Dorowaኩችዬ - መጋቢት 1 ቀን 2002 ዓ.ም. (ማርች 10 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.)

ሹም መሆን ብዙ ፈተና አለው ወዳጄ! አንዲት አነስተኛ ወረዳ ውስጥ አስተዳዳሪ ሆኖ የተመረጠ ሰው የህዝቡን ተሳትፎ ለማግኘት ቁርጥ ሃሳብ ያደርጋል። የነጋዴው፤ ያስተማሪው፤ የተማሪው፤ የገበሬው በር አልቀረውም። የሁሉንም አንኳኳ። አንዱን ቀን እግሩ ካንድ ገበሬ ቤት ይጥለውና ... 

 

 

“የዛሬው አመጣጤ አንድ ኮሚቴ ውስጥ በአባልነት እንዲሳተፉልኝ ለመጠየቅ ነው” ይላል አስተዳዳሪው።

 

“ምን ገዶኝ ጌታው! ታዲያ ተሳትፎዬን የሚፈልጉት በምን መልክ ነው? የዶሮዋን ዓይነት ነው ወይንስ የበሬውን ዓይነት?” ጥያቄውን በጥያቄ ይመልሳል - ገበሬው።

 

አስተዳዳሪው በገበሬው ጥያቄ ግራ ተጋባና፤ ደግሞም ገበሬዎች የአግብኦና የተምሳሌት ጨዋታ እንደሚወዱ ያውቅ ነበርና ፍችውን ለማግኘት ጉጉት አደረበት።

 

“አልገባኝምና እንዲያው ጥቂት ቢያብራሩልኝ” ይለዋል ገበሬውን፤ መልሱን ለማዳመጥ ትጋቱን አሰባስቦ።

 

“አይ! ተሳትፎ ማለት ሥጋ ጣል-ጣል እንደተደረገበት የንቁላል ጥብስ ነው ... ዶሮዋ ለጥብሱ አስተዋጽዖ ታደርጋለች እንጅ ራሷን አሳልፋ አትሰጥም” በማለት እንቆቅልሹን ፈታለት - አያ ገበሬ።

 

ይችን ጨዋታ ያካፈለኝ አንድ እጁ ከመጽሐፍ ሌላኛው እጁ ደግሞ ከላፕቶፕ ገበታ ላይ የማይነሳ ሌላው ወዳጄ ነው። ይንግሊንግ ቢራችንን (ይሄኔ እኮ ያሜሪካ ቀዳማዊ ቢራ መሆኑን የማታውቁ ትኖራላችሁ!) ጨብጠን በሌላ ርዕስ ላይ ገራ-ገር ጨዋታ ስንሰልቅ ነው አንቀጹን ያነበበልኝ። አጉል ልማድ አይለቅምና ሃሳቤ እንደገና ወደኛው ጉዳይ አቀና ...

 

ስንቶቻችን ነን የዶሮዋን ያህል አስተዋጽዖ እያደረግን ያለነው? ስንቶችስ ናቸው የበሬውን ያህል ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት የቆረጡ?

 

“ሠላማዊ ትግል” በሚለው አንቀጽ ውስጥ “ሠላም” የምትለዋ ቃል አዘናጊ ሆና ትታየኛለች - በዚህ ጎራ የሚታገሉ ዜጎችና ቤተሰቦቻቸው ያለችግርና በሠላም ውለው የሚያድሩ ታስመስላለችና። እውነቱ ግን ይህ አይደለም። በሙሉም ይሁን በከፊል አዱኛቸውን እርግፍ አርገው የሚጥሩ ሁሉ ችግር ይኖራቸዋል። ፓርቲዎቹስ ቢሆኑ ከየት በመጣ ገንዘብ ነው ከክልል ክልል ተዘዋውረው በምርጫው የሚወዳደሩት? ህዝቡስ ጋር የሚገናኙት?

 

በርግጥ ከመንግሥት የሚሰጥ በጀት እንዳለ ሰምቻለሁ። ግን ዘጠኝ ሺህ የኢትዮጵያ ብር የት ታደርሳልች? አባባሌ ሀገር ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችን መደገፍ የዜግነትና የህሊና ግዴታ አለበት ለማለት ነው። የዚህ ወይንም የዚያ ፓርቲ ደጋፊ መሆናችን አይደለም ቁምነገሩ። ለሀገራችን ዲሞክራሲንና ሠላምን የምንመኝ እስከሆነ ድረስ ለዚህ ለግንቦት 2002ቱ ምርጫ የሚረዳ አሥርና ሃያ ብር ለሚመስለን ፓርቲ ማዋጣቱ ላይ ነው።

 

ዶሮዋ ዕንቁላሏን ከቸረች እኛ ከማኅፀናችን ያልወጣው $20 ዶላር ይገደናል? ቢያንስ ዶሮዋን እንሁን!


ኩችዬ - መጋቢት 1 ቀን 2002 ዓ.ም.

Can we be the goose?

March 10, 2010

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

www.kuchiye.blogspot.com

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ