የግብርናው ነገር እውነታው ሌላ፤ የሚባለው ሌላ (ፕ/ር ሰይድ ሐሰን)
ፕሮፌሠር ሰይድ ሐሰን፤ መሪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
በመሪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስና ፋይናንስ ዲፓርትመንት ውስጥ የኢኮኖሚ ፕሮፌሠር የሆኑት ዶ/ር ሰይድ ሐሰን "የግብርናው ነገር እውነታው ሌላ፤ የሚባለው ሌላ” በሚል ርዕስ ባቀረቡት በዚህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ያለውን የግብርና መስክ፣ የመንግሥትን የመሬት ፖሊሲ፣ ድሃው የኢትዮጵያ ገበሬ ያሉበትን ችግሮች፣ በተለይም በኢህአዲግ የሥልጣን ዘመናት የደረሱበትን በደሎች፣ ... በመተንተን የመፍትሔ ሃሳቦችን ጠቁመውበታል። መልካም ንባብ!
የግብርናው ነገር እውነታው ሌላ፤ የሚባለው ሌላ
ክፍል አንድ፤
አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ስናጤን ከማንኛውም ችግር የበለጠው የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ ሲሆን፤ ህዝቡን መፈናፈኛ አሳጥቶትና አስጨንቆትም መላው እንዲጠፋበት አድርጎታል። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት በሄደባቸው ወቅቶች የኅብረተሰቡን ኑሮ ሁኔታ ጠጋ ብሎ ሲያይ (በተለይ በከተማው) ሀገሪቱን በጎበኘ ቁጥር ድህነቱ በአሰቃቂ ሁኔታ እየተስፋፋ መሄዱን ደጋግሞ ተገንዝቧል።
እኔም ሆንኩ አሁን በቅርቡ የተወለዱባትን ሀገር ጎብኝተው የሚመለሱት ሰዎች በተደጋገመ መልክ ከሚናገሯቸው ቃላቶች መካከል “ኑሮ እንዲህ ተወዶ እያለ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት ሊቋቋመው ቻለ?!” የሚል ነው። አንዳንድ በድህነት የተጎዱትን የኅብረተሰብ ክፍሎች ጠጋ ብለን ብናያቸውና ከአንደበቶቻቸው የሚወጡትን ስንሰማ “ዛሬ ምን በልቸ ልደር?” በሚል ሃሳብ ለዕለቱ የሚበሏትን ማግኘት እንጂ “የወደፊቱ ኑሯችንን እንዴት እናሻሽል?” የሚለው ሃሳብ እንደ ቅንጦት ተቆጥሮ በአዕምሯቸው እንደማይንሸራሸር ነው። በርካታ የቤተሰብ አባላትም፤ የጨለመውን ቀን ለማሳለፍ በተራ እንደሚመገቡም ሰምተናል፤ አይተናልም። አንዳንዶቹም “በቀን ሁለት ጊዜ መመገብ የሚባለው በቤታችን ውስጥ ከተከሰተ ወራቶች አልፈዋል” የሚሉም አሉ።
ረሃብ ከመግደሉም አልፎ የለማኞችን ገመና አጋልጦ ያዋርዳል፤ ለበሽታ ይሰጣል፤ አካለ-ስንኩል ያደርጋል፤ ከረሃቡ የተረፉትን ልጆችም ይህችን ዓለም ለቀው እስኪሄዱ ድረስ አቅመ-ቢስና የአዕምሮ ስንኩል እንዲሆኑ ያደርጋል፤ … አዕምሮንም ያስታል። እኔ በገጠር ያደግሁ የገበሬ ልጅ ስለሆንኩ እነዚህን ክስተቶች በተግባር አይቻለሁ። እንደነዚህ ያሉት አባዜዎች እ.ኤ.አ. የ1974 ዓ.ም. እና በተደጋጋሚ የተከሰቱት ድርቆችና ረሃቦች ያደረሷቸውን ችግሮች በመከታተሌ፤ እነዚህን ችግሮች ሳስታውስ አሁንም እንባየ ዱብ - ዱብ ይላል። በእርግጥ ብዙዎቻችን አንጋፋው ኢትዮጵያዊ ዘፋኝ ጥላሁን ገሠሠን ተከትለንም “ዋይ! ዋይ! …” ብለን እየዘፈን አልቅሰናል። ልዩነቱ ግን ከዚያ ኅብረተሰብ አብራኮች እንደመሆናችን መጠን ከማልቀስ ባሻገር ምን አድርገንለታል? ምንስ እያደረግን ነው? ህዝባችንን ረሃብ እየፈደፈደው እያለ ለዋጋ ግሽበቱ ምክንያት ገበሬው ሀብታም ሆኖ የመሸመት ፍላጎቱ ስለጨመረ ነው ብለው ሲያላግጡበት ምን አድርገንለታል?
የኑሮ ውድነቱን አስመልክቱ ትንሽ ለመጨመር ያህል፤ አሁን በቅርቡ የወጡት መረጃዎች እንዳመለከቱት የምግብ ዋጋ ባለፉት የጥርና የየካቲት ወሮች (ያውም በመኸሩ ጊዜ) ከ104% ባላነሰ ዓመታዊ አቆጣጠር ጨምሯል (በታህሣሥ ወር 96% ጨምሮ ነበር)። ለዚህም የጥሬ እህል ዋጋ መናር ዋናው መንስኤ የአቅርቦት ችግር ሆኖ እያለ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ግን አሁንም የችግሩ መንስኤ የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብታም ሆኖ የመግዛት ፍላጎቱ ስላደገ ነው ማለቱ ነው። ይባስ ብሎም አቶ መለስ ዘናዊ ባለፍው ዓመት (እ.ኤ.አ. 2008) መጨረሻ ላይ ሆን ተብሎ ተዘጋጅቶ ለፕሮፓጋንዳ በተሰራጨ ቪዲዮ አማካይነት መንግሥታቸው ለሚከተለው የኢኮኖሚ ዕቅድ እና ፍልስፍና ምስጋና ይግባውና የኢትዮጵያ ገበሬ ምርታማዊነቱ በየጊዜው እየጨመረ መጥቶ ዕድገቱ ኢትዮጵያ በአውሮፓ ታሪክ ታይቶ እንደነበረው “ኅዳሴ” (Renaissance) ጋር እንድትወዳደር አድርጓታል። ኅዳሴ ማለት “በአዲስ መልክ መወለድ” (“new birth”) ስለሆነም ኢትዮጵያ በአዲስነት እንደተወለደች ተድርጎ ስለሚቆጠር የኢትዮጵያ ህዝብ ደስ ሊለው እንደሚገባ አቶ መለስ ሳይሰለቻቸው አተቱ። ዕድገቱ የሚማርክ ከመሆኑም የተነሳ የገጠሩ አሠራርና ዕድገት በከተማ ለሚኖረው ኅብረተሰብ አስተማሪ እንደሚሆንም አሰመሩበት። የከተማው ህዝብም ከገጠሩ ኅብረተሰብ መማር እንዳለበት አስታወቁ። ይህም አልበቃ ብሎ አቶ መለስ እንዲህ አሉ፤ ኢትዮጵያ በአዲስ መልክ ከመወለዷ የተነሳ፤ በጣም ታዳጊ ከሆኑትና መለስተኛ ሀብታም ናቸው ከሚባሉት ሀገሮች ጋር በቅርቡ ትመደባለች!
ይህ የፕሮፓጋንዳ ቃለ ምልልስ በቪዲዮ መልክ የተሰራጨው ወደ 10.4 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን በረሃብ እየተገረፉ ባሉበት ወቅት ነበር። አቶ መለስ ይህን ቃለ-ምልልስ ከሰጡ ከአንድ ሁለት ወራት በኋላ መንግሥታቸው እነዚህ ወገኖቻችን በረሃብ አደጋ ላይ ሊወድቁ የተቃረቡ መሆናቸውን እያወቁ እንደነበርና ሆን ብሎ የፓርቲው ኮንግረስ እስኪገባደድ ድረስ የደበቀው መሆኑን የውጭ ሀገር ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶችኛ ሌሎችም ከመንግሥት ጋር ያልተያያዙ ድርጅቶች አመልክተዋል።
በርግጥ የአቶ መለስ መንግሥት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በሚመለከት ከእውነት የራቁ መግለጫዎችን እያጉተለተለ እንደሚያወጣ ሁሉም ተገንዝቦታል። ከዚያም አልፎ አንዳንድ ጊዜ ታዋቂ ኢኮኖሚስቶችንም (ለምሳሌ እንደነ Jeffrey Sachs, Joseph Stiglitz እና በቅርቡም Dani Rodrik)ን ወደ አዲስ አበባ እየጋበዙ በተዘዋዋሪ መልክ እራሳቸው በውሸት የቆለሉትን “የኢኮኖሚ ዕድገት” እንደ ገደል ማሚቶ እንዲያስተጋቡላቸው አድርገዋል። እንደነዚህ ያሉትን ታላላቅ የኢኮኖሚ ጠበብቶችን (ኢኮኖሚስቶችን)ም ሆነ የኢኮኖሚ “ዕርዳታ” የሚያደርጉትን ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ማታለልም ችለዋል።
“ኢኮኖሚው ተወዳዳሪ በማይገኝለት መልክ እያደገ” ብለው እየነገሩን መሆኑማ፤ ኢትዮጵያ ከዓለም ህዝቦችና ሀገሮች ጋር ስትወዳደር በሙስና ከ163 ሀገሮች መካከል 138ኛውን ይዛ እያለችና ሙስናው ከመጠንባቱ የተነሳ ወደ ማፍያ አይነት አሠራር እየተለወጠ ባለበት ሁኔታ፤ 37% የሚሆነው ህዝባችን በአሳቃቂ ድህነት ተወጥሮ እያለ፤ 81% የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በደንብ ተመግቦ የማያድር መሆኑና የቀን ገቢው ከሁለት የአሜሪካ ዶላር ያነሰ መሆኑ እየታወቀ፤ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረው የኢትዮጵያ ህዝብ በውጭ ሀገር የእህል ዕርዳታ እየተደገፈ እያለ፤ በበቂ መፀዳጃ ሊጠቀም የሚችለው የገጠር ህዝብ (84% የሚሆነው ህዝባችን) 7% ብቻ መሆኑ እየታወቀ፤ የሀገሪቱ ደኖች ድምጥማጣቸው ጠፍቶ መሬታችን በነፋስና በዝናብ ጎርፍ በአስፈሪ መልክ ተጠርጎ እየሄደ መሆኑንና ሀገሪቱ ወደ በረሃነት በሚያስፈራ መልክ እየተለወጠች መሆኗን ብዙ አማላካቾች መኖራቸውን ተገዘበን እያለ፤ በተፈጠረው የዓለምና የአካባቢው የአየር ጠባይ መለወጥ የተነሳ የውሃ እጥረት፤ ተዳጋጋሚ ድርቆች እየተፈጠሩና የአካባቢ ሁኔታ መበከል የተነሳ እነዚህ ችግሮች ሀገሪቱን በጥፋት ላይ ያስቀመጧት መሆኑ እየታወቀ፤ ሀገሪቱን የመሬት ጥበት ወጥሯት እያለ፤ በተባበሩት መንግሥታት የኅብረተሰባዊ ዕድገት (Human Development Index) ኢትዮጵያ ከ177 ሀገሮች የ170ኛውን ቦታ ይዛ እያለች … ነው። በነግራችን ላይ አንዳንድ ታዛቢዎች ከላይ የተጠቀሱትም ሆኑ ሌሎቹ ማወዳደሪያዎች ኢትዮጵያን ቸር በሆነ መልክ አስቀምጠዋታል ብለው ያምናሉ።
ይህ በዚህ ላይ እንዳለ፤ እስቲ ከዚህ በታች የሰፈሩትን ሁኔታዎች እንመልከትና በእውነትም የኢትዮጵያ ገበሬ ሀብታም ሆኖ ኢትዮጵያን ከ”ኅዳሴ” ላይ ያደረሳት መሆኑን ወይም አለመሆኑን እንገንዘብ።
ለጅማሯችን ያህል እስቲ የሀገሪቱን ዓመታዊ ገቢ ሀብት በ3 ከፋፍለን እንመለከት (የ2008 ዓ.ም. ግምት)፤
ሀ) እርሻና ከእርሻ ጋር በተገናኘ ምርት የሚገኘው 45.9%
ለ) የኢንዱስትሪው ክፍል 12.9%
ሐ) የፍጆታና መገልገያው (አገልግሎትን ሰጪ) ክፍል 41.2%
በነዚህ ክፍሎች የተሰለፈው የኅብረተሰብ የሥራ ድርሻ ደግሞ፤ 1) በየእርሻና ተዛማጁ ክፍል የተሰማራው የሠራተኛ ክፍል 80.2%፤ 2) በኢንዱስትሪው ክፍል የተሰማራው የሰው ኃይል 6.6%፤ 3) በአገልግሎትና መገልገያ ክፍል የተሰማራው የሰው ኃይል 13.2% (እ.ኤ.አ. 2005 ግምት)።
ከዚህ በላይ ያሉትን መረጃዎችና አኀዞች አስቀድሜ ለማስቀምጥ የፈለግሁት፤ በአንድ በኩል አሁን የወጣው የህዝብ ቆጠራ እንዳመለከተው፤ ወደ 83.8% የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በገጠር የሚኖር መሆኑን ለማስጨበጥና ቢያንስ 80% የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በግብርና ላይ የተሰማራ መሆኑን ለማሳየት፤ በአንፃሩ ደግሞ የእንዱስትሪውና የአገልግሎቱ ክፍሎች ተደምረው ወደ 19.8% የሚሆነውን የሰው ኃይል/አምራች ብቻ ያቀፉ መሆናቸውን ለማስገንዘብ ነው። በሌላው በኩል ደግሞ፤ አንባቢያን ሊረሱት የማይገባው ቁም ነገር የማንኛውም ሀገር ሀብትና ኢኮኖሚ ሊያድግ የሚችለው በሥራ ላይ በተሰለፈው የኅብረተሰብ ችሎታና አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ጉልበቱንና እውቀቱን ተጠቅሞ በተግባር ላይ ማዋል የሚችል ከሆነ ብቻ ነው። በተጨማሪም የግብርናው ክፍል 60% ለሚሆነው የውጭ ሀገር ሽያጭ (exports) ምንጭ የሆነ፤ እስከ 90% የሚሆነውን የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ የኢኮኖሚ ክፍል ነው። ከዚህም በላይ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የኢኮኖሚውን አማካይ ያደረገው በግብርናው ላይ ነው። እንግዲህ የግብርናው ክፍል በአንድ በኩል የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት መጠቀሚያ ከመሆኑም በላይ፤ ለኢንዱስትሪው ጥሬ ዕቃዎችን አቅራቢና አበርካች ይሆናል ማለት ነው።
የግብርናው ክፍል ለኢንዱስትሪው ባለማቋረጥ ጥሬ ዕቃዎችን በተሟላ ሁኔታ ሊያቀረብ ይችላል? ይህ የኢኮኖሚ ክፍል (84% የሚሆነውን የህዝብ ክፍል ያቀፈው) የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በየጊዜው እንዲያድግ ሊያደርጉ የሚያስችሉት ሁኔታዎች አሉን? እስቲ ችግሮቹን ከሞላ ጎደል በግርድፉ እንመልከታቸው።
1) የደኖች ተመንጥሮ መጥፋትና የመሬቱ መራቆት፤
በሀገሪቱ ውስጥ የነበሩት ዛፎችና ደኖች ተመንጥረው ተመናምነዋል። የዛፎችና የደኖች መመንጠር በሀገሪቱ ላይ በተዳጋሚ ለሚደርሱት ድርቆች ምክንያት ሆኗል። ኢትዮጵያ ደን-አልባ በመሆኗም የተነሳ በከፍተኛ የአየር/ነፋስና ጎርፍ መሬቷ እየተጠረገ መጥቷል። በዚህም የተነሳ ነው እንኳን ድርቅ ሊነካው ቀርቶ ደኑ ያስፈራራ የነበረው የሀገሪቱ ክፍል በድርቅና በረሃብ መጠቃቱ አሁን ግልጽ ሆኖ የሚታየን። ከማንኛውም የበለጠ ማስረጃ የሚሆነን ግን፤ ወደ ገጠር ገባ ብለን፤ የቱን ያህል የኢትዮጵያ መሬት ወደ በረሃነት እየተለወጠ መምጣቱን ስንገነዘብ ነው። ይህን ችግር የዓለም ኅብረተሰብ ሁሉ ያወቀው ከመሆኑ የተነሳ፤ አንዳንድ ድረ-ገጾች እንኳ (ለምሳሌ እንደነ C.I.A. World Fact Book) እንዲህ ይላሉ፦
Ethiopia’s poverty-stricken economy is based on agriculture, accounting for almost half of GDP, 60% of exports, and 80% of total employment. The agricultural sector suffers from frequent drought and poor cultivation practices. The country is faced with severe deforestation; overgrazing; soil erosion; desertification; water shortages in some areas from water-intensive farming and poor management.
በእውነቱ እነዚህን ችግሮች ለመገንዝብ ብዙ መሄድ አያስፈልግም። ምሳሌዎች ለመጥቀስ ያህል፤ በወሎ ክፍለ ሀገር ተወልዳችሁ ያደጋችሁ፤ ወደ ገጠር ወጣ ብላችሁ፤ የምንጮችን መድረቅ፤ የመሬቱን መቦርቦር፤ የዛፎችን መጥፋት በተጨባጭ ታያላችሁ። ብርዳም የነበረው ገራዶና ውሃውም ወደ ሞቃትነት ተለወጠው ወደ የስኳር አገዳ ማምረቻነት መለወጣቸውን ትገነዘባላችሁ። በደሴ ከተማ ያደጋችሁም፤ ደኑ ከመጥፋቱም አልፎ የቦርከና ውሃ መድረቁን (ከበፊቱ ሁኔታ ጋር ሲወዳደር)፤ የቦርከና ውሃ ይፈስበት የነበረው ቦታ በተጨናነቀ መልክ ወደ ከተማነት የተለወጠ ከመሆኑ አልፎ በአካባቢው የነበረው ጫካ ተመንጥሮ ያ የዝንጀሮ መስፈርያ የጅቦች መሸሸጊያ/መጮሂያ የነበረው ገደላዊ መሬት የሰው መስፈሪያ መሆኑን ትገነዘባላችሁ።
በቦረና-ሳይንት የነበሩት የሽፍታ መሸሸጊያ የነበሩት ደኖች ድምጥማጣቸው ከመጥፋቱም በላይ፤ ረግረግ የነበሩ ቦታዎች ደርቀው የህዝብ መስፈሪያ ሆነዋዋል። በደሴና በአዲአ አበባ ከተሞች ዞር ዞር ብላችሁ ስታዩ ደግሞ ለማገዶ የሚሆን እንጨት ከመጥፋቱ የተነሳ በጣሊያን ጊዜ ተተክለው የነበሩ የባህር ዛፎች ድራሻቸው ጠፍቶ ኅብረተሰቡ ሥሮቻቸውን ከመሬት እየቆፈረ ሲጠቀምና መሬቱን ለጎርፍ ሲያጋልጥ ታያላችሁ። እኔ ባልተጓዝኩባቸው ክፍለ ሀገሮች ተመሳሳይ ሁኔታዎች በሌሎች ክፍለ ሀገሮች ተከስተዋል ብዬ አምናለሁ። አንዳንድ ኢትዮጵያን ጎብኝተው የሚመለሱ ተመሳሳይ ድርጊቶችን ያዩ መሆናቸውንም ገልፀውልኛል።
2. የአካባቢው የአየር ሁኔታ/ጠባይ መለወጥና ይህንንም አባዜ ለመቋቋም ዝግጁ ያለመሆን፤
በመካከለኛው ምስራቅ ነዳጅ ለማውጣት የሚደረገው ቁፋሮ የአካባቢውን - በተለይም በከፍተኛ አቀማመጥ የምትገኘዋን የኢትዮጵያን የአየር ጠባይ የቀየረው መሆኑን አንዳንድ ሳንቲስቶች አመልከተዋል። ይህ የአየር ጠባይ መለወጥ ምናልባትም በኢትዮጵያ ላይ ፈጠን ባለ መልክ እየተመላለሰ ለመጣው ድርቅ አንዱ ምክንያት እንደሆነም የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ። በተጨማሪም የዓለም የአየር ሁኔታ መለወጥ (Global Warming) ኢትዮጵያን ለከባድና ተመላላሽ ድርቆች እንዲሁም በጎርፍ ለመጠረግ ዳርጓታል ይላሉ።
3. የህዝብ ብዛትና የመሬት መሸንሸን ችግሮች፤
በሀገሪቱ ውስጥ የህዝብ ብዛት በየጊዜው መጨመር - የገጠሩ መሬት ሊሸከመው ከሚችለው በላይ የህዝብ ቁጥር በአስፈሪ ሁኔታ እየጨመረ ነው። በዚህም የተነሳ የመሬት መሸንሸን ግድ ሆኗል። መሬት ከመሸንሸኑም የተነሳ መሬትን በዘመናዊ መልክ ማረስ አያስችልም። አልተቻለምም። ይህንንም በሚመለከት አንድ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ማኅበር ቀደም ሲል ባቀረበው ጥናቱ እንዳመለከተው አንድ ገበሬ ከነቤተሰቡ የሚያርሰው አማካኝ ማሳ 1.02 ሄክታር እንደሆነ፤ ወደ 37.6% የሚሆኑት ገበሬዎች አማካይ የማሳ ድርሻ 0.38 ሄክታር ብቻ መሆኑንና፤ ወደ 11% የሚሆኑት ገበሬዎች ደግሞ ማሳ የሌላቸው ናቸው ሲል ዘግቧል።
በዘመናዊ የእርሻ ቴኮኖሎጂ ተጠቅሞ የመገልገሉ ሁኔታ አሉታዊ ስለሆነ፤ የኢትዮጵያ ገበሬ የመረቃ ምርት አምርቶ በምርቱም ጠግቦ እንዲያድር ከተፈለገ፤ አዳዲስ የሚለሙ መሬቶች መኖር አለባቸው። በኢትዮጵያችን አዳዲስና ያልለሙ መሬቶች ግን ብዙም የሉም። የህዝብ ብዛት በበኩሉ የሚያስከትላቸው ሌሎች ተጨማሪ ጠንቆችም አሉ። ከነዚህም መካከል፤ከተሞች በተዛባ መልክ እንዲስፋፉ ያደርጋል። በርካታው የኅብረተሰቡ ክፍል ወጣትና ምርተ-ቢስ እንዲሆን ያደርጋል። የተማረውና እውቀት ያለው የኅብረተሰብ ክፍል እንዲጫጫ ያደርጋል። እንግዲህ፤ የኢትዮጵያ ገበሬ በዘመናዊ የእርሻ መሣሪያ አመርቂ በሆነ መልክ ማምረት ካልቻለ፤ መሬትን መለጠጥ ስለማይቻል፤ ያለው አንዱ ዋና አማራጭ የህዝብ ብዛትን መቀነስ ወይም ማገድ ነው።
የህዝብ ብዛቱን ከሚቀንሱት ጠቃሚ ፖሊሲዎች መካከል የመሬት ስሪትን መቀየር/ማስተካከል ነው። በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ግን የኢትዮጵያ የመሬት ስሪት የሚቀየረው እኔ ሞቼ ከተቀበርኩ በኋላ ነው ሲል ፎክሯል። እንዲህ አይነቱ ፉከራ ለፖለቲካ መጠቀሚያ ቢያገለግልም፤ የመሬት ስሪት የመለወጡን ጉዳይ ግን የተወሳሰበ እንዲሆን ያደርገዋል። ለመሆኑ የመሬት ጥበት ችግር አንዱና ዋናው መሆኑን የማያውቅ ማን አለ?
4. የለካፊ በሽታዎች መብዛትና የጤና ጥበቃ አገልግሎት በበቂ አለመኖር Low health service coverage and life expectancy aggravated by the prevalence of HIV/AIDS፤
በግብርናው ላይ የተሰማራው ኅብረተሰብ በቂ የሆነ የጤና ጥበቃ የማይደረግለት ከመሆኑም በላይ ከመቼውም በላይ የልዩ ልዩ ለካፊ በሽታዎች (ለምሳሌ የወባ፣ የሣንባ (ቲቢ)፣ የኤድስ እና የመሳሰሉት) ሰለባ እየሆነ መጥቷል። የወባ በሽታ ይታይባቸዋል መባሉ ቀርቶ ስማቸው በማይታወቅባቸው “ቀዝቃዛ ናቸው” በሚባሉት ስፍራዎች መታየቱ በጣም የሚያስፈራ ነው። ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ እንዲሉ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እንደ የወባና የኤድስ በሽታዎች ላይ ጦርነት እንደመክፈት ፈንታ፤ አላስፈለጊ የሆኑ ጦርነቶችን እየቀሰቀሰ ለትክክለኛው ጦርነት ሊውል የሚገባውን ሀገሪቱ ያሏታን ትንሽ አንጡራዎች አባክኗል/ያባክናል። ለምሳሌ ከኤርትራ ጋር የተደረገው ጦርነት ቢያንስ ሦስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላርን የሚያህል ገንዝብ አስጨርሷል።
5. የመሬት ስሪቱ ችግርና ገበሬው የመሬት ባለቤት ያለመሆን አባዜ - ገበሬው አሁንም ጭሰኛ መሆኑ፤
በተለይም ደግም በሥልጣን ላይ ያለው መግሥት የደርግ መንግሥት የመሰረተውን የመሬት ስሪት መሰረት በማደረግ ያሰፈረው የመሬት ስሪት/አያያዝ ባመጣው አባዜ የተነሳ፤ በሀገሪቱ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን የምርት ውጤት/የሰብል ምርት (ፕሮዳክቲቪቲ) እየቀነሰው እንጂ እየጨመረው አለመምጣቱን ስንመለከት፤ በአንድ በኩል መንግሥት ማረስ ለሚፈልግ ሁሉ መሬት እንደሚያድል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቃል ስለገባ፤ ይህ “ቃል ኪዳን” በገበሬው አዕምሮ ላይ የመሬት ችግር እንደሌለ ጫና ስላደረገበት ገበሬው ያለ-ጭንቀት (አባዜው ሳይገባው) እንዲወልድ / እንዲራባ / እንዲዋለድ ይገፋፋዋል። በሌላ በኩል ደግሞ መሬቱ የራሱ ስላልሆነ ገበሬው ለመሬቱ በጎርፍ መጠረግ ደንታ እንዳይኖረው ያደርገዋል/አድርጎታል። በዚህም የተነሳ ገበሬው መሬቱን በመንከባከብ እና የአካባቢ መበከልን በመከላከል በኩል ግድየለሽ እንዲሆን ገፋፍቶታል። በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ አፈር በጎርፍ እየተጠረገ የሱዳንንና የግብጽን በረሃ ከማዳበሩም በላይ ወደ ሜድትራኒያን ባህር ተጠርጎ መግባቱን ሳያሰልስ ቀጥሏል።
በ3ኛም በኩል ገበሬው ሊያርሰው የሚችለው የራሱ የሆነ መሬት፤ ማለትም “የኔ ነው፤ ማንም አይወስድብኝም፤ ልሸጠው፤ ልለውጠው፤ ለልጆቼ ላወርሰው፤ … ወ.ዘ.ተ. እችላለሁ” ብሎ የሚንከባከበው መሬት፤ በግል-ንብረትነት ደረጃ የራሱ የሆነ በወለድ-አግድ አስይዞ ሊበደርበትና ማምረቻ ነገሮችን የሚገዛበት (raise capital) መሬት ሊኖረው ሲገባ፤ የጉዳዩንም አስፈላጊነት የኢኮኖሚ ጠበብቶች ቢመክሩም ቅሉ ይህ ባለመሆኑ የተነሰ ሀብቱና ሊጨምር የሚገባው ሰብል ባክኖ ቀርቷል። መሬት የገበሬው ባለመሆኑ የተነሳም ገበሬው ሊኖረው የሚገባው አቢይ ንብረት (capital) ባክኖ ቀርቷል። መሬት የግል ባለመሆኑ የተነሳ፤ አርሶ አደሩ የሚያስፈልገውን ያህል በራሱ አነሳሽነት (የራሱ መሆኑን ዋስትናው ስላልተረጋገጠና መረጋጋት ስለሌለ) በምርትና በእንክብካቤ (ለምሳሌ ዛፍ በመትከል፤ ውሃና አፈርን በመከባከብ) በሙሉ ልቡ እንዳይሳተፍ አድርጎታል። “ማረስ ለሚፈልግ ሁሉ መሬት ይሰጠዋል” የሚለው የመንግሥት ፖሊሲም፤ ምንም እንኳ ለሁሉም ገበሬ በበቂ ሁኔታ ሊዳረስ የሚችል መሬት ባይኖርም፤ ገበሬው “አንድ ቀን በቂ መሬት ይደርሰኛል” በሚል አስተሳሰብ፤ የሚወልዳቸው ልጆቹን ከግብርና ሌላ ተግባር ላይ እንዳይሳተፉ፤ ወይም ወደ ከተማ/ወደ የኢንዱስትሪው የሥራ መስክ ፈልሰው እንዳይሄዱ ያግዳቸዋል።
የኢህአደግ መንግሥት የመሬት ፖሊሲን የፖለቲካው መሽከርከሪያ አድርጎ ዘላቂ ልማትን በተቀላጠፈ መልኩ ለማስገኘት ሳንካ እንደፈጠረ ባለሙያዎች ያስቀምጣሉ። ለምሳሌ አቶ ሠለሞን ጎሹ በሪፖርተር ጋዜጣ በቅርቡ እንዳቀረቡት፤
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አቶ ታፈሰ ኦሊቃ ‘Ethiopian Politics of Land-Tenure Policies under Three Rigimes፡ A carrot and stick Ruling Strategy’ በተሰኘው የጥናት ጽሑፋቸው ግብርናው የኢኮኖሚውን ዕድገት በማፋጠን በምግብ ራስን ለመቻል፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆን ለማድረግ፣ ለአዳጊ ኢንዱስትሪዎች ግብአትነት እንዲውል ለማድረግ መሬት ወሳኝ ቢሆንም መንግሥት ለፖለቲካ መጠቀሚያ ብቻ እያዋለው እንደሚገኝ ተችተዋል።
በዚሁ ጋዜጣዊ ዘገባም፤ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ያሰፈረው የመሬት ስሪት፤ ገበሬውን ወደ ከተማ ፍልሰት እንዲያቆም አላደረገውም፤ በምግብ ራሱን እንዲችል አልረዳውምል። በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት “ከኢህአዲግ መቃብር ላይ ካልሆነ በቀር የመሬት መሸጥ መለወጥ የሚታሰብ አይደለም” ቢልም ነገር ግን መሬት የተለየና ስም ተሰጥቶት እየተሸጠና እየተለወጠ እንደሚገኝም አቶ ገብሩ አስራት ለአቶ ሠለሞን ጎሹ ገልጸውለታል።
ፀሐፊው ቀጠለውም፤ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አባል አቶ አክሉ “የኢህአዲግ አብዮታዊ ዲሞክራሲና የሀብታም ገበሬዎች ጉዳይ ከምርታማነት፣ ከህዝብ ብዛት፣ አማራጭ ስትራቴጂ ካለመኖር፣ ከመስኖ ልማት ለመጠቀም ካለመፈለግ አንፃር ውጤታማ አለመሆኑንና ዛሬም ገበሬው በምግብ ራሱን እንዳልቻለ፣ ይልቁንም ተጠቃሚ የፓርቲው ካድሬ መሆኑን ይገልፃሉ። ዶ/ር መረራ ኢህአዲግ ገበሬውን በመሬት በማስፈራራት በግድ አባል እያደረገው መሆኑን አመልክተው፤ መሬትን የሀገሪቱን ፖለቲካ ወደ ንግድ ለመቀየር ዋነኛ መሣሪያ እያደረገው እንደሆነ አስረድተዋል። ገጠሩንና ግብርናን ማዕከል ያደረገው ስትራቴጂውም የሰው፤ የቁሳቁስና የቴክኖሎጂ ሀብትን ከከተማው ወደ ገጠር በማፍሰስ እየተገለፀ እንዳልሆነም ገልፀዋል። ገጠሩንና ከተማውን ለማመጣጠን እየተሠራ ያለውም ሥራ እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ ተናግረዋል።
አቶ ገብሩ በከተሞች አካባቢ ያለ ዋስትና ገበሬዎች በከፍተኛ ሁኔታ የተፈናቀሉ እንደሚገኙ ጠቁመው በመሬት አካባቢ የተሾሙ ባለሥልጣናት በከፍተኛ ደረጃ እየበለፀጉ እንደሚገኙም አስረድተዋል። የገበሬው ተጠቃሚነት በሕግ የተረጋገጠ ቢሆንም በተግባር የመሬት ደላላዎች እየተጠቀሙ እንደሚገኙ የገለፁት አቶ ገብሩ በሊዝ ለ50 ዓመት መሬት መከራየት ለመሬት ዋስትና ጥሩ ቢሆንም አስተማማኝ መንገድ መሆኑ አጠራጣሪ ነው ብለዋል።
6. የመሬት ማዳበሪያው ያመጣው ችግር፤
ምንም እንኳ የመሬት ማዳበሪያው በአንዳንድ ቦታዎች ምርት እንዲጨምር ቢያስችልም፤ በአንድ በኩል የኢህአዲግ ካድሬዎች ገበሬውን የመሬት ማዳበሪያ ሳይወድ በግድ ከአቅሙ በላይ እንዲገዛ/እንዲከፍል በማድረጋቸው፤ ገበሬው በየጊዜው ወደ ድህነት ማጥ እንዲገባ ሆኗል። በዚህም የተነሳ ገበሬው በተበዳሪነት ተጠምዝዞ ስለተያዘ፤ እንዳውም ባለዕዳነቱ አስጨንቆት ይገኛል። እነዚህ ተግባሮችና ሁኔታዎች የገበሬውን ጉልበትም ሆነ የማምረት ፍላጎቱን እየቀነሱት መጥተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ማዳበሪያ የለመደው መሬት የበለጠ ማዳበሪያ እንዲነሰነስለት ፈልጓል። አንዳንድ ጥናቶች እንዳመለከቱትም፤ በመሬቱ ላይ የተነሰነሰው ማዳበሪያ መጥፎና ለኢትዮጵያ መሬት የማይስማማ (ነገር ግን የኢህአዲግ ካድሬዎችን ካዝና ያደለበ - አቶ መለስም ያራ ተብሎ ከሚጠራው የኖርዌይ የማዳበሪያ አምራች ኩባንያ የ200,000 ዶላር “ጉቦ” ለመቀበል ወደ ኦስሎ (ኖርዌይ) በ2005 ዓ.ም. ሮጠው እንዲሄዱ ያደረገ) በመሆኑ፤ መሬቱን ከመበከሉም በላይ፤ በአንዳንድ ቦታዎች ምርቱን እንዲቀንስ አድርጎታል።
7. የገጠሩ ህዝብ የፖለቲካው ሰልባ መሆንና መብቱ አለመከበሩ፤
የገጠሩ ኅብረተሰብ ለኢህአዲግ የፖለቲካ መሣሪያ ሰለባ ስለሆነና በየጊዜውም ለጭቆና ሰለባ ከመሆኑም በላይ፤ በየጊዜው ስብሰባ እየተጠራ የገበሬው ጉልበት እንዲባክን ሆኗል። በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ኢ-ዲሞክራሲያዊ እስከሆነ ድረስ በመንግሥቱና በኅብረተሰቡ መካከል ፉክቻው ስለሚቀጥልም የመንግሥቱ ካድሬዎች ገበሬውን ማስቸገራቸውን ይቀጥሉበታል። የኢትዮጵያ ገበሬ በመንግሥት ካድሬዎች ሌት ተቀን ጭካኔ በተሞላበት መልክ ስለሚያሸብሩትም እየተሳቀቀ ነው ኑሮውን የሚገፋው። የአዕምሮ ነፃነቱን ያጣ የኅብረተሰብ ክፍል በአመርቂ ሁኔታ አምራች ሊሆን አይችልም። ምርት እንዲያድግ ከተፈለገ ገበሬውን ጠፍረው የያዙት የፖለቲካ ሥርዓቶች መወገድ አለባቸው ማለት ነው።
8. የኋላ ቀር የእርሻ አጠቃቀም ዘዴ፤
የኢትዮጵያ ገበሬ አሁንም የሚጠቀምበትን ኋላ ቀር የማምረቻ ዘዴ ምርትን እንዲጨምር አያግዝም። ምርቱ እንዲያድግ ከተፈለገ ገበሬው በዝናብ ከመተማመን ተላቆ በሰፊው ዘመናዊ ቴክኖሎግጂና በመስኖ ውሃ ተጠቅሞ ማምረት መቻል አለበት። በዘመናዊ የእርሻ መሣሪያ የሚታረሱ ሰፋፊ የመሬት እርሻዎች መኖርም አለባቸው። በሣይንስና በቴክኖሎጂ ያለተደገፈ የግብርና ሥራ ሊያድግና ምርታዊም ሊሆን አይችለም።
9. የሰፋፊ እርሻዎች ልማትና፤ የእርሻ ግብዓት አቅርቦቶች አለመኖር፤
የእርሻውን ምርት ለማሳደግ የሚያስችሉ የእርሻ ግብዓቶችና አቅርቦቶች አሁን ከሚደረገው በበለጠ ሊኖሩ ይገባል። የእርሻው ምርት ዕድገት በርካታ የሥራ መስኮች ሊፈጥር የሚችል እንዲሆንም መታቀድ አለበት። ይህ አሁን ገና በጅማሮ ላይ መሆኑ ቢታወቅም፤ አብዛኛውን ገበሬ ያሳትፍ እንደሆነ ገና አይታወቅም። የግብርናው ክፍል ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት እንዲሆን ከተፈለገ ሰፋፊ የእርሻ ልማቶች ተቋቁመው ባልተቋረጠ መልክ ለኢንዱስትሪው ጥሬ ዕቃዎችን ማቀበል አለባቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ሁኔታ እስካሁን አልተከሰተም። እንዳውም በቅርቡ የቡና ገበያን አስመልክቶ የታዩት ክስተቶች እንዳመለከቱት፤ መንግሥት ያቋቋመው የአቅርቦትና የንግድ ተቋም ችግሮቹ እንዲባባሱ አደርጓል።
10. በጥሩ መልክ አለመመገብና የምግብ እጥረት የተነሳ በረሃብ መጎዳት (ጠግቦ አለማደር)፤
ዛሬ የእያንዳንዱን የገበሬ ሰውነት ስናይ፤ በሚደርስበት የምግብ እጥረት የተነሳ (በርከት ያለውን ህዝባችንን ረሃብ እየቆላው ነው) ጤናውን ከማጣቱም በላይ፤ የማምረት ችሎታው እየቀነሰ እንጂ እየጨመረ አልመጣም። ሊመጣም አይችልም። የእርሻው ምርት እንዲያድግ ከተፈለገ ገበሬው በልቶ/ጠግቦ የሚያድርና ጤናማ መሆን አለበት። አሁን ወደ ገጠር ገባ ብለን የኢትዮጵያን ገበሬ የሰውነት ሁኔታ ስንመለከት በምግብ ማነስና የለካፊ በሽታዎች ሰለባ ከመሆኑ የተነሳ ገበሬው የቀጨጨና ጉልበት-አልባ መሆኑን እንገነዘባለን።
11. ሠላም መጥፋት/ማለቂያ በሌለው ጦርነት መጠመድ፤
በሀገሪቱ ውስጥ ሠላም ስለሌለ፤ በየክፍለ ሀገሩ፤ በየመንደሩ፤ መለስተኛም ሆኑ ከፍተኛ ግጭቶችና ብጥብጦች፤ ህዝቡን የኑሮና የአዕምሮ ሠላም እንዲያጣ ስላደረጉት፤ “ነገ ምን ላምርት፤ እንዴት ምርቴን ላሻሽል …” ብሎ ከማሰብ ሌላ “ነገስ ምን መከራና ጭቅጭቅ ይመጣብኝ ይሆን፤ የዛሬውን የመከራ ቀን እንዴት ላሳልፍ፤ ጠምደው የያዙኝን የመንግሥት ካድሬዎች እንዴት ልቋቋማቸው እችላለሁ? … ወ.ዘ.ተ.” በመሳሰሉት አሉታዊ ችግሮች ተወጥሮ የሚገኝ መሆኑን ስንመለከት፤ ይህም ችግር አምራችነቱን የቀነሰበት መሆኑን እንገነዘባለን።
12. በ”ነፃ” እና በዕርዳታ መልክ የሚታደለው የውጭ ሀገር እህል አባዜ፤
ሀገሪቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የእህል እጥረት እያጋጠማት ስለመጣ፤ የውጭ ሀገር እህል በነፃ እንዲታደል የግድ ሆኗል። ይህ በነፃ የሚታደለውም እህል፤ ድርቅ ባልመጣባቸው አካባቢዎች አምራች የሆኑትን ገበሬዎች በጣም ጎድቷል (በነፃ የሚታደለው እህል ምርታቸውን ዋጋ-ቢስ ስላደረገው)። ገበሬውም ተግቶ እንዳይሠራ፤ እንዲዘናጋና፤ ለማኝ የመሆን ዝንባሌንም ማምጣቱ አልቀረም።
13. ለሀብታም ሀገር ገበሬዎች የሚደረገው ድጎማ ያመጣው አባዜ፤
ለአሜሪካ፤ ለአውሮፓና ለጃፓን እንዲሁም ለደቡብ ኮሪያ ገበሬዎች የሚደረገው ድጎማ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ (ለምሳሌ ስዊዘርላንድ በምትባለው የአውሮፓ ሀገር ለአንድ እጅ የሰላጣ ችቦ ድጎማው እስከ 750% እንደሚሆን ከጥቂት ዓመታት በፊት “ዎል ስትሪት ጆርናል” በተባለው ጋዜጣ ተዘግቦ ነበር)፤ ድጎማ ማድረግ የማይችሉ ሀገሮችን ኢትዮጵያን ጨምሮ እየጎዳ መጥቷል። በዓለም የንግድ ድርጅት አባላት መካከል ለተነሳውም ጭቅጭቅ አንዱና ዋናው ይህ ደጎማ ነው!። ምናልባት አንዳንድ አንባብያን እንደ ኢትዮጵያ ያሉት ሀገሮችም ገበሬዎቻቸውን መደጎም አለባቸው ብለው ሊከራከሩ ይሞክሩ ይሆናል። ነገር ግን ይህ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም፤ ተግባራዊም አይሆንም። በአንድ በኩል፤ ሊደረገ የሚታሰበው ድጎማ የበለፀጉ ሀገሮች ለገበሬዎቻቸው ከሚያደርጉት ድጎማ ጋር ሲወዳደር በጣም ትንሽ ስለሚሆን (የድሃ ሀገሮች ኪስ/ካዝና የተራቆጠ ስለሆነ)፤ ድጎማ ማድረጉ ዋጋ-ቢስ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በበለፀጉት ሀገሮች ውስጥ በግብርናው ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው የሰው ኃይል በጣም ጥቂት ነው። ለምሳሌ በአሜሪካ ሀገር በግብርናው ላይ የተሰማራው የሰው ኃይል ከ2% አይበልጥም። በአንፃሩ ደግሞ ከ80% የማያንሰው የኢትዮጵያ የሰው/የሠራተኛ ኃይል በግብርናው ላይ የተሰማራ ስለሆነ፤ ማን ለማን ደጓሚ ይሆናል?
14. ገበሬው በዘመናዊው የመብራት ኃይልና ንፁህ ውሃ መጠቀም አለመቻሉና ገበሬው ተበታትኖ ስለሚኖር በበቂ መልክ ልማትን ለማካሄድ ያለው ችግር (Highly dispersed villages/population)፤
በዘመናዊ የመብራት ኃይል የሚጠቀመው የገጠር ህዝብ 2% ብቻ ነው። በገጠር የሚገኘው ኅብረተሰብ በየቦታው ተበታትኖ የሚኖር ስለሆነ እነዚህን ችግሮች መወጣት አልተቻለም፤ አይቻልምም። አንዱ መፍትሔ የመሬት ስሪትን መለወጥና ገበሬው እነዚህን ችግሮች አውቆ ዘመናዊና እንደ የኤሌክትሪክና የውሃ መገልገያዎችን፤ ዘመናዊ የመፀዳጃ ቦታዎችን ለመጠቀም የሚያስችሉ የመንደር/የከተማ አሰፋፈሮች ላይ ትብብር እንዲያደርግ ካልተደረገ ይህ ችግር ሊቀረፍ አይችልም።
ተበታትኖ መኖር የልማት ሥራዎችን ፋይዳ-ቢስ ያደርጋቸዋል። አንዳንድ ጥናቶች እንዳመለከቱትም የሳሳው የሠፈራ (የመንደር አመሠራረት) ከሰሃራ በረሃ በታች ለሚገኙት ሀገሮች የልማት ሥራን ለማቋቋም ብዙ እንደሚያስወጣቸው (ወድ እንደሚሆንባቸው) ነው። ይህም ችግር ተሰባስቦ በመኖር/በመሥራት ሊገኝ የሚቻለውን ጥቅም (benefit from economies of agglomeration) ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። አንዳንድ ጥናቶች እንዳመለከቱት ከሰሃራ በረሃ በታች ለሚገኙት ሀገሮች አንድ የልማት ሥራን ለማቋቋምና ተግባራዊ ለማድረግ በነፍስወከፍ እስከ 400 የአሜሪካ ዶላር የሚፈጅባቸው ሲሆን፤ በአንጻሩ ደግሞ በሌሎች ሀገሮች የነፍስወከፍ ወጪ የዚህን ግማሽ ብቻ ነው።
በእውነቱ በአንዲት ሀገር ውስጥ የልማት ውጥኖች/ዕቅዶች ተግባሮች ሲደረጉ በርከት ያሉ ነገሮች መመዘን አለባቸው። ከነዚህም መካከል፣ 1) የልማት ሥራ በአካባቢ ብከላ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ፤ 2) ጥቅሙና ጉዳቱ፤ 3) በተለይም የተዘረጋው የልማት ሥራ ለተጠቃሚው በአቅርቦት ሲቀርብ ተጠቃሚው ግልጋሎቱን ለመጠቀም ፍላጎት ያለው መሆኑንና ሊከፍል የሚችል መሆኑንን፤ 4) የተዘረጋውን ልማት ለመንከባከበ በየዓመቱ የሚያስወጣው ወጪ (operating and maintenance cost) … ወ.ዘ.ተ. ሊሸፍን መቻሉን ነው። በነገራችን ላይ በኢትዮጵያና በአንዳንድ አፍሪካ ሀገሮች እየተዘረጉ ያሉት የልማት ተቋሞች ከ1 እስከ 4 የተዘረዘሩትን ችግሮች ያልቀረፉ/የማይቀርፉ ስለሆኑ፤ ልማቶቹ እንደ ኪሳራ መቆጠር አለባቸው ብለው የሚያቀርቡ ብዙ አዋቂዎች አሉ።
የገጠሩ ህዝብ በከተማ መልክ እንዲኖር ማድረግ በርካታ ጥቅሞችን ያመጣል፤ ችግሮችንም እንዲቀረፉ ይረዳል። በአንድ በኩል የመሬት ጥብት የበለጠ እንዳያስቸግር ያግዛል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በከተማ ተከማችቶ የሚኖረው ህዝብም ትምህርት ቤቶችን፤ የመብራት ኃይል ማመንጫዎችን፤ የውሃ ጉድጓዶችን፤ የመፀዳጃ ቦታዎችን ተባብሮ እንዲሠራና በቀላሉና በቀነሰ ወጪ እንዲጠቅም ያስችሉታል። እስካሁን የተገኙት ተመክሮዎችና ጥናቶች እንዳመለከቱትም፤ በከተማ መልክ ህዝባቸውን እንዲሰባሰቡ ያደረጉ ሀገሮች የኢኮኖሚ ዕድገትንና የኑሮ መሻሻልን አስመዝግበዋል።
15. ለውጭ ሀገር ግለሰቦችና መሪዎች በመታደል ላይ ያለው ለም መሬታችን ወደፊት የሚያስከትለው ችግር፤
በአንድ በኩል መሬቱ ከጭሰኞች የሚነጠቅ ከሆነ ገበሬዎች እንዲፈናቀሉ ያድርጋል። ይህም ጉዳይ ግጭትን ሊያስከትል ይችላል። በሌላ በኩል መሬቱ በጭሰኞች ያልተያዘና ያልታረሰ ከሆነ፤ ለምለም መሬታችን በሀገር ከበርቴዎች ስር እንዳይሆን ከማድረጉም በላይ በሌሎች ሀገሮች እንደተከሰተው ሁሉ የውጭ ሀገር ከበርቴዎች ለሀገራችን የአካባቢ መበላሸት/መበከል ምክንያት ሊሆኑም ይችላሉ። ይህ ከሆነም በአንድ በኩል በውጭ ሀገር ከበርቴዎችና በሀገራችን ከበርቴዎች መካከል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በውጭ ሀገር ከበርቴዎችና በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ መካከል አለመስማማትንና ግጭትንም ሊፈጥር ይችላል። ሀገሪቱ ወደ ድህነት ባሽቆለቆለች ቁጥር ግጭቱ ሊስፋፋ እንደሚችልም መጠበቅ አለበት።
16. የሀገሪቱ ኅብረተሰብ በክልል/ጎሣ በመከፋፈሉ የተነሳ ሰፊ የሆነ ገበያና የህዝብ ብዛት ያለው ተጠቃሚ የሚያስፈልጋቸው የልማት ተግባራት በሥራ ላይ ሊውሉ አለመቻላቸው፤ The separation of regions via competing ethnicities makes it impossible to build a well-functioning business and infrastructure, such as internet servers, mobile phones, water wells, electricity power lines, fright, and airports, etc.
ለማጠቃለል ያህል፤
ማንም እንደሚያውቀው ለአንዲት ሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኙ ጤነኛ የሆነ፣ ጉልበት ያለው፣ አዕምሮው ነፃ የሆነ፣ የተማረ፣ ዘመናዊ መሣሪያን ተጠቃሚ የሆነ የሰው ኃይል እንደመሆኑ መጠን፤ በተጨማሪም የማምረት ችሎታውንና ፍልጎቱንም ሊያሳድጉ የሚችሉ ፖሊሲዎች አስፈላጊ ናቸው። ነገር ግን ይህ ወደ 84% የሚሆነው ህዝባችን በሚሰቀጥጥ መልክ በአግባቡ ካለመመገብ፣ የአስከፊ በሽታዎች ሰለባ በመሆን፣ በምግብ እጥረትና በረሃብ እየተገረፈና እየረገፈ ባለበት ሁኔታ ዕድገት ይመጣል ብሎ ማሰብ ቅዠት ነው። የህዝብ ብዛት (ያውም አምራችነት የሚያንሰው ወጣትና ልጅ የሆነ ህዝብ) የሚያስከትለውን (ያስከተለውን) አባዜም አንርሳ። ዕድገት አለ ብሎ መናገር ደግሞ በብዙ ሚሊዮን ህዝብ ሕይወት ላይ መቀለድ ነው። “ኢኮኖሚው ተወዳዳሪ በማይገኝለት መልክ እያደገ ነው፤ ገበሬው ሀብታም በመሆኑ የመግዛት ፍላጎቱ ጨምሯል …” ተብሎ ውሸት ቢቆለል የሚያመጣው ፋይዳ የለም! በአንዲት ሀገር ውስጥ የሚኖረው የሰው ኃይል ጉልበቱንና እውቀቱን በንቃትና በነፃነት በመጠቀም ብቻ እንጂ የአንዲት ሀገር ሀብትና ኢኮኖሚ ሊያድግ የሚችለው ስለተዋሸለት አይደለም።
በነገራችን ላይ በቅርቡ የወጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ መግለጫ እንዲህ አለ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በየዓመቱ ወደ 3% ስለሚያድግ፤ መንግሥት ከሚገልፀው የኢኮኖሚ ዓመታዊ ጭማሮ ላይ ዕድገቱን እውነታዊ ለማድረግ ይህንኑ 3% ቀንሱበት ይላል፤ ጥሩ ጅማሮ ነው! ነገር ግን ግሽበቱ በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ያለውን አሉታዊ ሁኔታ መቼ ይሆን ይቀነስ (ይስተካከል) የሚሉን?
በእውነቱ ከላይ ባጭሩ የተዘረዘሩት ችግሮች አንዳዶቹ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የፈጠራቸውም አይደሉም። እንዳውም አንዱ መንግሥት ሄዶ ሌላው ሲተካ የሚኖሩ ዘላቂ ችግሮች ናቸው። አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ከሌሎቹ የሚለየው እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ችሎታው ያነሰ (የሌለው) መሆኑና በተግባር ሲታይ ችግሮቹን ለመቅረፍ ፍላጎትም የሌለው መሆኑ ነው። ችግሮቹ 84% የሚሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ወጥረውት እያሉ ችግሮቹን የሚሸፋፍን መሆኑ በተደጋጋሚ ታይቷል።
ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች የሚያስከትሏቸው አሉታዊ ችግሮች በጋራ፤ በድምርና በሂደት አብረው እንጂ በተናጠል መታየት የለባቸውም። በእውነቱ ችግሮቹን በድምርና በሂደት መልክ ስንመለከታቸው፤ አንዳንድ ጥያቄዎች በአዕምሮችን ላይ መንሳፈፋቸው አይቀርም። ለምሳሌ “ይህችን ሀገር ድሮ ወደ ነበረችበት ሁኔታ ለመመለስ ቀርቶ (ድሮ የነበረችበት ሁኔታ የሚናፍቅና የሚማርክ ከሆነ)፤ አሁን ባለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ እንኳ ትቆያለችን?” የሚለው ጥያቄ ይመጣብናል/ሊመጣብን ይገባል። አስበን ስናሰላስልም መፍትሔው ይጠፋብናል፤ እንዳውም ጨልሞብን በጣም ይጨንቀናል።
የኢትዮጵያም ህዝቦች ስለጨነቃቸውውም ነው የተወለዱባትን፤ እትብታቸው የተቀበረችባትን፤ ወገኖቻቸውን - ቤተሰቦቻቸውን - ፍቅረኞቻቸውን …፤ ውድ ሀገራችውን እየለቀቁ እየተሰደዱ ያሉት። ከዚህ የበለጠ መረጃ ምን ይኖራል? በእውነቱ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንደዚሁ ከቀጠሉ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ መናወጥ የተነሳ እንድትበታተንም ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ! መረሳት የሌለበት ነገር ደግሞ፤ በአኳያው በሌላው ዓለም የሚገኙ ኅብረተሰቦችና ሀገሮች በሰው ልጅ እውቀት የተደገፈ ኢኮኖሚን (knowledge economy) ተጠቅመው እየገሰገሱ ስለሆነ ሀገራችን አሁን ባለችበት ሁኔታ ብትቆይ እንኳ ወይም የኢኮኖሚ ዕድገቷ ከተወዳዳሪዎቿና ከዓለም ኅብረተሰብ ጋር የማይመጣጠን ከሆነ፤ ተፎካካሪዎቿ ጥለዋት ሲያልፉ፤ ኢትዮጵያና ኅብረተሰቦቿ ወደኋላ ይቀራሉ። ሀገሪቱም የተማሩና የማምረት አቅም ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎቿንም ለቀደሟት ሀገሮች አስረካቢ እንደሆነች ትቀራለች። አዕምሮዋ እየደማ ይቆያል። እንዳውም የሀገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታዎች (ፖሊሲዎች) አሁን ባሉበት አካሄድ ከቀጠሉ፤ የበለጠ ህዝባዊ ሰቆቃ (human suffering)፤ የበለጠ የኢኮኖሚና የኅብረተሰብ እንዲሁም የፖለቲካ ችግሮች ቀስ በቀስ ሊከስቱ ይችላሉ። ያለመረጋጋትና የመፈናቀል/የመፍለስ ችግሮቻችን እየበዙ መጥተውም ለጎረቤት ሀገሮችና ለመላው ዓለምም የሚደርሱ እንደሚሆኑ ሊታየንም ይገባል።
እኔ እንደሚታየኝ ከሆነ የመሬት ስሪቱና በግብርናው ላይ የተሰማራው ኅብረተሰባችን ችግሮች በቀላሉ የሚቀረፉ አይደሉም። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም “ገበሬው ጠግቧል፤ ነፃ ስለሆነ ለምርቱ የፈልገውን ዋጋ መጠየቅ ችሏል፣ ... ወ.ዘ.ተ.” ብሎ ከመዋሸቱም በላይ የመሬት ስሪቱን ለመለወጥ እንዳይመችና የተወሳሰቡ እያደርጋቸው ስለሆነ ብዙ ልንጠብቅም አይገባንም ይሆናል። ነገር ግን ለኢትዮጵያና ለህዝባችን የተሻሉ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ የምንፈልግ ሁሉ ችግሮቹን ለመቅረፍ እንድንችል ካሁኑ በጥናት መልክ (አዋቂዎችን ባሳተፈ መልክ) ለማየት መጀመር አለብን።
ማስታወሻ፦ የዚህ ጽሑፍ ተከታዮች የኢንዱስትሪውንና የአገልግሎቱን የኢኮኖሚ ችግሮች ከተነተኑ በኋላ፤ በመጨረሻም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወጥረው የያዙት ችግሮች ያቀርባሉ።
እስከዚያው ቸር ይግጠመን!
ዋቢዎች፤
1. ይህ ፀሀፊ በተልያዩ ጊዜ ያወጧቸው ጽሑፎች
2. የተለያዩ የሪፖርተር ጋዜጣ እትሞች
3. የዚህ ጽሑፍ ተከታይ በሆኑት መጣጥፎች የሰፈሩት መረጃዎች
4. http://siteresources.worldbank.org/INTAFRICA/Resources/AICD_exec_summ_9-30-08a.pdf
ፕሮፌሠር ሰይድ ሐሰን፤ መሪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )



