 

አያይዞም በኬንያው የውሃ ሀብት ዳይሬክተር የሚመራ የኬንያ መንግሥት የልዑካን ቡድን ግንባታው እየተካሄደ ባለበት ስፍራ ተገኝቶ ፕሮጀክቱን በመመልከት በቱርካና ኃይቅ ላይ የሚያስከትለው አንዳችም ችግር እንደሌለ መግለጻቸውን ጠቁሟል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስተር ኬን ኦሃሺ፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት ለግልገል ግቤ ፕሮጀክት ምንም ዓይነት ድጋፍ አልጠየቀንም” ሲሉ ተናግረዋል። ሚስተር ኦሃሺ አክለውም በአወዛጋቢው በግልገል ግቤ ግድብ ግንባታ ላይ “የዓለም ባንክ ውሣኔ ላይ አልደረሰም” ብለዋል።

 

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የኢትዮጵያ መንግሥት ለፕሮጀክቱ ድጋፍ እንዲሰጠው ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብለትም ከረጅም ጊዜ በኋላ ገንዘብ አልሰጥም ማለቱን በመገናኛ ብዙኀን መዘገቡ አይዘነጋም። ይሁን እንጂ ባንኩ ስሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ገንዘቡን እንዳላገደ ገልጿል።

 

የግልገል ግቤ 3 ፕሮጀክት በኬንያ ፓርላማ አጨቃጫቂ እንደነበር የሚገልጹ አንዳንድ መገናኛ ብዙኀን፤ ኬንያ በከፍተኛ ሁኔታ መቃወሟን ማተታቸው ይታወሳል። ከወራት በፊት የቢቢሲ ቴሌቭዥን በኦሞ ወንዝ አካባቢ የሚገኙ ጎሣዎችን በማነጋገር ፕሮጀክቱ ለሕይወታቸው አደጋ እንደሆነና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለጦርነት እንደሚዘጋጁ፣ የኦሞ ወንዝ ሕይወታቸው ስለሆነ በወንዙ የመጣ በሕይወታቸው እንደመጣ እንደሚቆጥሩት መግለፃቸው ይታወሳል። ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ መንግሥት፣ በእርዳታ ሰጪዎች፣ በአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች፣ በኦሞ ወንዝ አካባቢ ባሉ ነዋሪዎችና በኬንያ መንግሥት ዙሪያ ውዝግብ ሲያስነሳ፤ ወሬውን በማርገብ ረገድ እንግሊዝ ቀዳሚውን ሥፍራ እንደያዘች ነው የሚታወቀው።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ