ለኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው
ወዶ የዋጡትቅልጥም ከፍርምባ ይጥም
ታምራት ታረቀኝ
ከኢ/ር ግዛቸው ጋር ለመጨረሻ ግዜ ተገናኝተን የተነጋገርነው ሰኔ 11 ቀን 2001 ዓ.ም. በእኔ ጠያቂነት በርሳቸው ቢሮ ውስጥ ነው። ከቀትር በኋላ። ርሳቸው ጋር ለመነጋገር ምክንያቶቼ ሁለት ነበሩ። አንደኛው ሰኔ 8 እና 9 በነበረው የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በሌሎች ሰዎች እየተመሩ ስህተት ሲፈጽሙ ማየቴ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ዋና ፀሐፊ አስራት ጣሴ ከኃላፊነት በመሸሽ በምክትላቸው ወጪ የሚያደርጉዋቸው ደብዳቤዎች ጉዳይ ነበር።
ከላይ በጠቀስኩት የምክር ቤት ስብሰባ ላይ፤
አንድ፦ ሥራ አስፈጻሚው ማሟያ ምርጫ ሲካሄድ አቶ ይልቃል ጌትነት በሁለተኛነት ተመርጠው እያለ ለምክር ቤቱ ቀርበው እንዲያልፉ የተደረገው አቶ ንጉሴ ነውጤ ናቸው። ይህም ሆኖ በአንደኝነት የተመረጡት አቶ ይልማ ይፍሩ “እኔ ዕድሜየ ገፍቷል ቦታው የሚገባው ለወጣቶች ነው” ሲሉ፤ አቶ ይልቃል በቀጥታ የሥራ አስፈጻሚው አባል መሆን ሲገባቸው፤ ስላልፈለጋችሁ አሰቀርታችኋቸዋል የሚል ጥያቄ ተነሳ።
ይህን ጥያቄ አስቀድመው ሞገቱት አቶ አስራት ጣሴ ሲሆኑ፣ እርሳቸውን ተከትለው ኢ/ር ግዛቸው ቀጸሉና የምትለው ሐሰት ነው፤ በሁለተኛነት የተመረጡት አቶ ንጉሴ ናቸው አሉ። ለዚህም ማረጋገጫ ቃለ ጉባዔ አለን አሉና አቶ አሥራት ያመጡላቸውን ቃለ ጉባዔ ለማሳየት ከመቀመጫቸው ተነሱ። ቃለ ጉባዔው በውጪ በኩል ተሰብሳቢዎቹ መጀመሪያ ወደ ስብሰባ ሲገቡ የፈረሙበት የእጅ ጽሑፍና ፊርማ ተያይዟል። ኢ/ር ያንን አይተው በልበ ሙሉነት ኮራ ብለው “ይሄው የፀደቀ ቃለ ጉባዔ አለን” ሲሉ፤ ተነቦ ተፈርሞበት የፀደቀ ቃለ ጉባዔ አይደለም። ስለሆነም ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም የሚል ተቃውሞ ተሰነዘረባቸው። ወረቀቱን በእጃቸው እንደያዙ በቆሙበት ሆነው ገለጥ ገለጥ ሲያደርጉት በመጨረሻው ገጽ ላይ የሥራ አስፈጻሚው አባላት ስም ተዘርዝሮ ከፊት ለፊት ያለው የፊርማ ቦታ ባዶ ነው። ክው ብለው ደነገጡ። በድንጋጤ ውስት ሆነውም “ታዲያ ምን አለበት አሁንም ቢሆን እንፈርመዋለን” በማለት ሌላ ስህተት ተናገሩ።
ሁለት፦ በተጓደሉ የም/ቤት አባላት ምትክ ማሟላት ሲደረግ ቀዳሚው አቶ ብስራት አቢ ሆነቀ ሳለ ሌላ ሰው እንዲገባ ተደርጓል የሚል ተቃውሞ ቀረበ። ለዚህም እየተረዳዱ መልስ ሲሰጡ ኢ/ር ግዛቸው “እኔ አቶ ይታየው ሠፈራው ይተካ ያልኩበት በተሰጠኝ ዝርዝር 59ኛ ተራ ቁጥር ላይ የሚገኝ በመሆኑ ነው” በማለት ግልጥ ስህተት ተናገሩ። ከአንድ እስከ ስልሳ ያሉት ቋሚ አባላት ናቸውና። ተጠባባቂዎቹ 15 ሲሆኑ፣ አቶ ብስራት 14ኛ፣ አቶ ይታየው 15ኛ ነበሩ።
በወ/ት ብርቱካን መታሰር የፓርቲውን መሪነት የያዙት ኢ/ር ግዛቸው በመተዳደሪያ ደንባችን አንቀጽ 29.3 “የፓርቲው ፕሮግራም ደንቦች ውሳኔዎችና መመሪዎች ተግባራዊ መሆናቸውን ይከታተላል ያረጋግጣል” በሚል ለሊቀመንበሩ የተሰጠውን ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ በሰዎች እየተገፉ በአደባባይ ስህተት ሲፈጽሙ አይቼ ለማለፍ ምንም እንኳን በወቅቱ የታገድኩ ቢሆንም የአንድነት መሥራችነቴና የሥራ አስፈጻሚ አባል ሆኜ መሥራቴ በዚህም የተነሱትን ጉዳዮች የማውቅ መሆኔ አላስቻለኝምና ከላይ የገለጽኩት ሰኔ 9 ተፈጽሞ ሰኔ 11 በቀጠሮ አነጋገርኳቸው።
ጉዳዩን በዝርዝር ከተነጋገርንበት በኋላ “እኔ እንደተረዳሁት ሆነ ብለው ሊያሳስትዎትና በርስዎ ስህተት አትራፊ ለመሆን የሚፈልጉ፤ ራሳቸው ተሳስተው ርስዎንም የሚያሳስቱ ሰዎች ያሉ ይመስለኛል። ምንም ሆነ ምን የመሪነቱ ቦታ ላይ እንደመገኘትዎ የጥሩው ነገር ተመስጋኝ፣ የመጥፎው ነገር ተወቃሽና ተጠያቂ ርስዎ ነዎትና አስተውለው ቢሠሩ መልካማ ነው። ሲሳሳቱም አውቀው ቢሳሳቱ ይሻላል፤ በሌሎች ተገፍተው ከሚሳሳቱ። የራስን ስህተት ለማረምም ይቻላል ኃላፊነቱንም መውሰድ ይቻላል። በቀደም ያልተፈረመ ቃለ ጉባዔ ይዘው፤ ‘ተፈርሟል’ ብለው ሲከራከሩ ያለመፈረሙን ባዩ ግዜ ምን ያህል እንደተሸማቀቁ በደንብ ተከታትዬዎታለሁ። ስለምክር ቤት ማሟም ሲናገሩ ሌላው ቀርቶ ከአንድ እስከ ስልሳ ያሉት ቋሚ አባል መሆናቸውን እንኳና ማስታወስ አልቻሉም ነበር። …” ብያቸው ተግባብተን የተለያየን መስሎኝ ነበር።
እግረ መንገዴን ከተገናኘን አይቀር በማለት ባነሳሁት በዋና ፀሐፊውና በምክትሉ ስለሚሰራው ደንብ ያልተከተለ አሠራር ተማምነን ወዲያውኑ እንደተለየን ዶ/ር ኃይሉን፣ አቶ አስራትን እና አቶ መስፍንን (ም/ል ፀሐፊውን) በነገራችን ላይ አሁን አቶ አንዱዓለም በሹመት ዋና ፀሐፊ ሲባልማ ይህ ሰው ምክትል ነው) ሰብስበው በም/ል ፀሐፊው የተጻፈልኝ ደብዳቤ ተለውጦ በዋና ፀሐፊው ተፈርሞ እንዲደርሰኝ አድርገዋል።
ከዚህ በመነሳትም ንግግራችን ፍሬ አፍርቷል። ኢ/ር ገብቷቸዋል ማለት ጀምሬ ነበር። ያለመሆኑን ለመረዳት ግን ግዜ አልፈጀብኝም። ይህን የሚያሳዩት ድርጊቶቻቸው እጅግ ብዙ ስለሆኑ እዚህ ላይ መዘርዘሩ አንባቢን ማሰልቸት ይሆናል። ደግሞስ በገሃድ የሚታይ ጉዳይ አይደል ሁሉ የሚያውቀው።
ታዲያ ይህን ጉዳይ ዛሬ ማንሳት ለምን አስፈለገ? የሚል ቀና ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። መልሱ በርዕስነት የተጠቀምኩበት አባባል ውስጥ ይገኛል። “ወዶ የዋጡት ቅልጥም ከፍርምባ ይጥም” እንዲሉ ኢ/ር ግዛቸው እንነጋገር የሚሏቸውን “ሰርጎ-ገብ” አፍራሽ እያሉ ከሚያጨበጭቡላቸው ጋር ሲዘምሩ፤ እርቅ ይፈጠር የሚሏቸውን “ወያኔ አደራጅቶ የላከብን” እያሉ፤ አባራቸው! ክሰሳቸው! ደግ አደረካቸው! ከሚሏቸው ጋር እስክስታ ሲወርዱ፤ የመድረክ ጉዳይ ታስቦበት የተሠራ አይደለም የሚሏቸውን “ፀረ-ሕብረት”፣ “ድብቅ ዓላማ ያላቸው”፣ … ወዘተ እያሉ አንድነት የአማራ ተወካይ ይሆናል ከሚሉት ጋር አሸሸ ገዳሜ ሲሉ፤ “ሊቀመንበሩ በእስር ቤት የምትገኝ ፓርቲ ወደ ምርጫ ሊገባ አይገባውም” ሲባሉ፤ “በብርቱካን መነገድ የሚከጅሉ” በማለት እያወገዙ እኛ ስንመረጥ ብርቱካንን እንፈታታለን” ከሚሉ ጋር አብረው ሲያፌዙ የአንድነትን ፕሮግራምና ደንብ ለውጠው ከእነ አቶ ስየ ጋር ውስኪ ሲራጩ ቆይተው፤ ዛሬ “እለቃለሁ” ማለታቸው መሰማቱ ከመድረክ ሁለተኛ ጉባዔ ላይ ፈልገን ልናያቸው ያለመቻላችን ያ የማይወዱት ሁለተኛ ሰው መሆን ርሱም በዝቶባቸው ሲነጠቁ ወደው የገቡበት ፈቅደው የፈጠሙት ነውና ማማረርም መሸሽም ሳያስፈልግ ዋጥ አድርጎ መቻል ነው ለማለት ነው ይህ ጽሑፍ ያስፈለገው።
አንድነት ዛሬ ለሚገኝበት አሳፋሪ ደረጃ መብቃት ሙሉ ኃላፊነቱ የኢ/ር ግዛቸው ነው። አሁን ደግሞ አንድነትን ለማያውቁትና ለማያውቃቸው ሰዎች ያለ ጨረታ ሸጠው ትቼ እሄዳለሁ ማለት የውርደት ውርደት ነው። ያኔ ለመልቀቅ ወስኜ ነበር ወዳጅ ዘመድ ውርደት ነው እያለ አስቸገረኝ እንጂ፤ ባሉበት ሰዓት ለቀው የያኔውን ውርደት ቢቀበሉ ይሻልዎት ነበር። ያን ግዜ ቢያንስ አንድነትን አልገደሉትም፣ አሳልፈውም አልሰጡትም ነበር። የአሁን ግን ውርደት ብቻ አይደልም። ለታሪክና ለትውልድ ፍርድም የሚቀርብ ልጆች ብቻ አይደሉም የልጅ ልጆችዎ የሚያፍሩበት ነው። እያንዳንዷ ክንውንም ተመዝግባ ትቀመጣለች።
ኢ/ር ግዛቸው የአቶ አስራት ምክርና ውትወታ የት እንዳደረሳቸው በአቶ ስየ አማካኝነት ከፖለቲካ ውሳኔ ወደ ቆረጣ ለመሸጋገር ያደረጉት ሙከራ ሁሉ አልሰራላቸውም። አንድነትን ገደሉት ራሳቸውን ቦታ አሳጣቸው። ለአራት ወራት የማይወዱትን ሁለተኛ ሰውነት እንደምንም ችለው አንደኛውን ወንበር ለመያዝ ሲጠብቁ ከነጭራሹ ሁለተኛነቱንም አጡት። በዚህም አንድነትን ይበልጥ ቦታ አሳጡት፤ ይበልጥ ገደሉት። መድረክ ውስጥ መሥራት ተቸገርን በማለት መግለጫ የሰጡት የሁለት ፓርቲዎች ሊቃነ መናብርቶች ምክንያት አድርገው ያቀረቡት አንድነትን መሆኑ ደግሞ ሌላው አሳፋሪ ክስተት ነው። የመድረክ ጉዳይ ሲነሳ ወባ እንደያዘው ሰው ያርገፈግፈው የነበሩት አቶ አስራት ዛሬም መድረክን አትንኩብኝ እሉ ይፎክራሉ።
በመጨረሻ እስከ ዛሬ አምቄ የያዝኩትንና መልስ ያላገኘሁለትን ጥያቄ ለኢ/ር ግዛቸው ላንሳ። የካቲት 12 ቀን 2001 ዓ.ም. አንድነት ከመድረክ ጋር መቀላቀሉን የገለጸው መግለጫ ከመሰጠቱ በፊት የመግለጫውን ረቂቅ ለብሔራው ምክር ቤታችን ሰብሳቢ ለዶ/ር ሽመልስ ተ/ጻድቅ በመስጠት “እነዚህ ሰዎች አንድነትን ሊያጠፉት ነው፤ አንተ የተቃውሞ ደብዳቤ ጻፍና ስጠን፤ እኔ ለሥራ አስፈጻሚው አቅርቤ አስወስናለሁ” ብለዋቸው፤ ርሳቸውም በነገሩም በርስዎም አምነው ደብዳቤውን አዘጋጅተው ሰጡዎት። ደብዳቤውን ተቀብለው ከዋና ፀሐፊው ጋር በመነጋገር ሥራ አስፈጻሚውን ለየካቲት 13 ስብሰባ ጠርታችሁ፤ እናንተ ግን በ12 ተፈራርማችሁ መግለጫ ሰጣችሁ። በርግጥ ርስዎ በመግለጫው ላይ አልተገኙም። የካቲት 13 ሥራ አስፈጻሚው ሲሰበሰብ ጉዳዩ በሌሎች አጀንዳዎች እንዲዋጥ ተደርጎ የዶ/ር ሽመልስ ደብዳቤ በሚል የመጨረሻ አጀንዳ ሆኖ ሆኖ ቀረበ።
አንዳንዶች ዶ/ር ሽመልስ በግል የጻፈውን ደብዳቤ አጀንዳ አድርገን መነጋገር አንችልም ሲሉ እንኳን የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የፓርቲው አባል ያልሆነ አንድ ዜጋ አንድነት ሊመለከተው ይገባል ያለውን ጉዳይ ጽፎ ቢያቀርብና ጽ/ቤቱ በአጀንዳ ለሥራ አስፈጻሚው ቢያመጣው ማየት ግዴታችን ነው። አንድን ነገር በውይይት ማንሳት መጣል ይቻላል። ከመነሻው አይቅረብ ማለት ግን ጤናማ አካሄድ አይደለም የሚሉ አስተያየቶች ቀርበው ክርክር ሲደረግ ደብዳቤው እንዲጻፍ ያደረጉት ኢ/ር ግዛቸው ተከራካሪ ሆነው አልታዩም። ይባስ ብለው በአጀንዳነት ይቅረብ 4 መቅረብ የለበትም 7 ተአቅቦ 3 በሆነ ድምፅ ሲወሰን፤ ኢ/ር ግዝቸውና አቶ አስራት ድምፀ ተአቅቦ ነበሩ። ራሳችሁ አጀንዳ ብላችሁ ባቀረባችሁት ጉዳይ ላይ እንዴት ድምፀ ተአቅቦ ታደርጋላችሁ ተብለው ተጠይቀው አጥጋቢ ምላሽ መስጠት አልቻሉም። ከዚህ በኃላ ነበር በአጀንዳ አይቅረብ ብላችሁ ከጣላችሁት እና አጀንዳ የማቅረብ መብት አለን ብለን እኔና አቶ አምሀ “ሥራ አስፈፃሚው ከተሰጠው ውክልና አልፎ ሄዷል” በሚል አጀንዳ አስይዘን 12 ለ2 በመባሉ የሚታወቀው ውሳኔ የተላለፈው።
ዶ/ር ሽመልስ ሰኔ 9 ቀን 2001 ዓ.ም. በተደረገው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ በኢ/ር ግዛቸውና በርሳቸው መካከል የተፈጸመውንና ያሳዘናቸውን ነገር በመዘርዘር ወቀሳ አቅርበው ኢ/ር ግዛቸው ምላሽ መስጠት አልቻሉም ነበር።
ኢ/ር ግዛቸው መጀመሪያ ዶ/ር ሽመልስ ደብዳቤ እንዲጽፉ ለማነሳሳት ያበቃዎት ምክንያት ምንድን ነበር? 24 ሰዓት ባልሞላ ግዜ ውስጥ አቋምዎን የሚያስለውጥ ምን ችግር ገጠመዎት? ከዛ በኋላስ ዶ/ር ሽመልስን ያንን ደብዳቤ በመጻፋቸው ካወገዙዋቸው ሰዎች አንዱ ሆነው መሰለፍዎና ዶ/ር ሽመልስን “ፀረ-መድረክ” አድርገው መፈረጅዎና ማስወራትዎ ከምን የመጣ ነው? እነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሳይሰጡባቸው አብሮዎት ይኖራሉ። እንደውም የተረሳ እያስታወሱ የሞተ ነገር እየቀሰቀሱ።
ለማንኛውም “ወደሽ ከተደፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ” ነውና ኢ/ር ምክር ከመስማት፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ከመወያየት፣ ለፓርቲ ሕግ ከመገዛት፤ በጭብጨባ ታውረው፣ በጀሌ አጀብ ታብየው፣ በፖለቲካ ውሳኔ ተማምነው አውቀው በድፍረትና በማንአለብኝነት የገቡበት በመሆኑ መቻል ነው። በአሁኑ ሰዓት አንድነትን ጥሎ መሄድ ግን በቁም መቀበር ነው። ደግሞም እኮ ወኔው ካለዎት፣ ብርታቱን ያገኙት ከሆነ፣ ከደረሰብዎት ሁሉ ተምረው ከሆነ፣ አንድነትን ማዳንና ስምዎን ማደስ ቀላል ነው። ግን ቁርጠኝነት ይጠይቃል። አንድነትን ከዓመት በፊት ወደነበረበት መመለስና ከዛ መጀመር። ይህን ለማድረግ ወኔውም ብቃቱም ከሌለዎት “ወዶ የዋጡት ቅልጥም ከፍርምባ ይጥም” ነውና የሚቻለውን ብቻ ሳይሆን የማይቻለውንም ላያስችል አይሰጥም እያሉ መቻል ነው። ወንበሩን ሲመኙት በብርቱካን እጅ በመግባቱ ሲቆጩና ሲያዝኑ ቀላል መስሎዎት ነበር።
መሪነት ወንበር መመኘት ተሳክቶም ከወንበሩ መቀመጥ አይደልም። መሪነት ማለት ሰዎች በጥልቀትና በማያቋርጥ ሁኔታ እውነታዎችን እንዲያውቁና እንዲተረጉሙ ማስቻልና በሂደቱም ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማብቃት ነው። የጌታና ሎሌ አሰራር መፍጠር የመሪነት ችሎታ መገለጫ አይሆንም። ጊዜውም ይህን አይፈቅድም። ዓይንን ጨፍኖ መሞከር ደግሞ ያደረሰው ታይቷል። ሎሌ እስከተመቸው እንጂ እስከመጨረሻው አብሮ አይቆምም።
ታምራት ታረቀኝ



