ወገኖቻችን በአገር ቤት ለለውጥ ዋጋ እየከፈሉ ነው - በውጭ ያለነውስ? (ግርማ ካሣ)
ግርማ ካሣ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.) የካቲት 27 ቀን 2002 ዓ.ም.
ግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም. ምርጫ በኢትዮጵያ ይደረጋል። ይህን ምርጫ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ሰንብተዋል። ስለዚህ ምርጫ ከአዲስ አበባ የሚመጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በአገር ቤት ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተከፈተውን እጅግ በጣም ጠባብ እድል በመጠቀም፣ የምርጫውን ዘመቻ በተጧጧፈ መልኩ የያዙት ይመስላል። ምንም እንኳን ዘግይተው ቢጀምሩም የምርጫ ክርክሮች በመጠኑም ቢሆን እየተሰሙ ነው። አፈናውና እንግልቱ፣ መታሰሩና መገደሉ ቢበዛም ያንን ሁሉ በመቋቋም ሕዝባዊ ስብሰባዎች በመደረግ ላይ ናቸው።
በዚህ በግንቦት አሥራ አምስቱ ምርጫ 524 (በሶማሌ ክልል ያሉ 23 ቱን ሳይጨምር) የፓርላማ መቀመጫዎች ለውድድር ይቀርባሉ። ገዢው የኢሕአዴግ ፓርቲን በዋናነት በመቀናቀን ትልቅ አማራጭ ሆኖ የቀረበው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ያካተተው መድረኩ ነው። መድረኩ ከ524 ወረዳዎች ከሰላሳ ስድስቱ በስተቀር፣ በ485 ቱ ይወዳደራል። (በዘጠና ሰባት በ418 ወረዳዎች ነበር ቅንጅቱ የተወዳደረው) ቢያንስ ቢያንስ በኦሮሚያ ከ178 ወረዳዎች በ175ቱ፣ በአማራው ክልል ከ138 ወረዳዎች ቢያንስ በ125 ቱ፣ በደቡብ ክልል በሁሉም 123 ወረዳዎች፣ በትግራይ ከ38 ወረዳዎች ቢያንስ በ34 ቱ፣ በቤኔሻንጉል ከ9ኙ ወረዳዎች ቢያንስ በሁለቱ፣ በአፋር ከስምንቱ ወረዳዎች ቢያንስ በአምስቱ፣ በጋምቤላ ከሶስቱ ወረዳዎች በሁለቱ፣ ከሃረሬ ከሁለት ወረዳዎች በአንዱ፣ በድሬደዋ በሁለቱም ወረዳዎች፣ በአዲስ አበባ በሃያ ሶስቱ ወረዳዎች ይወዳደራል።
ገዢው ፓርቲ ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳይኖር ያደረገውንና አሁን በማድረግ ላይ የሚገኘውን ደባና ጸረ-ዲሞክራሲያዊ አሰራር የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታትል ሰው ይዘነጋዋል ብዬ አላስብም። ጠንካራ የተቃዋሚ አባላትና አመራሮች እየተገደሉና እየታሰሩ ናቸው።
በትግራይ በአድዋ አካባቢ መድረኩን ወክሎ ለፓርላማ የሚወዳደር፣ አረጋዊ ገብረዮሀንስ የሚባል ወጣት፣ የኢሕአዴግ ታጣቂዎች ናቸው በሚባሉ ተደብድቦ ተገድሏል። አሁን በትግራይ አክሱም አካባቢ በምትገኝ ውቁሩ በምትባል ከተማ መድረኩን ወክሎ ለፓርላማ የሚወዳደር አያሌው አያለ የሚባል ሌላ ወጣት በታጣቂዎች ተደብድቦ ክፉኛ ተጎድቷል።
በነዚህ መድረኩን ወክለው በሚወዳደሩ ወገኖች ላይ ይህ አይነቱ አሰቃቂና አረመኔያዊ እርምጃ እየተወሰደ ያለው፣ ለሕወሃት ጀርባ እየሰጡ፣ ወደ አንድነትና ወደ አረና እየመጡ ያሉ የትግራይ ወገኖቻችን ሆን ብሎ ለማስፈራራት እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ሰውን በጉቦና በሸቀጣሸቀጥ ማሸነፍ ሳይቻል ሲቀር ወደ ጠመንጃና ወደ ጉልበት መሸጋገር ይሉታል ይሄ ነው።
አንጋፋ ወጣት የፖለቲካ ፓርቲ መሪ፣ የኢትዮጵያ አንሳ ሱንኪ፣ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ አሳፋሪና ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ በግፍ እንድትታሰር ተደርጓል። ይህም የሆነበት ምክንያት አሳሪዎቿ እንደሚሉት ሕግ ጥሳ ሳይሆን፣ በርሷ መሪነት ከጠበቁትና ካሰቡት በላይ የሆነ፣ የሚያራምዱትን የጎሳ ፖለቲካ አፈር ድሜ የሚያስገባ፣ እነርሱ ለአገዛዝ እንዲያመቻቸው በዘር የከፋፈሉት ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር የሚያሰባስብ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሰለጠነ ፖለቲካ በማራመዷ ነበር። “እረኛ ሲመታ በጎች እንደሚበተሉ” አላማቸው የሰላማዊ ትግሉን መሪ በማሰር ብርቱካን ሚደቅሳ የምትመራውን ድርጅት ለመበተን ነበር። ነገር ግን አልተሳካላቸውም። እንግዲህ አንድ በሉ።
አንድ ድርጅት ሁልጊዜ ስህተቶችን ይሰራል። በውስጡም ልዩነቶች መፈጠራቸው አይቀርም። በአንድነት ፓርቲ ውስጥ እንደ ማንም የፖለቲክ ድርጅት ልዩነቶች ታይተዋል። አንዳንድ ልዩነቶች በይፋ ለሕዝብ እንዲወጡ የተደረጉም አሉ። እነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምና አብረዋቸው ያሉ ጥቂት ወገኖች በአንድነት ፓርቲ አመርሮች ላይ ያለ ማቋረጥ ሲዘነዝሩት የነበረውን ወቀሳና ትችት መቼም ሁላችንም የምናስታወሰው ነው። (ይመስለኛል ብዙ የሚያዳምጣቸው ጠፋ እንጂ አሁንም ትችታቸውን ሳይቀጥሉ አልቀረም)
ገዢው ፓርቲ ማርክሲስትና ሚስጥራዊ አሰራር ስላለው በውስጡ ያሉ ልዩነቶችን ማወቅ አይቻልም። ያ ብቻ አይደለም በፓርቲ ውስጥ ካሉ ጥቂት ግለሰቦች ውጭ የተለየ ሃሳብ ከመጣ ውጤቱ መታሰር በመሆኑ ማንም የኢሕአዴግ አመራር አባል በራሱ ላይ ካልፈረደ በቀር ተቃውሞ የሚያሰማበት ሁኔታ የለም። ከታመኑ ምንጮች ያሉን መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አቶ አርከበ እቁባይ፣ አቶ አባይ ጸሃዬ፣ ዶር ቴዎድሮስ አዳኖም፣ አቶ ኩማ ደመቅሳ፣ አቶ ብርሃን ክርስቶስ (በአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር)፣ ዶ/ር ሳሙዔል አሰፋ (በአሜሪካ የቀድሞ የኢትዮጵያ አምባሳደር) እንዲሁም በርካታ የኢሕአዴግ አመራር አባላት በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የተወሰደውን እርምጃ የሚቃወሙና በአስቸኳይ መፈታት እንዳለባት የሚያምኑ ናቸው። ነገር ግን አቶ መለስ ለጋዜጠኖች “ታሳዝነኛለች” እንዳሉት ሳይሆን፣ በፍጹም ጭካኔ የተሞሉ በመሆናቸው፣ እነዚህ የኢሕአዴግ አመራር አባላት እኝህን ዴሞክራት መሳይ አምባገነን ሰው መጋፈጥ አልቻሉም። ይፈሯቸዋል።
እንግዲህ ኢሕአዴግ እንዲህ አይነት አሰራር እያለው ነው፣ የኢሕአዴግ ካድሬዎችና ፕሮፓጋንዲስቶች አይናቸውን በጨው አጥበው፣ እነ ፕሮፌሰር መስፍን የሚያነሱትን ተቃውሞዎችና በአንድነት ውስጥ ተፈጠሩ የተባሉ ልዩነቶችን እያጋነኑ፣ መረጃዎችን እየለጠጡና አንዳንዴ ውሸትን እየጨመሩ፣ ከፍተኛ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በአንድነት ፓርቲ ላይ እየነዙ ያሉት። ነገር ግን አልተሳካላቸውም። ሁለት በሉ።
የፕሮፖጋንዳ ዘመቻው በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ያሉትን ጥቃቅን፣ በአንድ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸውን ልዩነቶችንን በማጋነን ላይ ብቻ የተመረኮዘ አልነበረም። የአንድነት ፓርቲ መድረክን ከተቀላቀለ ጀመሮ በመድረክ አባል ድርጅቶች መካከል ልዩነቶችን ለመፍጠር ተራና ርካሽ ወሬዎችን አፍቃሪ ወያኔ/ኢሕአዴግ ሜዲያዎች ሲያራግቡ እያየን ነው። አቶ ስዬ አብርሃ የአንድነት ፓርቲ በመቀላቀላቸው አረና ትግራይ እንዳዘነ፣ በዶር ነጋሶ ጊዳዳ ውሳኔ ደግሞ እነ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ እንዳኮረፉ፣ በነዶር በየነ ጴጥሮስና በአንድነት ፓርቲ መካከል በደቡብ ክልል ለፓርላማ የሚወዳደሩትን በመምረጥ ዙሪያ ክፍፍሎች እንደተፈጠሩ የሚገልጹና ሌሎች የውሸት ዜናዎች በስፋት ሲሰራጩ ሰንብተዋል። አሁንም አልተሳካላቸውም። ሦስት በሉ።
(በነገራችን ላይ አይጋ ፎረምና ቤን የመሳሰሉ አፍቃሪ ኢሕአዴጎች መድረኩ ስብሰባ ሲያደርግ ስንት ወንበሮች እንደነበሩ፣ የመሰብሰባዊያው አድራሽ ግድግድ ቀለሙ ምን እንደነበረ እንዳልተረኩልን ሁሉ፣ ዛሬ በመድረኩ ከፍተኛ እጩ የፓርላማ ተወዳዳሪዎች ላይ በገዢው ፓርቲ ታጣቂዎች ኢሰባአዊና ኢፍትሃዊ ግድያና ድብደባ ሲፈጸም፣ ታላቅ የአፍሪካ መሪ እያሉ የሚያወድሷቸው አቶ መለስ ዜናዊ፣ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን “ጠላትና እንክርዳዶች” እያሉ ሲጠሩና እንደ ተራ ዱርዬ ሲሳደቡ እየሰሙ ዝምታን የመረጡ አደርባዮች መሆናቸውን እያየን ነው።)
የአንድነት ፓርቲና መድረኩ በተለያዩ የአገሪቷ ግዛቶች ከሕዝቡ ጋር እንዳይገናኙ ተደርገዋል። በአዳማ/ናዝሬት የኢሕአዴግ ካድሬዎች የአንድነትን ሕዝባዊ ስብሰባ ረብሸዋል። በአዲስ አበባ ከአምስት ጊዜ በላይ በመስቀል አደባባይ ስብሰባ ለማድረግ ተጠይቆ ገዢው ፓርቲ ተልካሻ የሆኑ ምክንያቶችን እየሰጠ ፍቃድ ከልክሏል። በርካታ የአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤቶች እንዲዘጉ ለማድረግ ተሞክሯል። በርካታ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች ከሥራ ተባረዋል። ብዙዎች ታስረዋል። አንድነትን፣ ኢትዮጵያውያን እንዳይደግፉ በየክልሉ ከፍተኛ ወከባና እንግልት እየደረሰ ነው። ብዙዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በአንድነት ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ከወያኔ/ኢሕአዴግ አካባቢ ብቻ አይደለም እየመጣ ያለው። ተቃዋሚ ነን የሚሉ በተለይም በውጭ አገር የሚቀመጡ ወገኖችም ይገኙበታል። ከነዚህም መካከል በተለይም አፍቃሪ ግንቦት ሰባት ንቅናቄ፣ የሆኑት እንደ ከረንት አፌር የውይይት መድረክ አይነቶችን መጥቀስ ይበቃል። እነዚህ ቡድኖች በተለይም በውጭ አገር ያለውን ኢትዮጵያዊ በማደናገር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ሰው እንዳይደግፈው ለማድረግ ይሄ ነው የማይባል አሉታዊ ሚና አውቀውም ሆነ ሳያወቁ እየተጫወቱ ነው።
አማራጭ ሳይሰጡ፣ እነርሱን የሰሩትን የተጨበጠ ነገር ሳያሳዩ፣ በውጭ አገር ተቀምጦ፣ በኢትዮጵያ ከህዝቡ ጋር ተኩኖ የሚደረግን እንቅስቃሴ፣ ትንሽ ትሁን ትልቅ፣ ማንኳሸሹ ይቅርታ ይደረግልኝና ግብዘነትና አሳፋሪ አድርጌ ነው የማየው። (ስለከረንት አፌር ፓልቶክ ክፍል ዘርዘር ያለ ዘገባ፣ እንዲሁም በቅርቡ ምርጫው በተመለከተ፣ መሰረቱ በአውሮፓና በአሜሪካ የሆነውና ከተቋቋመ ሁለት አመት በቅርብ ጊዜ የሚያከብረው፣ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ፣ ላወጣቸው ጠቃሚ ያልሆኑ፣ አፍራሽ መግለጫዎች ምላሽን የያዘ ጽሁፍ ወደፊት ለአንባቢያን እናቀርባለን።)
እንግዲህ የአንድነት ፓርቲ እንዲሁም መድረኩ በዚህ አይነት እሳት ውስጥ እያለፉም፣ በመጪው የ2002 ምርጫ ጠንካራ አማራጭ ሆነው መገኘታቸው በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ ለሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ትልቅ ደስታን ሊሰጥ የሚገባ ነው ባይ ነኝ።
የአንድነት ፓርቲ ያሰበውንና ያቀደውን ከግብ ላያደርስ ይችላል። እንደጠበቅነውና ተስፋ እንዳደረገነው ነገሮች ግጥምጥም ላይሉ ይችላሉ። በድርጅቱ የሚያሳዝኑ ሁኔታዎች ልናይ እንችላለን። መነሳት እንዳለም መውደቅ እንደሚኖር ማወቅ አለብን። የአንድነት ፓርቲ ወድቆ ያወቃል። የሰላማዊ ፖለቲካ ታጋዮች ወደ ኋላ ሄደው ያወቃሉ። ይሄ ሁሉ ያለ ነገር ነው።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ከላይ የተዘረዘሩት ዱላዎች አያረፉባቸውም የአንድነት ደጋፊዎችና አባላት ወድቀው እየተነሱ፣ እጅ ሳይሰጡ፣ ተስፋ ሳይቆርጡ፣ መንቀሳቀስ መቻላቸው በራሱ ትልቅ ድል ነው!! ኢትዮጵያ ተስፋ እንዳላት የሚያሳይ ነው።
አንድ ድርጅት ጥንካሬው የሚለካው ማጥቃት በመቻሉ ብቻ አይደለም። ነገር ግን ሲጠቃም ጥቃትን መመከት በመቻሉም እንጂ።
የአንድነት ፓርቲ እንዲሁም መድረኩ ጥቃትን መክቶ፣ በአሁኑ ወቅት በማጥቃት ላይ ይገኛል። ወያኔ/ኢሕአዴግ በኔ ሥር ያሉ ናቸው በሚላቸው ቦታዎች ከፍተኛ ትንቅንቅ እየተደረገ ነው። የተቃዋሚዎች ማእከል በሆኑት በነአዲስ አበባ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በኢሕአዴግ ማእከል በነበሩ እንደ ትግራይ ባሉ ቦታዎች እንቅስቃሴዎችን እያየን ነው።
እንደዚህም ሆኖ የሚያሳዝነው፣ በውጭ አገር የምንኖረው ኢትዮጵያዊያን፣ በዘጠና ሰባት ያኔ ተቃዋሚዎችን እንደደገፍነው አሁን ድጋፋችንን እያበረከትን አለመሆናችን ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት በዋናነት ተስፋ በመቁረጣችን ሲሆን በሁለተኛነት ደግሞ በውጭ አገር ያሉ አንዳንድ ከተቃዋሚ ወገን ነን የሚሉ በሚያሰራጩት አፍራሽና ተራ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ነው።
ይህ ሁኔታ መቀየር ያለበት ይመስለኛል። ሁላችንም ከስሜት ወጥተን ያሉትን ተጨባጭ ሁኔታዎች ቁጭ ብለን እንድናመዛዝን በአክብሮት እጠይቃለሁ። ቀኙን ግራውን በመመልከት፣ ብዙ የሚያወሩ አሉና፣ እስቲ ሁሉንም በሥራቸው እንመዝናቸው።
ከሌሎች መጠበቅ ቀላል ነው። ሌሎች ይሄን ለምን አያደርጉም ብሎ መተቸት ቀላል ነው። በውጭ አገር ተቀምጦ፣ ወይንም በፓልቶክ በሌላ ስም ገብቶ “የጀግንነት ቃላት ማውራት፣ ዘራፍ ማለት” ቀላል ነው። በቦታው ሆኖ ቢሳካም ባይሳካም ለውጥ ለማምጣት መጣር ግን ሌላ ነገር።
በአገር ቤት የሚደረገው ትግል ብርቱካን ሚደቅሳ ቃሊቲ ያስገባ፣ የወጣት አረጋዊ ገብረዮሐንስ ደም በአድዋ የረጨ፣ የአቶ አያሌውን አጥንቶች በውቁሮ የከሰከሰ፣ ወ/ሮ ገነት ባላቻ በዲላ ከሃያ አምስት አመት ሥራዋ እንድትባረር ያደረገ፣ የአቶ ዳንዔል ወልደገብርኤል የአሥራ ሁለት አመት ልጅን ያሳሰረ፣ ትልቅ መስዋእትነት እያስከፈለ ያለ ትግል ነው። በዚህ ትግል ውስጥ መሳተፍ ጀግንነት ነው። እነዚህ ጀግኖች ድጋፋችን ያስፈልጋቸዋል። እነዚህን ጀግኖች ጀግኖች አይደሉም የምንል ከሆነ ታዲያ ማን ነው ጀግናው? እነዚህን ጀግኖች ካልደገፍን ታዲያ ማንን ነው የምንደግው? አሁን ካልደገፍናቸው መቼ ነው የምንደግፋቸው?
አጠንክሬ የአንድነት ፓርቲ እንዲሁም መድረኩን እደግፋለሁ። በየአለም ዙሪያ ለተበተኑት ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ድጋፋቸውን እንዲለግሱም ጥሪ አቀርባለሁ። ፈረንጆች “Let not the perfect be the enemy of the good” ይላሉ። ሁኔታዎች ፍጹም እንደምንፈልገው ባለመሆናቸው ፊታችንን ከጥሩ ነገር አናዙር ማለታቸው ነው።
ኢትዮጵያ የኢንጂነር ግዛችው ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያ የአቶ ስዬ ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያ የአቶ አረጋዊ ብቻ አይደለችም። ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት።
እነ አቶ መለስ ዜናዊ በአገራችን ጉዳይ ተስፋ ቆርጠን ዝም እንድንል፣ የፈለጋቸውን እያሰሩ፣ የፈለጋቸውን እየገደሉ፣ የሕዝቡን ገንዘብ እየዘረፉ፣ እርስ በርሳችን እያናከሱን፣ ባርያ ሆነን እንድንኖር ነው የሚፈልጉት። “ሰው አለ ነጻነቱ ምንድን ነው” እንዳለች ብርቱካን ሚደቅሳ እኛም ለነጻነታችንና ለአገራዊ ክብራችን ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀት ይኖርብናል። በተራ ወሬዎች የምንሽመደመድ ከሆነ ወገኖቼ የትም አንደርስም።
ትግል ቀልድ አይደለም። ቀበቶዋችንን እንታጠቅ። የኛ የሆነውን እግዚብሄር ሲፈጠረን በጸጋ የተቀበልነውን፣ አምባገነኖች በጉልበት የሰረቁብንን ማንነታችንና መብታችንን እናስመለስ!
እግዚአብሔር ያክብርልኝ!
ግርማ ካሣ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)



