በቃሊቲ እስር ቤት የሰሞኑ አሳዝኝ ሁኔታ (ግርማ ካሣ)
ግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
ቶርቸር (ሰቆቃ) ከዓለም እንዲጠፋ የሚታገል የዓለም አቀፍ የፀረ-ቶርቸርና የተጎጂዎች ደጋፊ ድርጅት፣ የአዕምሮን ቶርቸር ሲተነትን፣ ረዘም ላለ ጊዜ በጨለማ ቤት ውስጥ ማስቀመጥን፣ እንቅልፍ ማሳጣትን፣ መድፈርንና የመሳሰሉትን ከቶርቸር ውስጥ ያስገባቸዋል። በእንደዚህ አይነት የአዕምሮ ቶርቸር የሚያልፉ ሰዎች እራሳቸውን እንዲጠሉ የሚያደርግና የሚቆይ ከፍተኛ የአዕምሮ በሽታን እንደሚያመጣ ይናገራሉ።[1]
የለንደን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ከቤልግሬድ የሕክምና ኮሌጅ ጋር በመተባበር 279 የቀድሞ እስረኞችን በማነጋገር፣ ሳይንሣዊ በሆነ መንገድ መረጃዎችን ሰብስበዋል። በሰበሰቡትም መረጃ መሰረት የደረሱበት ድምዳሜ የአዕምሮ ቶርቸር ከአካላዊ ቶርቸር በምንም እንደማይለይ የሚገልጽ ነበር። የአዕምሮ ቶርቸርን እንደ አካላዊ ቶርቸር የሚያግድ ዓለማቀፋዊ ሕግ መውጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።[2]
እስት ለትንሽ ጊዜ ከምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ቆጠብ እንበል። ዓይኖቻችንን እንጨፍን። እራሳችንን ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር ባለች ጠባብ ክፍል ውስጥ እንየው። የምንተኛበት መኝታ በጣም ይቆረቁራል። ከመጨለሙ የተነሳ ብዙም አይታየንም። ከእንቅልፋችን ስንነሳ ጨለማ ነው። ወደ መኝታ ስንሄድ ጨለማ ነው። በዚያች ክፍል ውስጥ ዓይኖቻችንን ጨፈንናቸውም ከፈትናቸውም ጨለማ ነው። በቀዳዳ፣ ሕይወታችንን ለጊዜው የሚያቆይ አፍ ላይ የሚደረግ ይወረወርልናል። ተኝተንም ሳለ የወፎችን ጫጫታ ወይንም ሙዚቃ ወይንም የሰዎች ድምፅ ሳይሆን የአይጦችን ጭጭጭ የሚል ድምፅ ነው የምንሰማው። አንዳንዴም አይጦቹ በተኛንበት በላይችን ላይ ይበራሉ። መጽሐፍ ማንበብ አንችልም። ሬዲዮ መስማት አንችልም። ቴሌቭዥኑንማ እርሱት።
መልካችንን የምናይበት መስታወት የለም። መስታወትም ቢኖር ጨለማው መስታወቱን ተራ ግድግዳ አድርጎታል። ቢገድሉን ወይንም ቢደበድቡን ደስ ይላቸው ነበር። ግን የምዕራቡን ዓለም ይፈራሉ። ስለዚህም በቀላቸውን በሌላ ነገር ይወጡታል። አውቀው ትናንሽ ጉንዳንና ቱኃን ይለቁብናል። ጉንዳኖቹና ቱኃኖቹ ሰውነታችንን ይነክሳሉ። አንዱን ከእጃችን ስናራግፍ አንዱ በእግራችን ይመጣል። ሰውነታችን ይላላጣል። “የሐኪም ያለህ!” ብንል የሚሰማ የለም። ብናለቅስ የሚሰማ የለም። ግድግዳውን ብንደበድብ የሚሰማ የለም። ብንለምን፣ “እባካችሁ! በእመብርሃን፣ በመድኃኔዓለም፣ በጊዮርጊስ፣ በአላህ! …” ብንል የሚሰማ የለም።
ለአንድ ቀን ብቻ አይደለም። ከአንድ ቀን አልፎ ለሁለት ቀናት፣ … ከዚያም ለሦስት ቀናት፣ … ለአሥር ቀናት፣ … ለሃያ ቀናት፣ … ቀኑ እየተራዘመ መጣ። ቀናት መቁጠራችንን ቀጠልን። አንድ መቶ ስድሳ አምስት ላይ ደረስን። እስቲ እናስብ እራሳችንን! አናብድም? አዕምሯችንን አንስተም? እራሳችንን አንጠላም? አንታመም?
በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የደረሰው እንግዲህ ይሄ ነው። በእጇ ጠመንጃ አልያዘችም። ሁሉን የምትወድ ናት። ፍቅርን፣ ፍትህን፣ አንድነትን ነው የሰበከችው። በምቾት ተሰዳ በምዕራቡ ዓለም መኖር ስትችል፤ ሀገሬንና ህዝቤን ብላ ለሀገሯ ለመታገል የወሰነች ሀገር ወዳድ ሴት ናት።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከታህሳስ 20 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 7 ቀን 2001 ዓ.ም. ድረስ በግፍና በጭካኔ በጠባብ ጨለማ ክፍል ውስጥ፣ ከሰው እንዳትገናኝ ተደርጎ ከጉንዳንና ከአይጦች ጋር ነው የምትውለውና የምታደረው። ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢሰጥም ከዘመድ ወዳጅ፣ ከሐኪም ከጠበቃዋ ጋር እንዳትገናኝ ታግዳለች።
ማክሰኞ ሰኔ 4 ቀን 2001 ዓ.ም. ትልቅ አስደንጋጫ ክስተት ተፈጠረ። የስድስት ወር ቶርቸር የወለደው እጅግ በጣም አሳሳቢ ነገር ነበር። በርጋታዋና በብርታቷ የምትታወቀው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከታሰረችበት አካባቢ ከፍተኛ ጩኸት እንደተሰማ አቡጊዳ ዘገበ። ለምን ወ/ት ብርቱካን እንደጮኸች እስከአሁን ማወቅ አልተቻለም። ከሰው እንዳትገናኝ አድርገው ምን እያደረጓት እንደሆነ እግዚአብሔር ነው የሚያወቀው።[3]
የመጀመሪያው ዓላማቸው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንድትል የሚፈልጉትን ብላ የፖለቲካ ተቀባይነት እንድታጣ ለማድረግና ትግሉን መሪ አልባ ለማሰኘት ነበር። አስፈራሯት። ዛቱባት። እርሷ ግን ናቀቻቸው። ለነርሱ ውሸት እንደማትንበረከክ አሳየቻቸው።
እነርሱም በእልህና በጭካኔ መጡባት። “እንግዲያውስ በፈቃዷ ለኛ ፈቃድ ካልተገዛች፣ ቶርቸር አድርገን መንፈሧን ሰባብረን ዋጋ ቢስ እናደርጋታለን! እናሳብዳታለን!” ብለው ተነሱ። ብዙ ነፍሳት በገደለ ነፍሰ ገዳይ እንኳን ያልተፈጸመ በደል አደረሱባት። ለስድስት ወር በጨለማ ቤት ውስጥ በግፍ አስቀመጧት።
አቡጊዳ እንደዘገበው የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች በማንም ሰው ላይ እንደዚያ ተደርጎ እንደማያውቅ፣ በወ/ት ብርቱካን ላይ የሚደረገው ግፍ ከላይ በመመሪያና በትዕዛዝ የመጣ እንደሆነ ይናገራሉ። (ከአራት ኪሎ ማለት ነው)
ለመሆኑ አራት ኪሎ የተቀመጡት ሰዎች (ሰዎች ልበላቸውና) ይሄ ሁሉ ግፍ በዚች ሴት ላይ እንዲደርስ የሚፈቅዱት ምን ወንጀል ብትሠራ ነው? “ወያኔ ጠላት አይደለም” ማለቷ ነው ወንጀሏ? ሠላማዊና ሕጋዊ ትግል ማድረጓ ነው ወንጀሏ? ሀገሯን ለቃ በስደት አለመኖሯ ነው ወንጀሏ?
“ለሕግ የቆምን ነን። ሕግ መከበር አለበት!” ይሉናል። የትኛው ሕግ? ሕግን ቢያወቁ ኖሮማ የፍርድ ቤትን ውሳኔ ባከበሩ ነበር? ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በጠበቃዎቻቸውና በሐኪሞቻቸው በወዳጆቻቸው እንዲጎበኙም በፈቀዱ ነበር። ይቅርታውን ከመሰረዛቸው በፊትም ሕጉ እንደሚያዘው፣ በጽሑፍ ምክንያታቸውን ያሳውቁና ለወ/ት ብርቱካንም፣ ምላሽ እንድትሰጥ፣ የሃያ ቀናት ጊዜ ይሰጡ ነበር።
የህወሓቱ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ለቢቢሲ ሐርድቶክ ጋዜጠኛ ስለወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ተጠይቀው ሲመልሱ “ከተፈታች በኋላ ‘ይቅርታ አልጠየኩም’ አለች። ያ ማለት ይቅርታ ያገኘቸው በማጭበርበር ነበር ማለት ነው። ስለዚህ በሕጋችን መሰረት በማጭበርበር የተገኘ ይቅርታ ወዲያውኑ መሰረዝ አለበት” ነበር ያሉት።
“የይቅርታ ውሳኔ ለይቅር ተባዩ ከደረሰና ተቀባይነት ካገኘ በኋላ የይቅርታ ውሳኔ በማጭበርበር ወይም በማታለል የተገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ የይቅርታ ውሳኔው ዋጋ አይኖረውም”[4] የሚለውን በይቅርታ ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 395፣ አንቀጽ 16፣ ንዑስ አንቀጽ 2 አስበው ይመስለኛል አቶ መለስ ይህን አይነት መልስ የሰጡት።
“አዲስ አድማስ” በሚባለው ሀገር ውስጥ በሚታተም ጋዜጣ በይፋ በወጣው ጽሑፏ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ስትጽፍ “በሽማግሌዎቹም የእርቅ ማግባቢያ መንፈሥ መሰረት በፖለቲካ የተቀሰቀሰውን ክስ ፖለቲካዊ እልባት ለመስጠት በማሰብ ለእርቅ ስል ከሌሎች የፓርቲው መሪዎች ጋር ተስማምቼ ሰኔ 11 ቀን 1999 ዓ.ም. በተጻፈው ሰነድ በሽማግሌዎች አማካኝነት ይቅርታ ጠይቄያለሁ። ይህ ብፈልግም ልለውጠው የማልችለው ሐቅ ነው” ነበር ያለችው።[5]
እንግዲህ እዚህ ላይ የምናየው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በግልጽ “ይቅርታ ጠይቄያለሁ” እንዳለች ነው። ታዲያ አቶ መለስ ዜናዊ ከየት አምጥተው ነው “ይቅርታ አልጠየኩም አለች” እያሉ የሚናገሩት? የቱ ላይ ነው ወ/ት ብርቱካን ያጭበረበረችው? ምንድን ነው ያታለለችው? ምኑ ነው ጥፋቷ? እንደዚህ ኢ-ሰብዓዊና አረመኔያዊ ግፍ ድርጅታቸው በዚች ሴት ላይ የሚያወርድበት ምክንያት?
ዋሽንግተን ፖስት እንደዘገበው ወይዘሪት ብርቱካንን ጨምሮ የቅንጅት መሪዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችና ጋዜጠኞች በሀገር ሽምግልና መሰረት ይቅርታ ጠይቀው በተፈቱ ጊዜ አቶ መለስ ዜናዊ የተናገሩት አባባል ነበር። “ይቅርታው ሙሉ ነው። ሕግን እስካከበሩ ድረስ ለመምረጥና ለመመረጥ ይችላሉ። ያለፈውን ትተን፣ ወደኋላ ሳንመለስ ወደፊት ነው ማየት ያለብን”[6] ነበር ያሉት። ታዲያ “ወደ ኋላ አንመለስ። ያለፈውን እንተው” ብለውን እራሳቸው ግን ወደ ኋላ ተመልሰው “ይቅርታ ጠይቄያለሁ” ያለችውን ሴት “ይቅርታ አልጠየኩም ብላለች” ብለው እንደነፍሰ ገዳይ ድርጅታቸው ማሰቃየቱ ምን ይባላል?
“ሕግን እስካከበሩ ድረስ” ነበር ያሉት አቶ መለስ ዜናዊ። ታዲያ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የትኛውን ሕግ ነው የጣሰችው? ጠመንጃ አንስታ ሰው ገደለች? ወይንም የህዝብን ገንዘብ መዝብራ ገንዝብ ወደ ውጭ አሸሸች? ወይስ ጉቦ ተቀብላ ባገኘችውና ባጠራቀመችው ገንዘብ አሜሪካን ሀገር ቤት ሠራች? የቱ ነው ወንጀሏ ለዚህ ሁሉ ግፍ የዳረጋት?
እንግዲህ ሀገር ፍረድ! አሁን ያለውን አገዛዝ እንደግፋለን የምትሉ፣ ልብና አዕምሮ ያላችሁ ሁሉ ፍረዱ! እንስሳውና አውሬውስ እንስሳና አውሬ ነው። “ሰው ነን። እናስባለን፣ እናገናዝባለን” የምትሉ ሁሉ ፍረዱ! የዚች ሴት ጥፋት ምንድን ነው? እንደዚህ ቶርቸር የምትደረግበት ምክንያቱ ምንድን ነው?
ይሄን ያህል ጭካኔ በሌላ ወገናችን ላይ እስክናደርስ ድረስ እንደዚህ አውሬ የሚያደርገንስ ነገር ምንድን ነው? ምን ይሻለን ይሆን ባካችሁ? ለምንድን ነው እንዲህ የምንጨካከነው? ለምንድን ነው አንዱ ሲጠቃ ሌላው ዝም ብሎ የሚመለከተው? ለምንድን ነው አንዱ ደብድብ ሲል ሌላው እሺ ብሎ የሚታዘዘው? ምንድን ነው እንደዚህ ሕሊና ቢሶች ያደረገን?
ኧረ! አንተ ደጉ መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በቃቹህ በለን! እባክህን እኛም እንደሌሎቹ ህዝቦች እንደታደሉት፣ ለተጠቁት የምንቆም፣ ለድሃ አደጉና ለመበለቲቶች የምንሟገት፣ የወደቀውን የምናነሳ፣ የተሰበረውን የምንጠግን፣ ክፋትንና ጭካኔ ቶርቸርን የምንፀየፍና የምንቃወም እውነተኞች አድርገን!!! ብርቱካን ሚደቅሳንም አስባት! ባላችበት ቦታ ኃይልህ፣ ብርታትህ፣ ፀጋህና ጥበቃህ አይለያት! - አሜን!!!
[1] http://www.tassc.org/index.php?sn=78
[2] http://www.abc.net.au/science/news/stories/2007/1864094.htm
[3] http://www.abugidainfo.com/?p=9813
[5] http://n.b5z.net/i/u/6142638/i/birtukan_1_.pdf
[6] http://www.washingtonpost.com/wp-dyn/content/article/2007/07/20/AR2007072000454.html



