የመለስ ዜናዊ ገደብ አልባነት
ካሕሳይ በርኸ እና ተስፋይ አፅብሃ (የካቲት 26 ቀን 2002 ዓ.ም. / ማርች 5 ቀን 2010)
መለስ የህወሓት 35ኛውን ዓመት አስመልክቶ ሲናገርና በድምፅ ወያነ ትግራይ ጥያቄዎች ቀርበውለት ሲመልስ ልዩ ክብደት የሚሰጣቸው የቅስቀሳ መልዕክቶች አሉ። አንዱ መልዕክት በሃሳቦች ላይ ሳይሆን በሰዎችና ድርጅቶች እንዲሁም በተሸፋፈነ መልክ በህዝብ ላይ ያነጣጠረ አስቀያሚ፣ መጥፎ አርኣያነት ያለውና ባህላችንን የሚበክል ስድብ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በሃሳቦች ላይ ያተኮረ የሚመስል ነገር ግን ሃሳቡ የተቃዋሚዎች መሆኑን ማስረጃ ሳይቀርብለት በእነሱ ያልተባለን እንደተባለ አድርጎ የሚያቀርበው በውሸት ላይ የተመሰረተ ህዝብን የማወናበድና የማስፈራራት ቅስቀሳ ነው።
እነዚህን መልዕክቶች ግልፅ ለማድረግ መለስ በትግርኛ የተናገረውን በቀጥታ በአማርኛ እየጠቀስን እናቀርባለን። የተሸፋፈኑ መልዕክቶቹን ለመረዳት ከቋንቋ እውቀት ባሻገር የህወሓት የቅስቀሳ ስልቶችና የትግራይ ህዝብ ከቅስቀሳዎቹ በለመደው ታሪክ ምን እንደሚረዳ ማገናዘብ ያስፈልጋል።
በዚህ መሰረት መለስ: „ብዙ ሰዎች አንስተኛ ቁጥር ያለው፣ ድሃና ያልተማረ ህዝብ ከሱ በላይ ብዛት ያላቸውን፣ ሃብታም የሆኑትን፣ የተማሩትንና የታጠቁትን ሊያሸንፍ ይችላል፤ የሚል ተመክሮና አስተሳሰብ ስላልነበራቸው በህዝባችን ድል አድራጊነት ሳያምኑ ቆይተዋል።” ይላል።
ደርግ ከትግራይ ህዝብ በላይ ብዛት ስላልነበረው መለስ ከትግራይ ህዝብ በላይ ብዛት እንደነበራቸው የሚጠቅሳቸው ጠላቶች እነማን እንደሆኑ ሳይገልፃቸው ስለሚናገር አድማጩ ህዝብ በውስጠ-ታዋቂ ይረዳዋል የሚለውን ህዝብ እንደጠላት እንዲያይ እየቀሰቀሰው መሆኑ አያጠያይቅም።
መለስ የራሱ አቋም ከተቃዋሚዎቹ አቋም በምን እንደሚለይና የሱ አቋም በምንና እንዴት እንደሚሻል በመግለፅ ፈንታ ልቅ በሆነና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በጎደለው አቀራረብ ተቃዋሚዎችን እንደ ግርድ፣ ገለባና ጉድፍ ሲገልፃቸው: “ህዝባችን በየጊዜው ጉልበቱን ለትግል ነፋስ እያጋለጠ ግርዱንና እህሉን እየለያየ፣ ግርዱን እያንጓለለ እህሉን እንደሚሰበስብ ጠንቃቃ ገበሬ ስለታገለ ድል ተቀዳጅቷል።” ይላል። መለስ አርሶ አደሮችን ለማወናበድ እንደተዘጋጀ ከሚጠቀምባቸው የግብርና ቃላት ያስታውቃል። ህዝቡ የተወዳዳሪዎችን ሃሳብ ሰምቶ የሚፈልገው ድርጅትን፣ ተዋዳዳሪ ግለ-ሰቦችም እንደ ሰዎች የሚያምናቸውን በመምረጥ ፈንታ እነ መለስን በክብር እንደ እህል ሌሎችን በንቀት እንደ ግርድ እንዲያይ ሲቀሰቀስ ህዝቡም መታዘቡ አይቀርም፤ ትናንት ሲደነቁ የነበሩ ዛሬ ከመለስ ስለተለዩ ሲሰደቡ ሲሰማ ነገ አሁን ከሚደነቁት ሌላ ሃሳብ ካመጡ እንደሚሰደቡ ያውቃል። ችግሩ ግን ህዝቡ የተባለውን ያመነ መስሎ የተባለውን ካላደረገ አገዛዙ ምን ሊያደርስበት እንደሚችል ስለሚያውቅ ህዝቡ በራሱ ህሊና ቢመራ ጥቃት እንዳይደርስበት ዋስትና የሌለው መሆኑ ነው።
መለስ ንግግሩን ቀጥሎ: „ዘንድሮ የሚካሄደው የክልልና አገር አቀፍ ምርጫም የዚህ ትግል አካልና ተጨማሪ ድል ሆኖ የሚቋጭ ምእራፍ መሆኑ ምንም አይቀርም።” ይላል። ሙከራው ህገ መንግስቱን አክብረው የሚወዳደሩትን ተቃዋሚዎች በትጥቅ ትግሉ ከነበሩት የትግራይ ህዝብ ጠላቶች ከተባሉት ጋር ለማመሳሰልና ተቃዋሚዎቹ እንደ ጠላት እንዲታዩ የሚደረግ ቅስቀሳ ነው። የትግራይ ህዝብ ደርግን እንደ ጠላት ብዙ የሕይወት መስዋእት ከፍሎ ስለታገለ በአሁኑ የይስሙላ ምርጫ የሚወዳደሩትን ተቃዋሚዎች እንደ ደርግ፣ ስለዚህም እንደ ጠላት እንዲያያቸውና በእነሱ ላይ ድል እንዲቀዳጅ ሲቀሰቀስ አደገኛ የደም መፋሰስ ሁኔታ ይፈጥራል።
ይህንንም ሃሳብ ሲያጠናክር: „የዴሞክራሲያዊ ስርዓታችንና የህዝባችን ጠላቶች የሆኑ ሃይሎች ዘወትር ባልተማረው ህዝባችን ላይ ንቀት ስላላቸው የትግል ግርድን ጥሩ እህል ብለው ሊሸጡለት በመጣጣር ላይ ይገኛሉ። ህዝባችን ግን አቅሙን ለነፋስ እያጋለጠ ጉድፍንና ጥሩውን መለያየት ስለለመደ በዚህ መስክ ለጠላቶቹ የማይረሳ ትምህርት ሊሰጥ የሚችል ህዝብ ነው። አየናችሁ! አዲስ ሸቃጮች ብሎ አሽቀንጥሯቸው ጉዞውን እንደሚቀጥል ላንዲት ቅፅበትም ቢሆን አንጠራጠረም።” ይላል። ተቃዋሚዎቹ የስርዓቱ ጠላቶች ሆነው የስርዓት አመራጭ ካቀረቡ መብታቸው ነው፤ ተቃዋሚዎቹ በሰላማዊ ትግል ላይ እያሉ ህዝቡ እንደ ጠላት እንዲያያቸው መቀስቀስ የቀስቃሹ ፀረ ሰላምነት ያመለክታል። ተቃዋሚ ድርጅቶች ህዝብን እንደሚንቁ መቀስቀስ ርካሽ ውሸት ከመሆኑም በላይ የጥላቻ መንፈስ ለማስፈን መሞከር ነው። ህዝቡ እንደለመደው ለተቃዋሚዎቹ የማይረሳ ትምህርት እንዲሰጥ ማመላከት ህዝቡ ጠላት በሚለው ላይ ያካበተውን ልመድ በተቃዋሚዎች ላይ እንዲፈፅም ተከናንቦ ጥሪ ቀርቦለታል፤ ትእዛዝ ተሰጥቶታል።
በመቀጠልም መለስ: “የስርአታችንና የህዝባችን ጠላቶች ግርዳችንን ተሸክመው በህዝባችን የሰላም፣ የልማትና ዴሞክራሲ ጦርነት ላይ ቀዳዳ ለማግኘት ይፈልጋሉ። ድርጅታችን ቀዳዳ እንደሌለ ስለሚያውቅ የሚያሳስበው ጉዳይ አይደለም። የእነዚህ ሃይሎች የመጨረሻ ዓላማ በኛ ጉድፍ ተከናንበው ድል ለመቀዳጀት ሳይሆን ምናልባት ከሆነላቸው ህዝብን እሰቆጥተው ህዝቡ ከአደባባይ ሙግትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ወጥቶ የጉልበት እርምጃ ወደ መውሰድ ይገባልናል የሚል ነው። (የነሱ) ተስፋ ህዝባችንን እንደነሱ ጭቃ ሊያደርጉት ባይችሉም ጭቃ ሊቀቡት፣ በስሜትና ቁጣ ከዴሞክራሲያዊ አግባብ ወጥቶ እንዲንሸራተትላቸውና ድሉንና ስርኣቱን ጥላሸት እንዲቀቡት ነው።” ይላል። በዚህ አገላለፅ መለስ „ጉድፍ (እንግውላይ)” እያለ የሚያጣጥላቸው ሰዎች በህወሓት ውስጥ መለስ ሲሸሽም ፀንተው የታገሉ ሰዎች ናቸው። መለስ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ማንም መንግስት የማይወያይበት የፈረንሳይ የድሮ የቦናፓርቲዝም ታሪክ (ከ150 ዓመት በፊት የነበረ) ለተለመደው የቅጥፈት ስራው ሲያቀርብ፣ እነሱ በተጨባጭ ጉዳይ ላይ፣ ማለትም ከኤርትራ ጋር የነበረውን ጦርነት መገምገም የፈለጉ ናቸው። „በኛ ጉድፍ ተከናንበው” ሲል ከህወሓት ወጥተው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የተሰለፉትን እንደ ጉድፍ ስለገለፃቸው በጉድፉ እንደተከናነቡ የሚገልፃቸው በህወሓት ውስጥ ያልነበሩ፣ ስለዚህም የትግራይ ህዝብ እንደ ጠላት እንዲያያቸው የሚፈለጉ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ሌላም አለ። ተቃዋሚዎቹ „ጭቃ” ሲባሉ ግልፅ የሚሆነው የእነሱ ጭቃነት ሳይሆን ጭቃ ሰው የለምና፣ ጭቃ ባዩን ያስገምታል፤ አገራችን በምን ዓይነት ሰው እንደምትገዛም ያሳያል። መለስ ህዝቡ „በስሜትና ቁጣ ከዴሞክራሲያዊ አግባብ ወጥቶ እንዲንሸራተትላቸው” ሲል የተቃዋሚዎቹ መወዳዳር ስሜት ይቀሰቅሳል፣ ያስቆጣል፣ በጉልበት ወደ መጠቀም ይገፋፋል የሚል መልዕክት ለህዝቡ እያስተላለፈ ነው። በመለስ መሳሪያነቱ ለሚጠቀምና ስሜቱን ለማቆይጣጠር ሰው በማያስቆጣ ነገር መቆጣቱ ተገቢ እንደሆነ ስለተነገረው ጉልበት ቢጠቀም አይገርምም፤ ድርጅቱን ይወዳል እንዲባል የሚፈልግ ሰው ጠላቱ እንደሆነና ሊያስቆጣው እንደተዘገጀ በተነገረው አካል ላይ እርምጃ ቢወስድ እንደማይቀጣ ያውቃል።
መለስ በየካቲት 11 ካደረገው ንግግር በፊት ከድምፂ ወያነ ትግራይ ጋር በዓሉን የሚመለከት ቃለ መጠይቅ አድርጎ ነበር። መለስ ለተዘጋጁት ጥያቄዎች የሚሰጣቸው መልሶች የመልስ ሰጪው ማንነት ሳይጠቀስ በፅሑፍ ቢቀርቡም ኖሮ ካላቸው የብልግናና የውሸት ይዘት ከመለስ እንደፈለቁና በካድሬዎቹ እንደሚደገሙ ሊታወቁ ይችሉ ነበር። ሰላማዊ ተቃዋሚዎቹን፡ ጥገኛ፣ የቀኝ፣ የበሰበሱ፣ የትምክህትና ጠባብ ብሄራዊ ሃይሎች የደርግና የኦነግ ትርፍራፊዎች ይላቸዋል።
መለስ ተቃዋሚዎቹን ለምን ጥገኛ እንደሚላቸው ለመግለፅ ሲያወናብድ ንዮ ሊበራል እንደሆኑ ይዋሻል። ድርጅቶቹ ግን የሚገልፁት በሊበራል ዴሞክራሲ እንደሚያምኑ ነው። ሊበራል ዴሞክራሲ ደግሞ የህግ የበላይነትና ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች ማክበር ማለት እንጂ የግድ ኒዮ ሊበራል የኢኮኖሚ መርህ መከተልና መንግስት በኢኮኖሚ ጣልቃ እንዳይገባ ማድረግ ማለት አይደለም። በሰለጠኑ አገሮች የኮሚኒሰቶች፣ የሶሻሊስቶችም ሆኑ የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲዎች ኒዮ ሊበራሊዝምን እየተቃወሙ የሊበራል ዴሞክራሲ ፖለቲካ ተግባረዊ ያደርጋሉ። ሊበራል ዴሞክራሲያውያን ሆነው ከይነስያን (Keynesian) የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚከተሉ ስለዚህም መንግሰት በኢኮኖሚ ጣልቃ እንዲገባ እየደገፉ የፍሪድማን/ Milton Friedman/ አይነት (በችሌ በፒኖቸ/Pinochet ፋሽሽታዊ አገዛዝ እንደተደረገው) በሞኒታሪዝም (monetarism) የተደገፈ ኒዮ ሊበራል ፖሊሲ የሚቃወሙ ዴሞክረሲያዊ ፓርቲዎች ብዙ ናቸው። (በነገራችን ላይ ፍሪድማንም ኒዮ ሊበራሊዝም የአምባገነንነት መሰረት እንደሚንድ ገልጿል።) ስለዚህ መለስ በሊበራል ዴሞክራሲና በኒዮ ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ መካከል ልዩነት እንደሌለ አስመስሎ እየዋሸ አድማጮቹን ለማታለል ይሞክራል።
ሌባ ሰርቆ ሊያመልጥ ሲሞክር፣ ሰው ሲከታተለው „ሌባ፣ ሌባ” እያለ እንደሚያወናብድ ሆነ እንጂ በውጭ የባጀት ድጎማ የሚኖረው የመለስ አገዛዝ በስልጣን ላይ የሌሉ ድርጅቶችን ጥገኛ ማለት አልነበረበትም። በዚህ መሰረት መለስ በአንዱ ርካሽ የማወናበጃ ስልቱ ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰው ተቃዋሚዎቹ ለኒዮ ሊበራሊዝም እንደቆሙ አስመስሎ ያቀርባል። አከታትሎ ደግሞ መሬት የግል ሃብት እንዲሆንና መሬቱን የመሸጥ መብት እንዲከበር መደገፍ የኒዮ ሊበራሊዝም ፖሊሲ ብቻ እንደሆነ አስመስሎ ይዋሻል።
እርግጥ ኢንዱስትሪ ባልተስፋፋበት ሁኔታ መሬትን የመሸጥ መብት ቢከበር ድሃ አርሶ አደሮች መሬታቸውን እየሸጡ ወደ ከተማ ሊገቡ ስለሚችሉ የስራ አጥነት ችግር ሊያስከትል ስለሚችል ጉዳት እንደሚያስከትል ሊያከራክር ይችላል፤ መሬት መሸጥን ከኒዮ ሊበራሊዝም ጋር ብቻ ማያያዝ ግን ማጭበርበር ነው። በሌላ በኩል መሬት እንዳይሸጥ በመንግስት መከልከሉ ከቀጠለ ደግሞ በኢኮኖሚ አይን ሲታይ መሬት በዘመናዊ እርሻ እንዳይለማ ስለሚገታ የምርት እድገት እንደቀጨጨ እንዲቀጥልና ረሃብ እንዳይጠፋ ሊያደርግ ይችላል። ድሃ አርሶ አደሮች በተራድኦ ተደራጅተው መሬታቸውን ካለሙና ምርታቸውን ካሳደጉ መሬታቸውን እንዲሸጡ አይገደዱም፤ ተራድኦዎች ብዙ ጊዜ ስለሚፈርሱ ግን የአርሶ አደሮች መሬትን የመሸጥና የማከራየት መብት መጠበቅ አለበት። በፖሊቲካ አይን ሲታይ እንኳንና ፀረ ዴሞክራሲ የከሃዲ አገዛዝ ባለበት ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ባገር ወዳዶች የቆመ መንግስትም በመሬት ላይ ባለው ስልጣን እየተጠቀመ አርሶ አደሮችን ሊቆጣጠርና ሊያስፈራራ ስለሚችል መሬት የግል አለመሆኑ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን ያደናቅፈል።
መለስ ሊበራል ዴሞክራሲ የሚደግፉትን ተቃዋሚዎች አቋማቸውን አጣምሞ ኒዮ ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደሚፈልጉ፣ በዚህም ምክንያት ጥገኞች እንደሆኑ ሲያጥላላ ደጋፊዎችንም እንደሚያታልል አይተናል። ልማታዊ መንግስት ለእድገት ጠቃሚ፣ ባንፃሩ ግን የኒዮ ሊበራሎች መንግስት ጥገኛና ፀረ እድገት መሆኑን ከገለፀ በሁዋላ ራሃብን ያጠፉ ልማታዊ መንግስታት ብሎ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ህንድ፣ ደቡብ ኮርያ ወዘተ… እንደ ምሳሌዎች አቅርቧል። ከቀረቡት ምሳሌዎች ውስጥ ከቻይና በስተቀር እንደ መለስ የሊበራል ዴሞክራሲ መርሆዎችን የሚቃወሙ አይደሉም። ስለዚህ ተቃዋሚ ድርጅቶቹ መለስ በሚለጥፍባቸው ይዘት ሳይሆን በራሳቸው አቋም የእነ ጃፓን ህንድና ደቡብ ኮርያ አርአያነት ሊከተሉ የማይችልበት ምክንያት የለም።
መለስ ተቃዋሚዎችን „የቀኝ” ሲላቸው ባለፈው ታሪክ የግራና ቀኝ ጠላትነት የተማሩት ደጋፊዎቹን ለጥላቻ ያሰልፋቸዋል፤ የቀኝ አክራሪዎች በሌሉበት ሁኔታ ጥላቻ መቅስቀሱ በሰላማዊ ትግል ሃላፊነት ሊሰማው ከሚገባ ሰው አይጠበቅም፤ ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም። ሰዎችን „የበሰበሱ” ብሎ መዝለፍ የዘላፊው ማንነት አጉልቶ ያሳያል። ትምክህተኞች የሚላቸው ልክ በትጥቅ ትግሉ እንደ ጠላት የሚታዩትን ለማስታወስና ቅራኔ ከማራገብ አልፎ ሌላ ፋያዳ የለውም። ሆኖም መለስ ከህወሓት ካስወጣቸው በሁዋላ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር አብረው የሚታገሉትን ሰዎች በትጥቅ ትግሉ ጊዜ ህወሓትን ከድተው ከደርግ ጋር በመሰለፋቸው ምክንያት በህዝብ ተጠልተው እንደነበሩት እንዲታዩ ለማድረግ ይጥራል። ተቃዋሚ ድርጅቶቹን ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ያላቸው ቅራኔ ህወሓት/ኢህአዴግ ከደርግ ጋር እንደነበረው የማይታረቅ ቅራኔ እንዳላቸው ስለሚገልፃቸው ለህዝብና ለአገር ሃላፊነት የሌለው ቅስቀሳ በማጋጋል ላይ ይገኛል። ከመለስና ግብረ አበሮቹ በስተቀር የህወሓት/ኢህአዴግ አባሎች በጥቅል እንደ ወንጀለኛ መታየት እንደማይገባቸው ሁሉ ከደርግና ኦነግ ጋር የሰሩም በጥቅል ወንጀለኞች አይደሉም። መለስ ቅንነት ቢኖረው ኖሮ፣ ከደርግ ጋር ሆኖው ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች ስለታሰሩና ስለተቀጡ፣ በህግ ያልተከሰሱና ህጋዊ ፈቃድ አግኝተው በሰላም የሚታገሉ ሰዎች ወንጀለኞች እንዳልሆኑ ራሱ መለስ መመስከር ነበረበት። ስለዚህ በወንጀል ያልተከሰሱ ኢትዮጵያውያንን በደርግና ኦነግ ስር ስለነበሩ ብቻ በጠላትነት መፈረጁ የቅጥፈት ጠባይ ያመለክታል።
ሁሉም ፍፁም ስልጣን ያላቸው ግለ-ሰቦች እንደ መለስ ልቅ፣ ገደብ አልባ፣ አስፀያፊና ጥላቻ ቀስቃሽ ንግግር አያደርጉም። ስለዚህ ፍፁም ስልጣን ለጊዜው ከቅጣት መከላከያ ከመሆን አልፎ የወራዳ ንግግር ምንጭ ሊሆን አይችልም። ምንጩ ከሰውየው ማንነት ጋር የተያያዘ ቢሆንም ቆሻሻው ደግሞ ካለ ስልጣን ተገን በህዝብ ላይ አይረጭም ነበር። የሰንደቅ ዓላማ ጨርቅነት፣ ወርቅ ስለሚባልና ስለማይባል ህዝብን የመከፋፈል ጋጠ ወጥነት፣ በዓይን ቀለም ሰውን ካገር ማስወጣት እንደሚቻል፣ የአክሱም ሃወልት ለማን ምኑ እንደሆነ ወዘተ…የተባሉ ብዙ ነገሮች አሉ፤ አንዳንድ ጊዜም ሃላፊነት በሚሰማቸው ኢትዮጵያውያን ‚አይባሉም’ የሚባሉ ቃላት መለስን የሚመለከቱ አይመስሉም። መለስ የተወሰኑ የህወሓት አባላትን ከስልጣንና ከድርጅት ሲያባርር የይስሙላው ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ሃላፊ (ሕቡር) ስነ ስርዓት ለማስያዝ ሲሞክር በመለስ ‚ሰገራ’ ተብሎ እንደተሰደበ ብዙ ሰዎች ሰምተውታል።
የገደብ ጥያቄ ከተነሳ መለስ ለስልጣኑ ገደብ ስለሌለው ከ34 ዓመት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሰው ደም ሲጨማለቅ የሚገኝ ወንጀለኛና ለጭካኔው ገደብ የሌለው አረመኔ ነው። መለስ „ወርቅ” እያለ የሚያታልለው ህዝብ በረሃብ እንደ ቅጠል ሲረግፍ ለተራበው ከተሰበሰበው እርዳታ 95% እያሰቀረ ህዝቡ በረሃብ እንዲሞት ወስኗል፤ ይህም ገደብ የለሽ ጭካኔ ነው።
በህወሓት ስልጣን ከነበራቸውና አሁንም ካላቸው ሰዎች ውስጥ በፍርሃት እንደ መለስ ሃፍረተ ቢስ ሰው አለጋጠመም። መለስ ገና ለወታደራዊ ስልጠና በጉዞ ላይ እያለ ካለ ምንም ምክንያት አብረውት ለነበሩት ሳይነግር ከድቷቸውና ጥሏቸው ከአስመራ እንደጠፋ የሚያውቁት ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበሩ። መለስ ከወራት በሁዋላ ተመልሶ ደርግ እንደነቃበትና ህይወቱ ለአደጋ እንደተጋለጠ ገልፆ እንደገና እንዲቀበሉት እነ አረጋዊን ለምኖ ወደ ድርጅቱ ገባ፤ ክዶ እንደነበረም በምስጢር ተይዞለት ሳይጋለጥ ቀረ።
እንደገና አድዋ ላይ ለመዋጋት መለስ የአረጋዊ ምክትል አዛዥ ሆኖ ከገባ በሁዋላ መለስ ውጊያ ማሰተባበሩን ትቶ ማድ ቤት ውስጥ ተደበቀ። ውጊያው ስላልተሳካ እነ ተክለሃይማኖት ገብረየሃንስ (ተኽለ ሸሪፎ) ተሰውተው ሬሳቸው እዛው ስለቀረ የደርግ ባለስልጣኖችም ሬሳውን እንዳይቀበር ከልክለው ውጭ አሰነበቱት። በውጊያው የነበሩ የድርጅቱ ታጋዮች በስብሰባ ላይ መለስ እንዲቀጣ ጠይቀው፣ ስብሓት፡ „እናንተ መለስን እንድንገድለው ፈልጋችሁ ነው፤ እኛ ግን አንገድለውም።” ብሎ ተከላከለለት። ስለዚህ የመለስ ጥፋት በቀላል ቅጣት ታለፈ።
አሁንም እንደገና አረጋዊ በርሀ በደጀን ረድዮ እንደገለፀው በአንድ የዓዲ ዳዕሮ (ሽረ ውስጥ) ውጊያ ላይ መለስ ደንግጦ ለእነ አረጋዊ ጥይት ወደ ራሱ እንደገባች ነገራቸው። የጥይት መግቢያም መውጫም ስላላገኙ ሰውየው ፈርቶ ከቦታው ሊርቅ እንደፈለገ ስለገባቸው እንዲርቅ ፈቀዱለት። ስለዚህ መለስ ለፍርሃቱና ከመጠን ላለፈ ራስ ወዳድነቱም ገደብ ስለሌለው አብዛኛውን የትጥቅ ትግል ጊዜ ከሞት አደጋ ርቆ አሳልፎታል። እዚህ ላይ ራስ ወዳድና ፈሪ ሰው በሌሎች ህይወት ላይ ጨካኝ መሆኑ ግራ የሚያጋባ ይመስላል፤ ለህይወቱ ከመጠን በላይ የሚፈራ ሰው እንዴት የሌላ ሰው ፍርሃትና ጭንቀት መረዳት አይችልም ሊያሰኝ ይችላል። ችግሩ ግን ከመጠን በላይ የሚፈራና ራሱን የሚወድ ሰው አደጋ በሌለበት አደጋ ስለሚያይና የተለየ ሃሳብ ያለው ሁሉ ስልጣኑን የሚነጥቀው፣ ጥቅሙን የሚያሳጣውና የሚገድለው ስለሚመስለው ሊቀድሙት ያላሰቡትን ሰዎችንም ሳይቀድሙኝ ልቅደማቸው እያለ የማያምናቸውን ሰዎች የማጥፋት ስነ ልቦና እንዳለው የሚያመለክት ክስተት ነው። በሚፈፅማቸው ወንጀሎች ምክንያት እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ የሚገነዘብ ሰው (አሁን ለመለስ የሚደረግለት የተጋነነ ጥበቃም ይህን ያመለክታል) ካለ በቂ ምክንያት ተሸብሮ ስለሚኖር ካለ በቂ ምክንያት አሽብሮ ለሞኖር በሚጠረጥራቸው ሰዎች ላይ ግፍ ከመስራት አይቆጠብም።
ኢሕአዴግ እንደ ድርጅት ይጠፋል
ፍፁም ስልጣን ይዘው፣ ህዝብን አሽብረውና ከፋፍለው፣ በወንጀልና ሙስና ተዘፍቀው፣ እየዋሹና እያጭበረበሩ የሚገዙ ገደብ አልባ ቡድኖች ሲደመሰሱም ሙሉ ለሙሉ፣ በፍፁምነት እንደሆነ የኢሰፓ፣ የናዚዎች፣ የፋሽስቶች፣ የክመር ሩዥ (Khmer Rouge/Cambodia) ወዘተ ታሪክ ይመሰክራል። ኢሕዴግም እንደ ድርጅት ይጠፋል፤ ከዚህ የታሪክ ሂደት አያመልጥም፤ ፍፃሜው የጊዜ ጥያቄ ብቻ ነው።
የመለስ አገዛዝ በፍላጎቱ በድርጅቱ ውስጥም ይሁን በህዝብ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ እንደማይፈቅድ ለ34 ዓመታት ተደጋግሞ ተረጋግጧል። „ምርጫ” በተባለ ቁጥር የተቃዋሚዎችና ደጋፊዎቻቸው እንግልት፣ እስራትና ግድያ ተለምደዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ማንንም ለማጥቃት ሳይሆን ራሱን ለመከላከልና መብቶቹን ለማስከበር በቁጣ ተነስቶ ማንም ዜጋ በፖለቲካዊ አቋሙ ምክንያት የዜግነት መብቱ እንዳይነፈግ፣ እንዳይታሰር፣ አንዳይዛትበት፣ እንዳይዋከብ፣ እንዳይደበደብና እንዳይገደል መቃወሙ አይቀርም። ኢሕአዴግ እንደሚያጨበረብር ስለተነቃበት ተንቋል፤ ተጠልቷል። አገዛዙ ስለጣኑን የያዘውም እስካሁን ያቆየውም በዋናነት በጉልበት ስለሆነ በመረጠው የትግል ስልት ከስልጣንም ከፖሊቲካ መድረኩም ይወገዳል።
ካሕሳይ በርኸ እና ተስፋይ አፅብሃ
የካቲት 26 ቀን 2002 ዓ.ም. / ማርች 5 ቀን 2010



