”ብርቱካንን እወዳታለሁ” (አማኑኤል ዘሰላም)
ወርቀ አማኑኤል ዘሰላም ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
ከሀገሬ ተሰድጄ የስደት ኑሮ ከጀመርኩኝ በርካታ ዓመታት አለፉ። አዲስ አበባ የነበርኩ ጊዜ የግል ትምህርት ቤት ስለተማርኩ እንግሊዘኛ ብዙ አይችግረኝም። ከፈረንጆች ጋር በኢትዮጵያዊ አነጋገር (accent) ደህና እግባባለሁ። ነገር ግን እንደ አማርኛ የውስጤን ሃሳብ መናገር አልችልም።
አንድ ቀን አብሮኝ የሚሠራ የሕንድ ተወላጅ የሆነ ጓደኛዬ ቤት ተጋብዤ ሄድኩ። በዚያ ከሁለት ልጆቹ አንዷ፣ ኮሌጅ ልትገባ አንድ ዓመት የቀራት፣ በጉጅራቲ (በሕንድ ከሚነገር ቋንቋዎች አንዱ) አባቷን ስታናግር ሰማሁ። ልጅቷ በቅርብ ከሕንድ የመጣች መሰለኝ። ነገር ግን ልጆቹ አሜሪካ ሀገር እንደተወለዱ ጓደኛዬ ሲነግረኝ ተገረምኩ። ለምን? የማውቃቸው ብዙ ኢትዮጵያውያን ልጆቻቸው አማርኛ የማይናገሩ በመሆናቸው።
ይህ ሕንድ እንዴት ልጆቹን በሀገሩ ቋንቋ እንዳስተማረ ጠየኩት። ”ሙሉ ለሙሉ የወላጆች ጉዳይ ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን በሚፈልጉበት መስመር በልጅነታቸው መምራት ካልቻሉ ጥፋቱ ልጆቹ ላይ ሳይሆን ወላጆቹ ላይ ነው።” አለኝ። እኔም ያን ጊዜ፣ የኔ ልጆች አማርኛ የሚያወቁ ይሆናሉ ብዬ በውስጤ ዛትኩ።
ጥቂት ዓመታት አለፉ። ጊዜ መድረሱ አይቀርም፣ እዚሁ አሜሪካን ሀገር ከተዋወኳት ከአንዲት የወንዜ ልጅ ጋር ትዳር መሰረትኩ። እናቷን የምትመስል ቆንጅዬ ሴት ልጅ ወለድን። ከባለቤቴ ጋር ተመካክረን የአማርኛውን ጉዳይ ከልጃችን ጤንነት ቀጥሎ ትልቅ ቦታ ሰጠነው። ይኸው አሁን አሥራ ሁለት ዓመቷ ነው፤ ቀልጣፋ የአማርኛ ተናጋሪ ወጥቷታል። ወላጆቻችን ከኢትዮጵያ እኛን ለመጠየቅ ሲመጡ እንደሌሎች የሐበሻ ልጆች የኔ ልጅ ተርጓሚ አላስፈለጋትም። ኢትዮጵያ ለጉብኝት ስትሄድም እንደልቧ እያወራች ተቀላቅላና ተሳስቃ ትመለሳለች።
ከአራት ወራት በፊት አንድ ነገር ሆነ። ስልክ ይዤ አወራለሁ። ልጄ ትንሽ ራቅ ብላ ታዳምጣለች። ያናደደኝ፣ ያሳሳዘኝ ነገር እንዳለ አወቀች። ስልኬን ጨርሼ ወደ ሶፋው ሄጄ ተቀመጥኩ። እንደመተከዝ ብሎኛል። የምትሠራውን ትታ ከጎኔ ተቀመጠች። ”ምን ሆነሃል ባባ?” አለችኝ። ”ዳዲ” የሚለውን ስለምጠላው ”ባባ” ነው የምትለኝ። ”ደህና ነኝ። ምንም አልሆንኩም” አልኳት ያበሳጨኝንና ያሳዘነኝን ለመሸፋፈን ፈልጌ።
ዝም ብላ ለጥቂት ደቂቃ ደረቴ ላይ ከተኛች በኋላ ”ብርቱካን ማን ናት?” አለችኝ። ወዲያው ”ክው አልኩኝ”። በስልክ ሳወራ የነበረው በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የደረሰውን ግፍ በተመለከተና እንዴት አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት ወያኔ-ኢህአዲግ እንደፈጸመ ነበር። የምመልሰው ግራ ገባኝ። ምን እንደምላት አሰላሰልኩና ”አንድ ታዋቂ ሴት ናት” የሚል መልስ ሰጠሁ። ”ኢትዮጵያ ነው የምትኖረው? ምን ሆነች ባባ?” አለችኝ። ”አዎ! ኢትዮጵያ ነው ያለችው። ታስራለች” ብዬ መለስኩ። ጥያቄው አላቆመም። ”ለምን ታሰረች?” የሚል ጥያቄ ተከተለ። ቁና ቁና መተንፈስ ጀመርኩ። ኢትዮጵያን እንዳትጠላብኝ በኢትዮጵያ የሚደረገውን ግፍ ልነግራት አልፈለኩም ነበር። እርሷ ግን ለምን እንደሆነ አላውቅም አጥብቃ ጠየቀች።
”ምንም ነገር ሳታጠፋ ነው የታሰረችው” አልኳት። ”እንዴ ባባ? ጀጅ የለም እንዴ?” አለች። ”ጀጅ አይደለም ዳኛ ነው በአማርኛ የሚባለው” ብዬ እርማት ሰጠሁና ”ዳኛ አለ። ግን እዚያ ያለው መንግሥት ጥሩ መንግሥት አይደለም። ዝም ብሎ ሰው ያስራል። ሰው ይገድላል። ሕግ አያከብርም። ዳኛ አይከበርም” አልኳት።
”ለዚህ ነው እናንተ አሜሪካን ሀገር የመጣችሁት?” አለችኝ። ”አዎን!” ብዬ መለስኩ። ”ኢትዮጵያን ጠላኋት ባባ” አለችኝ። ወዲያው ውስጤ ደንግጦ ”ይሄማ አይሆንም። ኢትዮጵያ ማለት እኮ እኔ፣ እናትሽ፣ አክስቶሽ፣ አጎቶችሽ፣ … ማለት ነው። ኢትዮጵያን መጥላት ማለት እኛን መጥላት ማለት ነው። አንቺን እራስሽንም መጥላት ነው።” ብዬ የአሜሪካንን ታሪክ በማንሳት ለማስረዳት ሙከራ ጀመርኩ።
አሜሪካን ሀገር ስለነበረው የሲቪል ራይት እንቅስቃሴ በተለይም ስለዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግና ሮዛ ፓርክ ፕሮጀክት ነገር በትምህርት ቤቷ ሠርታ ስለነበረ ያንን አስታወስኳት። በአሜሪካ የነበረውን ችግር፣ እንዴት ጥቁሮች እንደተበደሉ በሰፊው ገለጽኩላት። ”አሜሪካ መጥፎ ሰዎች ቢኖሩም ጥሩ ሰዎች ብዙ ስለደከሙ ሀገሪቷን ቀየሯት። ኢትዮጵያንም በተመለከተ ኢትዮጵያን መጥላት ሳይሆን መፍትሄው እንደ አሜሪካ ኢትዮጵያን መቀየር ነው። እነብርቱካን ልክ ያኔ እነ ማርቲን ሉተር ኪንግና ሮዛ ፓርክ እያደረጉት እንደነበረው እያደረጉ ነው። ያኔ ማርቲን ሉተር ኪንግ ሳያጠፋ እንደታሰረው ነው አሁንም ብርቱካን ሳታጠፋ ነው የታሰረችው።” አልኳት።
”አንተ ታውቃታለህ?” አለችኝ። ”አዎ! አውቃታለሁ” አልኳት። ”እኔንስ ታውቀኛለች” አለች። ”አንቺን አታወቅሽም። ግን ለአንቺና ለሌሎች ልጆች ወደፊት ጥሩ ሀገር እንዲኖራችሁ ለማድረግ ስትል ነው የታሰረችው” አልኳት። ”ልጅ አላት?” አለችን። ”አዎ! የአራት ዓመት ሴት ልጅ አላት።” አልኳት። ያኔ ልጄ ማልቀስ ጀመረች።
ከሁለት ቀናት በኋላ ኮምፒዩተሬ ላይ ቁጭ ብዬ ስሠራ አሁንም እንደልማዷ መጣችና እግሮቼ ላይ ቁጭ አለች። ”ባባ የብርቱካንን ፎቶ ታሳየኛለህ?” አለችኝ። ወዲያው ወደ ድረ ገጾች ሄጄ አሳየኋት። ”ባባ እኔ ብርቱካንን እወዳታለሁ!” አለችኝ። ”አንቺ ብቻ አይደለሽም። በኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብ ሁሉ ነው የሚወዳት። አይዞሽ ትፈታለች። እግዚአብሔር ከርሷ ጋር ነው። እግዚአብሔር ካለ ደግሞ በዓይንሽ ታያታለሽ። ሁልጊዜ ማታ ማታ ግን ከመተኛትሽ በፊት ፀልይላት” አልኳትና ግንባሯን ስሜ አሰናበትኳት።
አንድ ማታ አምሽቼ ገባሁ። ልጄን ሳልስማት ስለተኛች ወደ ክፍሏ አመራሁ። እጆቼን በራሷ ላይ ጭኜ እግዚአብሔር ልጃችንን እንዲባርክልን አጭር ፀሎት አደረኩና ግንባሯን ስሜ ተነሳሁ። ከክፍሏ ልወጣ ስል በግድግዳዋ ላይ ከነ ሃና ሞንታናና ሌሎች ፎቶዎች መካከል የተለጠፈ አንድ ፎቶ አየሁ። ቆም አልኩኝ። ከኮምፒዩተራችን ላይ የታተመ የብርቱካን ሚደቅሳ ፎቶ ነበር።
ውስጤ ቀለጠ። ፍርድ ቤት ቢፈቅድም ብርቱካን ሚደቅሳ ከወዳጅ ዘመድ እንዳትገናኝ መታገዷ ይታወቃል። ነገር ግን በዚያን ወቅት ብርቱካን ሚደቅሳን ያገኘኋት መሰለኝ። በጆሮ የሚሰማ ድምፅ የለም፤ ግን ልብ የሚያዳመው ድምፅ ነበር። ከብርቱካን ሚደቅሳ የሚመጣ መልዕክት ነበረ። ”እኔ አንድ ሰው ነኝ። ጉዳዩ የኔ ጉዳይ አይደለም። ጉዳዩ የሀገር ጉዳይ ነው። ጉዳዩ የልጆቻችን ጉዳይ ነው። እያንዳንዳችን ለመስዋዕትነት ተዘጋጅተን ትግሉን ከግብ ማድረስ አለብን። እኔ እስረኛ አይደለሁም። በመንፈሤ ነፃ የወጣሁ ነፃ ሰው ነኝ። እስረኞቹስ ያሰሩኝ ሰዎች ናቸው፤ በጥላቻና በዘረኝነት የታሰሩ። እስረኞቹስ ከቃሊቲ ውጭ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው፤ በፍርሃት የታሰሩ። እስረኞቹ ነፃነት በቀላል የሚመጣ መስሏችው የሚቅበዘበዙ ናቸው። በተስፋ መቁረጥ የታሰሩ። እስረኞቹ እራሳቸውን ለባርነትና ለጊዚያዊ ጥቅም ሸጠው ሰብዕናችውን ያዋረዱ ናቸው” የሚል መልዕክት ነበር።



