አማኑኤል ዘሰላም This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. (ሚያዝያ 29 ቀን 2001 ዓ.ም.)

ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ሁኔታ፣ የፖለቲካ መሪዎችን ተጠያቂ የሚያደርጉ ጥቂቶች አይደሉም። አንዳንድ ሰዎች “መሪ የለንም!” ብለው እስከመናገርም ይደርሳሉ።

 

እርግጥ ነው የፖለቲካ መሪ ተብዬዎች፣ ተስማምተው መሥራት አለማቻላቸው፣ እርስ በርስ መጠቃቃታቸው፣ የተወሰኑትም ጭራሹኑ ከገዢው ፓርቲ ጎራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መሰለፋቸው ትግሉን ክፉኛ ከመጉዳቱም በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ስቃይና ሰቆቃ እንዲራዘም ማድረጉ የማይካድ ነው። በተቃዋሚው ወገን፣ እጅግ በጣም ልብን የሚያደሙ ብዙ ስህተቶች ተሠርተዋል።

 

በተለያዩ ዘርፎች “መሪ ነን፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ እናስባለን” የሚሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሚያንቀሳቅሱ የሚያውጁ ጥቂት አይደሉም። ነገር ግን “የትኞቹ ናቸው እውነተኞች? ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ ለህዝብ ጥቅም የሚያስቡ?” ብለን ብንጠይቅ ግን በጣት የሚቆጠሩ ሆነው እናገኛቸዋለን።

 

ከነዚህም ጥቂት መሪዎች ውስጥ በቀዳሚነት የማስቀምጣት አንድ ሴት አለች። አምባሣደር እምሩ ዘለቀ “የኢትዮጵያ እመቤት” ብለው የጠሯት ብርቱካን ሚደቅሳ ናት።

 

ብርቱካን ሚደቅሳ መኖሪያዋ ቃሊቲ እስር ቤት ከሆነ ይኸው አራት ወራት ከስምንት ቀናት አለፈ። አሁንም ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር በምታህል ጠባብ ክፍል ውስጥ ለብቻዋ፣ በጨለማ ተቀምጣለች። ሕገ መንግሥታዊ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቷ ተረግጦ በነፍሰ ገዳዮችና ሕጻናትንና ሴቶችን በሚደፍሩ (Rapist) ላይ እንኳን ያልደረሰ ቅጣት፣ በዚች ለእውነት፣ ለፍትህ፣ ለሠላምና ለኢትዮጵያዊነት በቆመች ወጣት እህታችን ላይ እየደረሰ ነው።

 

ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ለልጇም ሆነ ለራሷ በሥጋ በጣም በሚመች በአሜሪካ መኖሪያዋን አድርጋ፣ የአንድ ዳያስፖራ-ወለድ ፖለቲካ ፓርቲ መሪ ሆና መቀጠል ትችል ነበር። ያም ደግሞ ካልሆነ፣ በኢትዮጵያ ውስጥም በገንዘብና በጥቅም የገዢው ፓርቲ አቀንቃኞች እንደሆኑትና የቀድሞ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ እንደነበሩት እንደ አንዳንዶቹ፣ ገዥው ፓርቲ የሚላትን እያደረገች፣ ለገዢው ፓርቲ ባለሥልጣናት “እሺ ጌቶቼ!” ብላ በመታዘዝ፣ ይሄን ጊዜ በመንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን አግኝታ መኖሩ የሚያቅታት አልነበረም።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ግን ከራሷ ጥቅም ይልቅ የሀገርን ጥቅም፣ ከማጭበርበር ፖለቲካ ይልቅ እውነትን፣ ከጦረኝነት ይልቅ ሠላምን፣ ከፍርሃትና ከመሽመድመድ ይልቅ ቆራጥነትን ያሳየች ሴት ናት።

 

“እኛ ዝግጁ ነን። እናንተ ዝግጁ ናችሁን?” ብላ ዋሽንግተን ዲሲ ተሰብስበው ለነበሩ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ጥያቄ አቅርባ እንደነበረ አስታወሳለሁ። ያኔ እንደዚያ ስትል “እኛ ከኋላ ሆነን እናንተን አናስቀድምም። ከፊት ቀድመን ግን እናንተን እናስከትላለን። ታዲያ እኛ ስንቀድም እናንተ ትከተላላችሁ ወይ?” ማለቷ ነበር።

 

አንዳንድ እንደ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም አይነት መሪዎች አሉ። አስታወሳለሁ ኮሎኔል መንግሥቱ “አንድ ሰው እንኳን ቢቀር እንደ ቴዎድሮስ ሽጉጤን ጠጥቼ እሞታለሁ” ሲሉን ነበር። እኝህ ሰው የብሔራዊ ውትድርና እያሉ በጉልበት የድሃውን ልጅ ለጦርነት ማግደውታል። ‘ድሃው ወደ ጦሌ፣ ያለው ወደ ቦሌ’ እንደተባለው ማለት ነው። የእኝህ ሰው ጀግንነት የአፍ ጀግንነት ነበር። የበታቾቻቸውን ለመግደልና ለማስገደል እንደውም በሌላው ሕይወት ለማዘዝ አንደኛ ነበሩ። ወሳኝ ጊዜ ሲምጣ ግን በቦታው አልተገኙም። ሀገር ጥለው፣ ህዝብን ክደው ኮበለሉ።

 

ከኋላ ሆነው ሌላውን “ቅደም! በርታ! አይዞህ!” የሚሉ ራስ ወዳዶች፣ በሌሎች ሬሳ ላይ ተራምደው እንዲያልፍላቸው የሚፈልጉና እራሳቸውን ሥልጣን ላይ ከማወጣት ውጭ ሌላ አጀንዳ የሌላቸው መሪ ነን የሚሉ አሉ። እነዚህ መሪዎች ከኋላ ሆኖ በጎችን እንደሚነዳ፣ ተኩላ ሲመጣ በጎቹን ለተኩላ አሳልፎና አጋልጦ እንደሚሸሽ እረኛ ናቸው። በሠላሙ ጊዜ በመድረክ የሚታዩና “አለሁ! አለሁ!” የሚሉ፣ መከራ ሲመጣ ግን ሌላውን አጋልጠው የሚደበቁ ናቸው።

 

እነዚህ ሰዎች የምንፈልገውን ይነግሩናል። መስማት ያለብንን ግን አይነግሩንም። ለጊዜው ስሜታችንን ይቀሰቅሱታል። ቆየት ብሎ ግን እውነታውን ስንረዳ መታለላችን ይገባንና እናዝናለን። እነዚህ ሰዎች በተጨበጠ ነገር ያልተመሰረተ የፉከራ ፖለቲካ ያራምዳሉ። ነጋም ጠባም ወያኔ መወደቁ ነው ይሉናል። ጠዋትና ማት ከውጭ ሆነው አገዛዙን ይረግማሉ። ነገር ግን የተጨበጠ ነገር ሲሠሩ አይታዩም።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ግን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲ ትግል “አልጋ በአልጋ ላይ ነው” አላለችም። ሠላማዊው ትግል መስዋዕትነት እንደሚያስከፍል እውነቱን ነግራናለች። የዚህ የሠላማዊ ንቅናቄ መሪ ሆና ስትወጣ ልትታሰር፣ ልትገደል፣ አሁን እየደረሰባት ያለው ግፍ ሊደርስባት እንደሚችል ታወቅ ነበር። የገዢው ፓርቲ መሪዎችን ጨካኝና አረመኔ እንደሆኑ አላጣችውም።

 

ነገር ግን ውስጧ በጀግንነት ተሞላ። ጠመንጃ ሳትይዝ ጉልበተኞችን ገጠመች። እነርሱ ስጋዋን አሰሩ። እርሷ ግን ሕሊናቸውን አሰረች። በሄዱበት ቦታ እንዲሸማቀቁ አደረገቻቸው። ለዚህም ምሳሌ እንዲሆን አቶ መለስ ዜናዊ ከቢቢሲ ሃርድቶክ ጋዜጠኛ ጋር ያደረጉት እርስ በርሱ የሚቃረን፣ ውሸት የተሞላበትና የተምታታበትን ቃለ መጠይቅ መጥቀስ ይበቃል።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ወሬ ብቻ አላወራችም። በሥራዋ ማንነቷን ያሳየች ታላቅ የኢትዮጵያ ልጅ እንደሆነች እንኳን ኢትዮጵያውያን የውጭ ሀገር ዜጎች የሚናገሩላት ነው።

 

ታዲያ እንደዚህ አይነት መሪ እያለን “መሪ የለንም! መሪ አላገኘንም!” ብለን መናገራችን ምን ይባላል? እንዲህ አይነቶቹን መሪዎች፤ ‘መሪያችን’ ካላልን ማንን ነው ታዲያ መሪያችን ልንል የምንችለው? እራስን ለህዝብ ጥቅም አሳልፎ ከመስጠት ሌላ አንድ መሪ ሌላ ምን ሊያደርግ ይችላል?

 

እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን በኛ ላይ እያነገስኳት ወይም እየካብኳትም አይደለም። እውነቱን፣ ያደረገችውንና የሠራችውን ነው የጻፍኩት። ነገ ከእስር ቤት ስትወጣ የማልስማማበት አቋም ይዛ ከተንቀሳቀሰች ወይም ሰው ናትና ስትሳሳት የእርሷ ተቃዋሚ ሆኜ ልቀርብ እችላለሁ።

 

አሁን ግን በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥም ያለውን ኢትዮጵያዊ አንድ ያደረግች፣ ለዲሞክራሲ፣ ለመብት መከበር፣ ለፍትህና ለነፃነት የሚደረገው ትግል አመላካች የሆነች ሴት ሆናለች።

 

ስለሆነም የዚች እህታችንን መፈታት ሁላችንም ትልቅ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያውያን ስናደርግ የነበረውን የ‘ወት ብርቱካን ሚደቅሳ ትፈታ!’ ግፊት የበለጠ ከማጠናከሩ ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ