Ethiopia Zare (አርብ ሚያዝያ 23 ቀን 2001 ዓ.ም. May 1, 2009)፦ በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ታሪክ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ጉልህ ስፍራ ያላቸውና፣ ከቅንጅት አመራሮች ጋር ለ21 ወራት ታስረው የተፈቱት የአሁኑ የአንድነት ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ ታምራት ታረቀኝ በብዕር ስም በጋዜጣ ጽፈው ባወጡት ጽሑፍ ፖርቲውን አደጋ ላይ ጥለዋል በሚል ዛሬ ጠዋት ከአንድነት ፓርቲ ለአንድ ወር ታገዱ።

 

ምንጮች ለኢትዮጵያ ዛሬ እንደገለጹት አቶ ታምራት ታረቀኝ አንድነት ፓርቲ ውስጥ ባላቸው ኃላፊነት ከወጣቶች ጋር በጥሩ ግንኙነት ሥራቸውን ይሠሩ እንደነበርና ይህም በአንዳንድ ሸምገል ባሉ አመራር አባላት ስላልተወደደላቸው ከጥቂት ወራት ጀምሮ በክፉ ዓይን ይታዩ እንደነበር ነው።

 

ከሁለት ወራት በፊት “ጎግል” በተባለ በሀገር ውስጥ በሚታተም አንድ የአማርኛ ጋዜጣ ላይ “ወ/ት ብርቱካን ቃሊቲ በገቡ ማግስት” የሚል ርዕስ በተለይ የፓርቲው አመራር የሆኑትን ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያምን የሚተች ጽሑፍ ወጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ዛሬ ጠዋት ሥራ አስፈጻሚው ተሰብስቦ የዕጅ ጽሑፉን ከጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ማግኘቱን በመግለጽ “ይህ ፓርቲውን የሚጎዳ ተግባር ስለሆነ መታገድ አለበት” የሚል ሃሳብ ቀርቦ ለአንድ ወር ከፓርቲው እንዲታገዱና ከዛ በኋላ ያለው በቀጣይ ውሳኔ ይሰጥበታል የሚል ውሳኔ መተላለፉን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልፀዋል።

 

ምንጮቻችን ጨምረው እንደገለጹት የእጅ ጽሑፉ የሳቸው መሆኑን እንዲምኑ ሥራ አስፈጻሚው ለአቶ ታምራት ሲያቀርብ “ይህን የምወደው አይደለም፤ ነገር ግን ከተጻፈው ነገር ውስጥ አንድም ሐሰት ነገር የለበትም። ሁሉም እውነት ነው። በመናገርና በመጻፍ ነፃነት ውስጥ አንድ ሰው በብዕር ስም የፈለገውን ነገር መጻፍ ይችላል።” ብለው መልስ ሰጥተዋል።

 

ከሥራ አስፈጻሚ አባላት የተወሰኑት አቶ ታምራት ታረቀኝ አንድነትን ለማቋቋም በጣም ከደከሙት አባላት ውስጥ አንዱ በመሆናቸው ጉዳዩ ጥፋት ሆኖ ቢገኝ እንኳን በማስጠንቀቂያ ሊታለፉ ይገባል የሚል አቋም የነበራቸው ቢኖሩም፤ ቀድሞውኑ የአቶ ታምራት በፓርቲው መኖር የማያስደስታቸው አመራሮች መታገድ አለባቸው የሚለውን ውሳኔ አስተላልፈዋል።

 

በዛሬው የሥራ አስፈጻሚ ውሳኔ የተወሰነው ከፓርቲው ለአንድ ወር እንዲታገዱ የሚል ሲሆን፣ አቶ ታምራት በፓርቲው የሙሉ ጊዜ የቢሮ ሠራተኛ በመሆናቸው በሥራቸው ይቀጥሉ አይቀጥሉ የሊለውም ሰኞ ዕለት ውሳኔ እንደሚሰጥበት ለማወቅ ችለናል።

 

አቶ ታምራት ታረቀኝ በ1987 ዓ.ም. የመአህድ አባል የነበሩ ሲሆን፣ ከዚያም ኢዲአፓ-መድህንን አቋቁመው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊና ም/ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል። ቅንጅት ሲመሰረት ከምስረታው ጀምሮ ጉልህ ድርሻ የነበራቸውና ከውህደት በኋላ የምክር ቤት አባል ሆነው ሠርተዋል። በወቅቱ ከቅንጅት አመራሮች ጋር አብረው የታሰሩና የተፈቱ፣ በ1993 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተነስቶ በነበረው ረብሻ ዝዋይ ታስረው የነበሩ ሲሆን፤ አንድነት ፓርቲ ሲቋቋም ከአመሰራረቱ ጀምሮ ጉልህ ድርሻ የነበራቸው ናቸው። በፓርቲው ውስጥም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ በመሆን እየሠሩ ይገኛሉ።

 

አንድነት ፓርቲ ከፓርቲው አመራሮች ውስጥ ሲታገድ አቶ ታምራት ታረቀኝ ሁለተኛው ሰው መሆናቸው ታውቋል። ከአንድ ወር በፊትም የፓርቲው መሥራች፣ የምክር ቤት አባልና የሥራ አስፈፃሚ አባል የነበሩት አቶ አማሃ ዳኘውን ማገዱ ይታወቃል። አቶ አማሃም የታገዱት እንዲሁ በጋዜጦች ላይ ጽሑፍ ጽፈዋል በሚል ነበር።

 

ኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡት የጠየቃቸው የዘወትር ተባባሪ የፖለቲካ ተንታኝ፤ “ፓርቲው ለማገድ ያቀረበው ምክንያት ሐሰት ቢሆንም፣ እንደተባለው እውነት ቢሆንም፤ አንድነት ፓርቲ የወሰደው እርምጃ ፓርቲው የግለሰቦችን ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት የሚጋፈፍና በመናገር፣ በመጻፍ፣ በማንበብ ሰብዓዊ መብቶች ላይ የፓርቲው አመራሮች ያላቸውን የተሳሳተና ፀረ-ፕሬስ የሆነ አቋም አጉልቶ ሊያሳይ የሚችል ነው።” ብለዋል።

 

አክለውም፣ “ግለሰቦቹ እውነትም እንደተባለው ሃሳባቸውን በነፃነት ገልጸው ከሆነ፤ ፓርቲው የራሱን አመራሮች ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት ሊያስከብር ካልቻለ፤ የሌሎች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት (የመናገር፣ የመፃፍ፣ የማንበብ፣ …) እንዲሰፍን ከማይፈልጉት ፓርቲዎች ውስጥ ያስመድበዋል። በመሆኑም የፓርቲው አመራሮች ራሳቸውን አጥብቀው ሊመረምሩና አቋማቸውን ሊያስተካክሉ ይገባል።” ሲሉ ጠንከር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ