ሁሉ ነገር በእጃችን ነው (ግርማ ካሣ)
ግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) ሰኔ 17 ቀን 2001 ዓ.ም.
ኢትዮጵያን በጽጌረዳ አበባ እመስላታለሁ። ጽጌረዳ አበባ በጣም ተወዳጅ የሆነች አበባ ናት። ብዙ ጊዜ በማስቀመጫ ውስጥ ተደርጋ የሚመጡ እንግዶች በሚያዩዋት ቦታ ትቀመጣለች። የክብር፣ የፍቅርና የውበት ምልክት ናት። ኢትዮጵያ ሀገራችንም በነፃነቷና በአንድነቷ ታፍራና ተክብራ የኖረች፣ ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተውጣጡ ልጆቿ ውበቷ የሆኑላት፣ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝብ ሁሉ ኩራት የሆነች ሀገር ናት።
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ስለኢትዮጵያ “ኢትዮጵያ በሃሳቤ ልዩ ቦታ አላት፤ ኢትዮጵያን መጎብኘትም ፈረንሣይን፣ እንግሊዝንና አሜሪካን ከመጎብኘት የበለጠ ይስበኛል” ብለዋል። ስለዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አንድ በተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ፎር አፍሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩ፣ ሴኔጋላዊ ከአሥራ ሰባት ዓመታት በፊት የነገሩኝ ቁም ነገር ነበር። “ስለ ዐፄ ምኒልክና የአድዋው ጦርነት የሴኔጋል ተማሪዎች ይማሩታል። የአድዋው ድል የአፍሪካ የነፃነት ምዕራፍ ጅማሬ ነው። ምኒልክ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ አባት ናቸው” ሲሉ ነበር፤ ኢትዮጵያ በሴነጋል ተወላጆች ዘንድ ያላትን ልዩ ቦታ በግልጽ ያስቀመጡልኝ። አዎ! ኢትዮጵያ የኛ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝብ ሁሉ ጽጌረዳ ናት።
ኢትዮጵያ ለጥቁር ህዝብ ሁላ ኩራት የሆነችው በቀላሉ አይደለም። የኢትዮጵያን ነፃነትና ክብር ለማስጠበቅ የተከፈለው መስዋዕትነት እጅግ በጣም ትልቅ ነው።
በአድዋ፣ በማይጨው፣ በአዱሊስ በወልወልና በመላው የኢትዮጵያ ግዛት ከወራሪ ጣሊያኖች ጋር፤ በጉንደትና በጉራ ከግብጾች ጋር፤ በአፋር ምድር ከቱርኮች ጋርና እንዲሁም “ታላቋ ሶማሊያ” በሚል መርኅ የተሰማራውን የውጭ ወራሪ ኃይል ለመመከት በሐረርጌ በተደረጉት ታላላቅ ትንቅንቆች ታላቅ የደም መስዋዕትነት ተከፍሏል።
በመተማ ከደርቡሾች በተተኮሰ ጥይት ያለፉትን ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ፤ በመቅደላ ተራራ ለኢትዮጵያ ክብር ሲሉ እጃቸውን ለእንግሊዞች ላለመስጠት የራሳቸውን ጥይት የጠጡትን መይሳው ዐፄ ቴዎድሮስን፤ የዘርዓይደረሰን፣ የአብዲሳ አጋን፣ የደጃች ባልቻ አባነፍሶን፣ የፊታውራሪ ገበየሁን፣ የጥቁር አንበሳ ጀግኖችንና እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚ ለኢትዮጵያ ነፃነትና ክብር ሲሉ ሕይወታቸውን ሰውተው ያለፉ ወገኖቻችንን ሁሉ ብንደምር ቁጠራቸው እጅግ በጣም ብዙ ነው።
ጽጌረዳ መልከ መልካምና ያማረች የሆነችውን ያህል የሚዋጉና የሚያደሙ እሾሆችም አሏት። በአዲስ አበባ፣ በሐውዜን፣ በአሲምባ፣ በከረን፣ በአስመራ፣ በአሶሳ፣ በጎንደር፣ በኦጋዴን፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ … በእሾህ ተወግቶ የስንቱ ኢትዮጵያዊ ደም ፈሰሰ? ስንቱ በወንድሙ እጅ ታረደ? የስንቱ ወጣት እናት ልጇን አጣች?
በሀገራችን ለዘመናት በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ያለቁት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተምረው፣ ትዳር ይዘው፣ ልጆች ወልደውና ከብረው፣ ለወግ ለማዕረግ መድረስ የሚችሉ ነበሩ። አሁን በሕይወት እንዳለነው እንደ ማናችንም ሐኪሞች፣ መሃንዲሶች፣ ምሁራን፣ የሕግ ባለሞያዎች፣ … ሆነው ኅብረተሰባቸውንና ሀገራቸውን ሊጠቅሙ የሚችሉ ነበሩ። ታዲያ ምን ያደርጋል የኢትዮጵያ ኋላ ቀር የደም መፋሰስና የመገዳደል ባህል ሰለባ ሆነው ቀሩ።
ለዚህ ነው በአኩሪ ታሪካችን እንደምንኮራው ሁሉ በአሳፈሪው ታሪካችንም ማፈር አለብን የምለው። ሀገር እያለን ተሰደናል። ወገን እያለን ብቸኞች ሆነናል። ለሌሎች ሀገሮች የተረፉ ታላላቅ ወንዞች እያሉን ተጠምተናል። ምግብ እያለን ተርበናል። የሀገራችን መሬቶች በደም ከመራሳቸው የተነሳ እህል ማብቀል አቁመው ከዓመት እስከ ዓመት ለህልውናችን የፈረንጆችን እጅ እየጠበቅን ኖረናል። (ስንዴና ሩዝ ዘይትና ብስኩት እየለገሱን።)
ታዲያ ለዚህ ሁሉ መከራና የሰቆቃ እሽክርክሪት ተጠያቂው ማን ሊሆን ይችላል? አንዳንዶቻችን በሀገራችን ለተፈጠረው ችግርና መከራ እጆቻችንን በሀገራችን የነበሩና አሁን ያለው መንግሥታት ላይ እንቀስራለን። በንጉሡ ዘመን የዐፄ ኃይለሥላሴ ቀዳማዊን አገዛዝ ስንረግምና ስንቃወም አብዮቱ ፈነዳ። “ኢትዮጵያ ትቅደም! ያለ ምንም ደም!” ተብሎ ተለፈፈብን። ወታደራዊው መንግሥት ዙፋኑን በልጆቻችን አስክሬን ላይ ሰርቶ ገዛን። ከዚያም ቁምጣ የታጥቁ፣ “ከደርግ ብሶት የተወለድን ነን” የሚሉ “ነፃ ልናወጣችሁ፣ ዲሞክራሲ ልናመጣላችሁ ነው” አሉን። የከተሞቻችንን በሮች ከፍተን አስገባናቸው። ብዙም የተሻለ ነገር አልመጣም። ሀገር ወደብ አልባ ሆነች። ሀብት በጥቂቶች ተመዘበረ። ህዝብን በጎሣና በዘር ለመከፋፈል ተሞከረ። በዲሞክራሲ ስም ከአንድ በመቶ በታች የሆኑት ጨረቃ ላይ ሲመጠቁ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ የሆነው ህዝባችን ቁልቁል ወረደ። ለሠላምና ለፍትህ የቆሙ ለወራት ጨለማ ቤት በግፍና በጭካኔ ይታሰራሉ። የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አይከበርም። መንደሮች ይቃጠላሉ።
አዎን! - በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር ዋነኛው ምክንያት የመልካም አስተዳደር ጉድለትና የሕግ የበላይነት አለመኖር መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው።
ነገር ግን በዚህ ጽሑፌ ከመንግሥታት ሌላ መጠየቅ ያለበት አካል እንዳለ ለማሳየት እሞክራለሁ። ይህም አካል እኔና እናንተ ነን። እያንዳንዳችን ለኢትዮጵያ ሀገራችን ድህነትና መቆርቆዝ በርግጥ ተጠያቂ እንደሆንን ማወቅና መቀበል ይኖርብናል። ሁላችንም መጠኑ ይለያያል እንጂ ሀገራችንና ወገናችንን ጎድተናል። ጥይት ላንተኩስ እንችላለን። ነገር ግን ወንድሞቻችን ሲገደሉ ዝም ማለታችን እራሱ ተጠያቂ ያደርገናል።
በሀገራችን እኮ ነፍሰ ገዳይና ጨቋኝ የሚበዛው እኛ ስለምንፈቅድላቸው ነው። በጥቅም ይገዙናል፣ ያስፈራሩናል፤ ከዚያ ለፍቃዳቸው ሕሊናችንን ሸጠን እንገዛለን። በኛ ላይ ቆመውም በሀገራችን ላይ ግፍ ይፈጽማሉ። ስለዚህ አሁን ያለውን አገዛዝ ብቻ ከመርገም ይሄንን አገዛዝ የፈጠርነውንና እንዲኖር ያደረግነውን እኛኑ እራሳችንን እንውቀስ።
ችግሩ የገዢዎች አምባገነንነት ላይ ሳይሆን ችግሩ የኛ አምባገነንነትን መፍቀዱና እሺ ብሎ መቀበሉ ላይ ነው። ችግሩ እግዚአብሔር የሰጠነን ሰብዓዊ ነፃነት ለጥቂቶች አሳልፈን መስጠቱ ነው። ችግሩ የወደፊቱንና የሚበጀውን ከማየት ይልቅ በጥቃቅን ነገሮችና ባረጁት ባፈጁት ያለፉት ነገሮች መተብተባችን ነው። ችግሩ በራሳችን አለመተማመናችንና አለመተባበራችን ነው። ችግሩ መተሳሰብና መደጋገፍ እኛ መካከል አለመኖሩ ነው።
መተሳሰብና መደጋገፍ እንደሚያስፈልግ ለማስረዳት፣ “አሁን አንድ ኢትዮጵያዊ ጂንስ መልበስ አለበት? ካኪ አይለብስም። ዊስኪስ መጠጣት አለበት? ጠጅ አይጠጣም” ብሎ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንጂንየሪንግ ፕሮፌሠር የነበረ አንድ ምሁር ከአሥር ሦስት ዓመት በፊት የተናገረው ቁም ነገር ትዝ ይለኛል። ብልጽግና፣ ሀብትና መሻሻል መልካም ነገር ነው። ግን ከራሳችን አልፈን የወደቀውን ሌላው ኢትዮጵያዊ ወገናችንን ለማንሳት እጆቻችን አጥረው ካልተዘረጉ ይህ የሞራል ውድቀት ነው።
በሰሜን አሜሪካ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። በሕግ አንድ ሠራተኛ በሰዓት ከ7 $ (ዶላር) በታች አይከፈለውም። በጣም ዝቀተኛ ደምወዝ አገኘ ቢባል አንድ ሰው ቢያንስ በዓመት 15,000 $ ያገኛል ማለት ነው። የካናዳ ወይንም የአሜሪካ መንግሥት ቢያንስ 15% (2,500 $ በዓመት) ግብር ያስከፍላል። በሺህ የሚቆጠሩ የተማሩ ከ50፣ ከ70፣ ከ100 ሺህ ዶላር በላይ በዓመት የሚያገኙ ኢትዮጵያውያን አሉ። በንግዱ ሥራ ተሰማርተው የከበሩና በርካታ ሱቆችና ኢንቨስትመንቶች ያሏቸውም የሚናቁ አይደሉም።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በቀን አንድ ዶላር ለኢትዮጵያ ቢለይ፤ በዓመት 365 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል። በዚህ ገንዘብ በአየር ጠባይ መለዋወጥ በየጊዜው ለረሃብ የሚጋለጠውን ወገናችንን የፈረንጆችን እጅ ሳንጠብቅ ማዳን እንችል ነበር። ታዲያ አሁንም የነጮች ጥገኛ መሆናችን መንፈሣዊ ክስረታችንን አያሳይምን? በሀገራችን ላለው ድህነት ተጠያቂዎች አያደርገንምን? ለካናዳና ለአሜሪካ 15% ከከፈልን ወገኖቻችንን ከረሃብ ለማውጣትና ኢትዮጵያ በረሃብ ምሳሌነት እንዳትጠቀስ ለማድረግ ከደምወዛችን ከዜሮ ነጥብ ሦስት በመቶ በታች መክፈል ያቅተናል? ለልመና በጂ-20 በጂ-ስምንት ስብሰባ መጋበዝ የሚያኮራና አንበሳ የሚያሰኝ ነውን?
እኛ ኢትዮጵያውያን ከቻይናዎች፣ ከጃፓኖችና ከነጮች በምን እናንሳለን? ሀገራችንስ የተፈጥሮ ሀብት ከማናቸውም ባላነሰ መልኩ እግዚአብሔር የቸራት አይደለችምን? በዓለም የተደነቁ ምሁራን፣ ሣይንቲስቶች፣ የሕግ ባለሞያዎች፣ መኃንዲሶች፣ ሐኪሞች ያሏት ሀገር ሆና ኢትዮጵያን ከድህነቷ ማንሳትና መቀየር እንዴት ያቅተናል?
መልሱ “አያቅተንም!” ነው። ከቃሊቲ እስር ቤት እንደተፈቱ አንድ ወቅት ዶ/ር በፈቃዱ ደግፌ በስዊድን ለሚገኝ የሬዲዮ ጣቢያ የተናገሩት አንድ አባባል ነበር። “ኢትዮጵያን የተቸገሩና የተጨቆኑ ከእርሷ የሚሸሹ ሳይሆን ወደ እርሷ የሚሸሹ እናደርጋታለን። ይቻላል!” ነበር ያሉት። እውነታቸውን ነው። ኢትዮጵያን የአፍሪካ ጃፓን ማድረግ ይቻላል። የሚያስፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው። እርሱም ፍቅርና መተሳሰብ ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልዕክቱ የፍቅርን ትርጉም ይሰጠናል። “ፍቅር ይታገሳል፣ ፍቅር ያስተዛዝናል፤ ፍቅር አይቀናናም፤ ፍቅር አያስመካም፤ ፍቅር አያስታብይም፤ ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም፤ ፍቅር አያበሳጭም፤ ክፉ ነገር አያሳስብ፤ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመጻ ደስ አይለውም፤ ሁሉን ይታገሣል፤ …” በማለት በዝርዝር አስተምሯል። (ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ፩፣ ም. ፲፫፣ ቁ. ፬-፯)
ፍቅር ካለን አንዳችን በአንዳችን ላይ በበቀል፣ በእልህና በጭካኔ አንነሳም። ፍቅር ካለን ያለፈውን መጥፎ ታሪካችን ላይ ብቻ “እኝኝ” ብለን ልባችንን ለእርቅና ለይቅርታ አንዘጋም። ፍቅር ካለን በወንድማችን ሬሳ ላይ እየተረማመድን በደም የተገኘ ሀብት አናከማችም። ፍቅር ካለን ጎንበስ ብለን የወንድማችንን እግር እናጥባለን እንጂ በባዶ ትዕቢት አንሞላም። ፍቅር ካለን ያለችንን አንድ ዳቦ ግማሹን ቆርሰን ለተራበው ወንድማችን እናካፍላለን። ፍቅር ካለን በሚሊዮን የሚቆጠር ወገናችን የሰቆቃ እንባ እያለቀሰ በዳንኪራና በጨዋታ ንዋያችንን አናጠፋም። ፍቅር ካለን ያለፈን ክስ በመምዘዝ ሠላማዊ ሰውን በጨለማ ቤት ውስጥ በግፍና በጫካኔ አናስርም። …
“ፍቅር ከወዴት ትመጣለች?” የሚል ጥያቄ ሊጠየቅ ይችላል። መልሱ ግልጽና ቀላል ነው። ፍቅር የፍቅር አምላክ ከሆነው ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ትገኛለች። መጽሐፉ እንደሚል እግዚአብሔር እራሱ ፍቅር ነው።
አሜሪካኖች ሀገራቸውን የመሰረቱት በእግዚአብሔር ላይ ነው። የሚጠቀሙበትን ገንዝብ አገላብጠን ብንመለከት እንኳን ”በእግዚአብሔር እናምናለን” የሚለው ዐረፍተ ነገር ተጽፎበታል። በእርሱ ላይ ተመስረተዋልና እግዚአብሔርም ባረካቸው።
እኛ ኢትዮጵያዊያን በጣም ኃይማኖተኞች ነን። ነገር ግን ኃይማኖተኝነታችን ብዙውን ጊዜ በውጭ ብቻ ነው። መንፈሣዊ አባቶቻችን በአንድ ጎን እየተራገሙና እየተወጋገዙ ስጋ ወደሙን ይዘው ይቀድሳሉ። “ይህ ህዝብ በከንፈሩ ያከበረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው” ተብሎ እንደተጻፈ፤ በከንፈራችን እንጂ በልባችን እግዚአብሔርን አልፈለግነውም። በከንፈራችን ፍቅርን እናወራለን፤ ልባችን ግን በጥላቻና በቂም የተሞላ ነው። ታዲያ እግዚአብሔር እንዴት አድርጎ ይታረቀን?
እግዚአብሔር ሊባርከን፣ ሊያድሰንና ሊጎበኘን የታመነና ጻድቅ ነው። በግላችን በቤተሰባችንና በሀገራችን መጀመሪያና ተቀዳሚ ካደረግነውና “በእግዚአብሔር እናምናለን” የሚለውን ቃል በልባችን ካተምን የፍቅር መንፈሥ በምድራችን ይፈልቃል። ፍቅሩም እንድንተቃቀፍ፤ እንድንሳሳም፤ እንድንሸካከም ያደርገናል።
እኛ የአስተሳሰብ ለውጥ ካደረግን፣ ከራሳችን ያለፉ ሥራዎችን ለመሥራት ከወሰንን፣ ከታጠርንበት ግላዊ የአስተሳሰብ ማዕቀፍ ከወጣን፣ ለተጠቁትና ለተበደሉት ለመበለቶች ከተሟገትን፣ ግፍ ሲሠራ፣ ዜጎች በግፍ ሲታሰሩ ከንፈር መምጠጥ ሳይሆን በድርጊት ላይ የተመሰረተ ተጨባጭ ተቃውሟችንን ካሰማንና በራሳችን ከተማመንን በጋራ በአንድነት መለወጥ የማንችለው ነገር የለም። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳንና ሌሎች የሕሊና እስረኞችን ማስፈታት እንችላለን። በኢትዮጵያ የምንፈልገውን የዲሞክራሲ ሥርዓት መገንባት ሀገራችንንም ከድህነት ማውጣት እንችላለን።
ሁሉ ነገር በእጃችን ነው። ወ/ት ብርቱካን በዋሽንግተን ዲስ ካደረጉት ንግግር አንዲቷን ልውሰድና፤ ሀገራችንን ለመለወጥ፣ ለሀገራችን ከወሬና ከምኞት ያለፈ ተጨባጭ ሥራን ለመሥራት ዝግጁዎች ነን? እግዚአብሔር ልቦናችንን ለፍቅሩ፣ አዕምሯችንን ለመልካምና ጤናማ አስተሳሰቦች ይክፈትልን!



