ስንት ዘመን “መፈንቅለ መንግሥት”፣ “ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ሊናድ …”፣ “ልንገደል ነበር” እያሉ ቴያትር ይስሩብን?

ልዑልሰገድ (ከአቢሲኒያ)  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

በሥልጣን ላይ ያለው የአቶ መለስ ቡድን በየጊዜው ንጹሃንን ለመግደል ለማሰቃየትና ለማስር የመሰለውን ወንጀል ይፈጥራል። አንዳንዴ ቴአትሩ መልኩን ለወጥ አደረገ ሲባል ሌላ ጊዜ እንዲህ እንደሰሞኑ የተለመደና አስቂኝ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች ሞልተዋል።

 

የሥርዓቱ መሪዎች በሥልጣን ዘመናቸው ገጥሟቸው የማያውቅ ዱብ ዕዳ ደርሶባቸዋል። የፈለጉትን ገለው፣ የቻሉትን ዘርፈው፣ የጠሉትን ሁሉ አስረውና አዋርደው አመሻሽ ላይ እብስ ለማለት የማያስችላቸውን መርዶ ሰምተዋል። መርዶው በፈጸሙት የዘር ማጥፋት ወንጀል የመጠየቃቸው አይቀሬነት ፈጦ መውጣት ነው። የዚህን ዜና ተከትሎ ለንደን ላይ በአቶ መለስ ላይ የደረሰበት ጠንካራ የወገኖቻችን ተቃውሞ አዲስ አበባ ላይ የሰሞኑን ቴያትር አስፈጠረ።

 

የወያኔው ቴያትር በመፈንቅለ መንግሥት ተጀምሮ ማግስቱን ያልታወቁ ባለሥልጣናትን መግደል እና ሽብር ተብሏል። ምን አልባት በቴአትሩ ቀጣይ ክፍል ሌላ ፈጠራ ታክሎ ይጠብቀን ይሆናል።

 

ኢትዮጵያውያን ከዓመት ዓመት በወያኔ የባርነት ቀንበር ተይዘን በጭሰኝነት። በገዛ ሀገራችን ውርደት እየቆጠርን ጥቂቶችን መስዋዕት እያደረግን መቀጠልን ይብቃ ማለት አለብን። በጨካኝና ጨቋኝ ገዥዎቻችን የሚሞቱና የሚታሰሩ ወገኖችን ስም በመዘከር የትም አንደርስም። ለጨቋኞች ዕድሜ መስጠት ተጨማሪ ውርደትና ውድቀት ካልሆነ የተሻለ ነገር አልመጣም።

 

ዛሬ ባለው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በሥልጣን ላይ ያለው የእነ መለስ ቡድን ህዝቡን አንዴ በኃይማኖት፣ ሌላ ጊዜ በዘር አፋጅቶ በአንድ ጠባብ ቡድን የበላይነት በሥልጣን ለመቆየት የቆረጠ ነው። ምርጫ በሌለበት ምርጫ፣ ፍትህ ሳይኖር ስለፍርድ ቤት፣ ነፃ ተቋማት በጠፋበት ስለ ሕግ የበላይነት ማውጋት ከንቱ ነው።

 

በሀገራችን ላይ የነገሠው ገዢ ቡድን በምንም መንገድ ሥልጣኑን ላለማጣት የቻለውን ሁሉ ለመግደል፣ ለማሰርና ለመርገጥ ቆርጦ ተነስቷል። ብዙኀኑ ህዝብ ይሄን ሐቅ ተረድቷል። ጥያቄው መከራችን በጊዜ አብቅቶ እውን እኛም እንደ ሰብዓዊ ፍጡር በሀገራችን የዜግነት መብታችን ተከብሮ በነፃነት ለመኖር የሚያስችለንን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በአንድ መቆም አቃተን የሚል ነው።

 

ለዚህ አብይ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተን የጋራ ግባችን የሆነውን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን መገንባቱን ዕውን ለማድረግ ካልጣርን የወያኔ ግድያ፣ እስራትና የፈጠራ ክስ የተለመደ ቴያትር ሊያስገርመን አይገባም። ይልቅ የሚያስቆጨንና የሚያስጠይቀን እንዴት የምንጠላውን የንጹሃንን ሞት፣ እስራት፣ በአጠቃላይ የሀገርና የወገን ውርደት ተባብረን ማስቀረት አቃተን? ብለን ምላሽ ካጣን ነው።

 

ዛሬ ከሀገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን ያገኘውን የወያኔ ቡድን ዘር ጨፍጫፊነት፣ የሀገር ሀብት ዘራፊነት፣ ደጋግመን ብናነሳ ችግሩን አናቆመውም። መፍትሔ የሚሆነው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ እያንዳንዳችን የበኩላችንን አስተዋጽዖ ማድረግ ስንችልና በእውነት ለሀገራችንና ለወገናችን ተቆርቋሪ ሆነን ስንገኝ ነው።

 

ለኢትዮጵያ ከገዳዮቻችን ጋር ከአበሩትና በክህደት ከተሰለፉት በስተቀር ሁሉም እውነተኛ የህዝብ ለውጥ ፈላጊ ተቋዋሚዎች ያስፈልጉናል። የጋራ ግባችን በሀገር ወገን ላይ የወደቀውን ጨቋኝ ሥርዓት አስወግደን በጋራ በህዝብ ይሁንታ የሚመሰረት አዲስ መንግሥት ለማቆም እስከሆነ ድረስ የጠብ ወይም ያለመግባባት መሰረት የለንም።

 

በእነ አቶ መለስ የሚመራው ቡድን እኛን ቆሞ እየጠበቀ አይደለም። በዘረኝነት ጅራፍ እየገረፈ፣ ሀገሪቱን እየዘረፈ፣ የቻለውን እየገደለና እያሰረ በተባበረ ክንድ እስኪወድቅ ይቀጥላል። በንጹሃን ላይ ወንጀል እየለጠፈ በዜጎች ደም እየታጠበ ከበደኖ፣ ከአርባ ጉጉና ከወተር ግፍ ወደ ጎንደር አደባባይ እየሱስ ጭፍጨፋ፣ ከደቡብ እስከ ጋምቤላ ግድያ ከ1985 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሠላማዊ ሰልፍ ብተና እስከ ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓ.ም. ጅምላ ጭፍጨፋ ሳይበቃ ከዚያም በኋላ ቀጥሏል። በስም እገሌ ብለን ካልጠራናቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ እስረኞች አንስተን በስም ፕሮፌሠር አስራት ብለን እስከ ብርቱካንና ቴዲ ደርሰናል። ከህፃናት እስከ አዛውንቶች ሬሳ ቆጥረናል። የደርግ አልበቃ ብሎን ከምርጫ 97 በኋላ ለተገደሉት ንጹሃን የተገደሉበትን ጥይት እስከመክፈል ሄደናል።

 

የወያኔን የግፍ ድርጊት ብንዘረዝረው ዋጋ የለውም። በእኛ ቀርቶ በዓለም መድረክ ዕውቅና አግኝቷል። ችግሩ ያለው እንዴት እነዚህን ነብሰ በላዎች ተባብረን አደብ ማስገዛት አቃተን የሚለውን መመለሱ ላይ ነው።

 

የፖለቲካ ሽኩቻና እንካ ሰላንቲያ አቁመን ትግሉን መደገፍ ይገባናል። ውርደት እንዲበቃን በጋራ መነሳት አለብን። ለእኛ ነፃነት የሚታረድ የመስዋዕት በግ መጠበቅ የለብንም። እያንዳንዳችን ለነፃነታችን አርበኛ ለመሆን መቁረጥና ለዚህም በየተሰለፍንበት አቅጣጫ ሁሉ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ በጋራ መቆም ግድ ይላል። ይሄ ሲሆን የገዠዎቻችንን በንፁሃን ሕይወት ላይ እየተጫወቱ የሚሠሩትን የፓለቲካ ቴያትር ማስቆም እና በደም የታጠበ እጃቸውን ለሕግ ፊት ማቅረብ እንችላለን። መከራችንን ለማሳጠር ሁላችንም በወያኔ ቴያትር አንጀታችንን ከማቃጠል በአንድነት በመቆም ጥቂቶች የሚፈነጩበት የወያኔ አይነት የዘረኝነት፣ የአፈና ሥርዓት ሳይሆን በድምፃችን የምንመሰርተው የሕግ የበላይነት የሚያከብር፣ ለሕግ የሚገዛ፣ ዜጎች ሁሉ በእኩልነት የሚስተናገዱበት፣ ነፃ ተቋማት የተመሰረቱበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማቆም እየጣሩ ያሉትን ማገዝ የበለጠ ማጠናከርና መከራችንን ማሳጠር የሁላችንም አደራ ነው።

 

አሰልችው ነገር የእነ አቶ መለስ ቡድን ዓይኑን በጨው አጥቦ ስንት ዘመን “ልንገደል ነበር”፣ “ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ”፣ “ሽብርተኝነት”፣ … የሚሉ ቴአትሮች ይሠራብናል። በገዳይነት፣ ሕገ-መንግሥት በመናድና፣ በአሸብሮ በመፈንቅለ መንግሥት የህዝብ ድምፅ ሰርቆ ሥልጣን ይዟል። በዘር ማጥፋት፣ በሀገር ሀብት ዝርፊያ ፍርድ ቤት ልናቆማቸው ሲገባን በተገላቢጦሽ እየተሳለቁብን፣ ጩኸታችንን ተቀምተን እየተቀለደብን ነው። ይሄን ብሔራዊ ውርደት ማስቀረት በየትኛውም መመዘኛ ፍትሐዊነት ነው።

 

ይሔን ማድረግ ካልቻልን ወያኔን በመራገም ብቻ ከነብስ ገዳይነት፣ ከሀገር አፍራሽነት፣ ልናቆመው አንችልም። ያን በማድረግ የምናገኘው ትርፍ ተጨማሪ የንጹሃን ሬሳ መቁጠር፣ የእስረኞች ቁጥር ማሻቀብ፣ ስር የሰደደ ባርነትና የሀገር ውድመት ነው። የሚሻለን ለህልውናችን ስንል በጋራ መቆም እንጂ በወያኔ የፈጠራ ወንጀል ቴያትር በየምዕራፉ መገረም አይደለም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ