ኤርትራውያን መንገድ ከሚመታቸው አቶ መለስ ለምን ወደ ኤርትራ አይሔዱም? (ልዑልሰገድ)
ልዑልሰገድ (ከአቢሲኒያ) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
አዲስ አበባ ስታዲየም በተመልካች ግጥም ብሏል። ታዳሚው ገና ኳስ ጨዋታው ሳይጀመር ከየአቅጣጫው ድጋፉን ይገልጻል። በአቶ መለስ ጥብቅ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ወታደሮች ከወትሮው በቁጥር ጨምረዋል። በጊዜው ጨዋታው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ከእናት ሀገሯ በተገነጠለችው ኤርትራ ቡድን መካከል የሚደረግ የወዳጅነት ነበር።
በአቶ መለስ ተደጋጋሚ ዲስኩር “ጨርቅ” የተባለችው የሀገራችን ባንዲራ በበርካታ ደጋፊዎች ዘንድ ትውለበለባለች። በዘፈን፣ በጭፈራ፣ በጭብጨባ ብሔራዊ ቡድን መደገፉ ደራ። ጨዋታው እንደተጠናቀቀ በህዝቡ የሀገሩን ቡድን መደገፍ የተናደዱት እና አስቀድመው ለትንኮሳ ወታደሮች ያዘጋጁት ተልዕኳቸውን ጀመሩ። ከተመልካቹ መሃከል ‘ሀገሩን ደገፈ’ እና ‘ብሔራዊ ባንዲራውን አውለበለበ’ ያሉትን ከመሀሉ እየመነጠሩ ወደአዘጋጁት የጭነት መኪና በቆመጥ እየደበደቡና እየገፈተሩ በተሰጣቸው መመሪያ ንዴታደውን ይወጡ ገቡ። በርካታ ተመልካቾች ከስታዲየም በዚህ መሰሉ ሁኔታ ተግዘው ኮልፌ ፖሊስ ማሠልጠኛ ተወሰዱ። በዚያም ተጨማሪ ድብደባ አሰቃቂ ግፍ እየተፈጸመባቸው ብዙዎች እየፈረሙ ተለቀቁ። በዕለቱ ስታዲየም ብሔራዊ ቡድኑን ሲደግፉ ከነበሩትና ያ ግፍ ከተፈጸመባቸው መካከል አንዱ አርቲስት ታማኝ በየነ እንደነበረ አይዘነጋኝም።
ያንን ከዓመታት በፊት የተፈጸመ አሰቃቂ ትዕይንት ተመልሼ እንዳስብ ያደረገኝ የሰሞኑ የእነ መለስ “ኤርትራዊያን ኑልን!” አዋጅ ከሰማሁ በኋላ ነው። በእነዚህ የወያኔ መሪዎች የተፈጸሙ በመግቢያዬ የጠቃቀስኩትንና ዝቅ ብዬ የማነሳቸውን እውነቶች ለተመለከተ ዕውን ያ ድርጊት የተፈጸመው “ኢትዮጵያን እንመራለን” በሚሉ ሰዎች ነውን? ብሎ መጠየቁ አይቀርም። ሐቁ ግን በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ለኤርትራ እና ለኤርትራውያን ሲል ታላላቅ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች አሳልፎ የሰጠ እና ወደፊትም ለመስጠት ራሱን ያዘጋጀ መሆኑ ነው።
እናም ኤርትራውያን እንዲመለሱ፣ የተወረሰ ንብረታቸው እንደሚመለስላቸው፣ በኢትዮጵያ እንደሀገሪቱ ዜጎች መታየት መብታቸው መሆኑን በአዲሱ አዋጅ አስነግረዋል። የኝህ ከሃዲ መሪ ከሜዳ ተጀምሮ የመጣ የኤርትራ ተቆርቋሪነት ላይ የአዲሱ አዋጅ ጥሪ ላያስገርም ይችላል። የሚገርመውና የሚደንቀው ይልቅ ምን ቢተማመኑ ነው በአሁኑ ወቅት ይህን የመሰለውን ዓይን ያወጣ አዋጅ እስከማውጣት የደረሱት? የሚለው ነው። ለዚህ መሰረታዊ ጥያቄ ምላሽ ከመሰንዘሬ በፊት ተጨማሪ ማጣቀሻዎችን ከትውስታ ማኅደራችን ላውጣ።
ኤርትራ ከእናት ሀገሯ የተለየችው በኤርትራ ህዝብ ነፃ ምርጫ ውሳኔ አለመሆኑ ተደጋግሞ ተብሏል። በሻዕቢያና በወያኔ መመሳጠር ህዝቡን በአጣብቂኝ ምርጫ በማሳጣት “ነፃነት ወይም ባርነት” ብለው እንደፈለጉት ገነጠሉ።
የአቶ መለስ አስተዳደር ገና የሽግግር መንግሥት እያለ ከህዝቡ ባልተሰጠው ውክልና ለመንግሥታቱ ደርጅት የኤርትራን ሀገርነት ማወቁን አረጋገጠ። ከዚያ ውሳኔ በፊት በደርግ መውደቂያ ዋዜማ ለንደን ላይ በተደረገ ድርድር የአሜሪካው ዲፕሎማት ኸርማን ኮኽን ሳይቀር ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል ሲሉ እነ አቶ መለስ አሻፈረኝ ብለው ሁሉን ለኤርትራ አፀደቁ።
በ1985 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የጊዜው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ግብፃዊው ዶ/ር ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊን ኢትዮጵያ መምጣት ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ። ሰልፉ ገና ከዩኒቨርስቲ መነቃነቅ ሲጀምር የአቶ መለስ ወታደሮች ተማሪውን በቆመጥና በጥይት ያራውጡት ገቡ። “ብሔራዊ ጥቅማችን ይከበር!”፣ “ተው ስማኝ ሀገሬ!”፣ … ያሉት ተማሪዎች በፋሽስቱ ጣሊያን የወደቁ ወገኖቻቸው ሐውልት አጠገብ በአዲሶቹ ፋሽስቶች በጥይትና በቆመጥ ተራወጡ። አንድ ተማሪ ሞተ።
ማምሻውን እነ አቶ መለስና በረከት ዛሬም ድረስ የሚጨፍሩበት መገናኛ ብዙኀን የተገደለውን ተማሪ “ኢሠፓ” መሆኑን ተናገሩ። የመግለጫው መልዕክት ‘ኢሠፓ ይገደላል’ ለማለት ይሁን ሌላ ባይገባም፤ ህዝቡ ግን “የወያኔ ጥይት የተማረች ነች ስትተኮስ ነጥላ ኢሠፓውን ተማሪ መታች” ሲል በውሸታቸው ላይ አሾፈበት።
እነ መለስ የኤርትራን ጉዳይ የሚያነሳ “ጦርነት ናፋቂ”፣ “ፀረ-ሠላም” የሚል ስም እየሰጡ፣ የቻሉትን እያሰሩ፣ እየገደሉ እና የራቀውን በነገር እያስፈራሩ ለማፈን ሞከሩ።
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የኤርትራ ጉዳይ በአግባቡ መያዝ አለበት እንጂ፤ ኤርትራውያን ከወንድሞቻቸው ኢትዮጵያውያን ጋር ዘላለም ተቆራርጠው ይቅሩ የሚል ሃሳብ የለውም። በጣሊያን ለጊዜው የተገነጠለችውን ኤርትራን ወደእናት ሀገሯ ለመቀላቀል “እናት ሀገር ወይም ሞት” ብለው በአርበኝነት ታግለው ከወገናቸው የተቀላቀሉ ጀግኖችን ታሪክ አይረሳቸውም። በዚህም ዘመን ቢሆን ጥቂቶች የሻዕቢያ እና የወያኔን ሴራ ስላልደገፉ እና ሪፈረንደም ስላልመረጡ እንደከሃዲ ተቆጥረው አንገት እንዲደፉ ተደርገዋል። የህዝቡ አንድነት ትናንትም፣ ዛሬም፣ ምናልባትም ወደፊት ይኖራል። ቁም ነገሩ ኢትዮጵያና ኤርትራ በዓለም አቀፉ መድረክ እንደ ሁለት ሀገር ከሆኑ በኋላ የሁለቱ ሀገሮች ጉዳይ እንዴት መያዝ አለበት? የሚል ነው። ሐቁ በሥልጣን ላይ ያለው አመራር የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች አሳልፎ ለኤርትራ የሚሰጥ መሆኑ ነው።
የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በርካታ የሻዕቢያ አባላት ከታላላቅ መንግሥታዊ ሥልጣን እስከ የበታች ሹማምንት ነበሩ። ዛሬ ለወያኔ አባላት ሁሉም ነገር ቅድሚያ ይሰጥ እንደሚባለው፤ ከጦርነቱ በፊት የመጀመሪያው ቅድሚያ ለሻዕቢያ፤ የተረፈው ለወያኔ ነበር። ብዙዎቹ የወያኔ ቱባ ባለሥልጣናት ጭምር በዚህ ውስጥ ውስጡን ይንተከተኩ ስለነበር ለህወሓት አመራር መከፋፈል ጉልህ አጀንዳ የሆነውም የአቶ መለስ ብሔራዊ ጥቅምን አሳልፎ ለመሸጥ መነሳት ነው።
ከኢትዮ-ኤርትራ ይፋ ጦርነት መጀመር በፊት አቶ መለስና ኢሳያስ በሚስጥር ደብዳቤ መለዋወጣቸውን ከጦርነቱ በኋላ ይፋ ሆኗል። አቶ ኢሳያስ በይፋ የበተኑት የሁለቱ “ሸሪኮች” የሚስጥር ደብዳቤ ይዘት በድንበር አካባቢ እያየለ የመጣ ውጥረት መኖሩን፣ አቶ መለስ ችግሩን አስታግሳለሁ ማለታቸው፣ የችግሩ ፈጣሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል መግባቱን ይጠቃቅሳል። ይሄን ምስጥር አቶ መለስ ለህወሓት ከፍተኛ አመራር ጭምር ሳያካፍሉ ደብቀው የያዙት ነበር። በጦርነቱ ሰሞን “ኤርትራ ወረራ መፈጸሟ አስደንግጦኛል” ብለው እንደአዲስ ሊያደናግሩን መሞከራቸው ሰውዬው ዓይን ያወጡ ከሀዲ መሆናቸውን ያጋለጠ ነበር።
ከጦርነቱ መጀመር ጥቂት ቀደም ብሎ ኤርትራ ናቅፋን ለሀገርዋ መገበያያ ይዛ ብቅ አለች። በዚህ ሳትወሰን ከአዲስ አበባ አስመራ ድረስ ለሔዱት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አንድ ናቅፋ አንድ ብር ነው አለች። በወቅቱ ከባለሙያዎቹ መሀከል አቶ ዱባለ ጃሌ የተባሉት የባንክ ገዥ በነገሩ የማይስማሙ መሆናቸውንና ድርጊቱ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚጎዳ ነው ይላሉ። እንደ አቶ መለስ ፍላጎት ሳይሆን ቀርቶ መስማማቱ ቀረና የኢኮኖሚ ትንኮሳው በድንበር ተመካኝቶ ወረራ ተፈጸመ። አቶ ዱባለ ጃሌ ከባንክ ገዥነታቸው ተባረሩ።
የኢሳያስን የጦርነት ዝግጅት የሚያውቁት አቶ መለስ እመራዋለሁ የሚሉትን ሀገር ወታደር ሲበትኑ ከረሙ። በጊዜው የሠራዊቱን ቁጥር ካልቀነስን የዓለም ባንክ ዕርዳታ አይሰጥም እያሉ ያጭበረብሩ እንደነበር አይዘነጋም። ታንክ ይዞ የመጣው የኤርትራ ጦር በድንበር ላይ የጠበቀው የአካባቢ ሚሊሽያ ብቻ ነበር። የሕግ የበላይነት ቢኖር አቶ መለስ ኤርትራን ለመጥቀም በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸሙት ወንጀል በሀገር ክህደት መጠየቅ በተገባቸው ነበር።
የማይቀረው ጦርነት ተለኮሰ። ዛሬ ተገለሉ የተባሉት የህወሓት አመራር አባላት ለጊዜው ገነው ወጡ። ህዝቡም በሀገር ጉዳይ ሳያኮርፍ በጋራ ቆመ። የልጆቹን ሕይወት ጭምር መስዋዕት አደረገ። የአቶ መለስን ሚና በሚገባ ስለሚያውቅም “ከባድመ መልስ ወደ መለስ!” እስከማለት በቃ። በሁለቱ ወንድማምቾች መሀከል በተደረገው በዚያ ጦርነት ከ90 ሺህ በላይ ሕይወት ጠፋ። ቂም ቋጥረው የሰነበቱት አቶ መለስና በረከት ዘመቻቸውን አጠናክረው ሻዕቢያ በጦርነት ያጣውን ድል ሊያጎናጽፉት አዲስ እንቅስቃሴ ጀመሩ። አቶ መለስ የይስሙላውን ፓርላማ፣ የህወሓት አመራር የተባለውን እንኳ ሳያማክሩ አልጀርስ ላይ ሮጠው ሔደው ይግባኝ የሌለው ውሳኔ እንቀበላለን የሚል ፊርማ በመፈራረም ብሔራዊ ድሉን ሸጠው ተመለሱ። በዚህ አላበቁም፤ ሻዕቢያ ላይ ጨክነዋል ያሏቸውን ጓዶቻቸውን ከፓርቲው መነጠሩ። አቶ ስዬን በሙስና እስር ቤት ሲወረውሩ እነ አቶ ገብሩን ያለ ጡረታ አባረሩ። ሚስቶቻቸውንና የአንዳንዶቹን ዘመዶች ጭምር ከሥራቸው አፈናቀሉ። በጦርነቱ የተማረኩ ኤርትራዊያንን በአግባቡ ይዘው ወዛቸው ጠፍ እንዳለ ሳይጠየቁ አለባብሰው በአውቶብስ ወደ ሀገራቸው ሸኙ።
በጦርነቱ የተማረኩ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ የነመለስ አጀንዳ ሆኖ አያውቅም። እንደጥያቄም ገፍተው ሔደው አልጠየቁም። ከአሰብና ምፅዋ ወደብ የተዘረፉ የመንግሥትና የኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ንብረትን በተመለከተ የካሣ ኮሚሽኑን ውሳኔ ለማስፈፀም አልተንቀሳቀሱም። ይልቁኑ ንብረታቸው ከወደብ የተዘረፈባቸው ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ባንክ ዕዳችንን ለመክፈል የፋታ ጊዜ ይሰጠን ብለው በየደረጃው አቤቱታ አሰሙ። በየጊዜው በንግድ ም/ቤት በኩል መለስን ጠየቁ። ለፓርላማ ተብየው አቤት አሉ፤ ነገር ግን ሰሚ አጡ። የብዙዎቹ ንብረት በሐራጅ ተሸጠ። ከጨዋታ ውጭ ሆኑ። የወያኔ ልዩ አስተያየት ከተደረገላቸው ጥቂት የወያኔ ደጋፊዎች በስተቀር ብዙዎች ዛሬ ባዷቸውን ቀርተዋል። ለተወረሰ ንብረት የተበደሩትን ብድር እየገፈገፉ ነው።
አቶ መለስ በምርጫ 97 ዋዜማ ከመሸኘት የተረፉና ከሥራ የተባረሩ ኤርትራዊያንን የውዝፍ ደምወዝ እየከፈሉ ወደ ሥራ መለሷቸው። የዛን ሰሞን የብሔራዊ ትኩረቱ የሠሩትን ሠርተው በምርጫ ካርድ እንሸኛቸዋለን ስለነበር ለዚያ ውሳኔ ትኩረት የሰጠ አልነበረም።
ከጦርነቱ በፊት እንደታየው የባንክ ብድር ቅድሚያ የሚሰጠው በቀጥታ የሻዕቢያ አባላት ለነበሩ ነጋዴዎች እንደነበረ አይዘነጋም። ከእነሱ ከተረፈ ለባለሥልጣናት ዘመዶችና ህወሓት ለፈጠራቸው ነጋዴዎች ነበር።
በዚህም በርካታ የትራንስፖርት ድርጅቶች፣ ኢንዱስትሪዎችና ማከፋፈያዎች በኢትዮጵያ ባንክ ብድር በኤርትራውያን ይንቀሳቀሱ ነበር። በዚህ ወቅት ነው በቡና አምራችነት የማትታወቀው ኤርትራ በቡና ኤክስፖርት ኢትዮጵያን ቀድማ በሰንጠረዥ የተቀመጠችው። በኢትዮጵያውያን ኪሳራ ኤርትራንና ኤርትራውያንን ማበልጸግ ቀጠለ። ከዚህ አልፎ ዛሬም ድረስ ለውጭ ዜጎች ያልተፈቀደው የባንክ ሥራ ፈቃድ ተሰጥቷቸው “ሆርን” የተሰኘ ባንክ ለመክፈት በእንቅስቃሴ ላይ ነበሩ። ‘ኤርትራን የአፍሪካ ሲንጋፖር እናደርጋለን’ የሚለው ምኞት የአቶ ኢሳያስ ብቻ ሳይሆን መሰረቱ ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግሥት ጭምር ነው።
በጦርነቱ ሰሞን መጀመሪያ እንደምናስታውሰው ወያኔን ከሻዕቢያ ለመለየት ለአብዛኛው ህዝብ ግራ ነበር። በወቅቱ ከኤርትራውያን የተነጠቀውን የመንግሥት ሥልጣንና ቤት እንዲሁም ንብረት “ጊዜው የኛ ነው” ያሉ የህወሓት አባላት የድርሻቸውን ወስደዋል። ከዚህ ባሻገር ህዝቡ፤ “አብረን ኖረናል የፀጥታ ችግር ካለም ጉዳዩ በአግባቡ ይያዝ” ሲል የሰማው አልነበረም። “የዓይናቸው ቀለም ካላማረን እናባርራለን …” እስከማለት ተደረሰ።
በጦርነቱ በመቀሌ አይደር ት/ቤት በሕፃናት ላይ ከተፈጸመ የቦንብ ድብደባ እስከ ግንባር የደረሰው ሰብዓዊ ዕልቂት ሁሉም የሚያቀውቀው ስለነበር መዘርዘሩ ቁብ የለውም። ቁም ነገር የሚኖረው አቶ መለስ እንዴት ዛሬ “ኤርትራውያን ኑ! እንደ ኢትዮጵያዊ ትታያላችሁ” የሚል ሕግ እስከማውጣት ደረሱ የሚል ነው።
በአቶ መለስ ሒሳብ ኢትዮጵያውያንን በዘር የመክፈሉ እና ለብሔራዊ ጉዳይ በአንድነት እንዳይቆሙ የማድረጉ ሥራ ተሠርቶ አልቋል። የባድመ ጉዳይ ዕልባት ያግኝ የሚለው የትግራይ ህዝብ፤ “ሌላው ወገንህ ሊጨርስህ ነው፣ እኔን ካልደገፍክ አለቀልህ” ተብሎ ከምርጫ 97 በኋላ ሰፊ የዘመቻ ሥራ ተሠርቷል። አቶ መለስ ከዚያ ቀደም በኤርትራ ደጋፊነት ጭምር ሲከሷቸው የነበሩት ህወሓቶች እና የትግራይ ምሁራን በሙሉ በጫማዬ ስር ውለዋል የሚል ብርቱ ግምት አላቸው። ለዚህም ይመስላል ዛሬ በሀገር ክህደት፣ ሉዓላዊነትን አሳልፎ በመሸጥ አቶ መለስን የሚከስ የወያኔ የቀደመ አመራር አይደመጥም። ከደርግ ጊዜ ጀምሮ አቶ መለስ ታላቅ ሴራ አለው ሲሉ የነበሩትም “አፋቸውን” እንዲይዙ ተደርገዋል።
የእነ መለስ የወቅቱ የጠነከረ ዕምነት የትግራይ ህዝብ (በእነሱ የተሳሳተ ስሌት) የቀረው ህዝብ ጠላቴ ነው ብሎ በማመን ህልውናውን ከህወሓት ጋር አጣብቋል ባይ ናቸው። በዚህ ስሌት መሰረት ከላይ እስከታች ላለፉት ጥቂት ዓመታት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የትግራይ ተወላጆችና ምሁራን የሚነገራቸውን ውሸት አምነው “ትልቅ አደጋ ተደቅኖብናል” ብለው የቀረውን ወገናቸውን እንዲጠራጠሩ ሆነዋል።
የትግራይ ህዝብ ይሔን ሃሳብ ተቀብሎታል ባይባልም፤ የትግራይ ምሁራንና ተወላጆች ዛሬም ከወያኔ “ጅቡ ሊበላችሁ ነው” ማስፈራሪያ በቅጡ ነቅተው ምላሽ ሲሰጡ አይታይም። አንዳንዶቹም ‘ችግሩ እኛን አይነካንም፣ ስለሌላው ምን ቸገረን’ የሚል ዝምታ የዋጣቸው ይመስላሉ። ጥቂቶች የበኩላቸውን ጥረት ቢያደርጉም እነሱም ወያኔ እንደከሃዲዎች እንዲቆጠሩ ስለሚቀሰቅስባቸው ፈራ ተባ ለማለት የተገደዱ ይመስላሉ።
በእነ አቶ መለስ ስሌት ትናንት ለሀገር ብሔራዊ ደህንነት ያሰጋሉ የተባሉትን ኤርትራውያንን ለመጥቀም ከዚህ የተሻለ ጊዜ የለም። በኤርትራ ንብረታቸው ስለተወረሰባቸው፣ ተማርከው ፍዳቸውን ስለሚያዩ ዜጎች የነሱ አጀንዳ አይደለም። ይህንን ስናይ ታዲያ አቶ መለስ እና ጥቂት አፍቃሪ ኤርትራዊ አጋሮቻቸው የሚጨነቁላቸው ኤርትራውያን ብዙ መንገድ ከሚመታቸው እነሱ ኤርትራ ቢሔዱላቸው አይሻልም? እያልን እንጠይቃለን። ጥያቄው ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፈው የሚሸጡት ለፍርድ እስክናቀርባቸው ይቀጥላል።



