ይሁዳ …

ሠላምታ 5 / Selamta5 /

ይሁዲ ይሁዲ ይሁዳ

ሰተት ብሎ ገባ ከወያኔ ጓዳ።

 

ስንቱ ተበተነ ስንት ደም ፈሰሰ

እንደወጣ ቀርቶ ስንት ቤት ፈረሰ።

ስንቱ ልጁን አጣ ስንቱ ተሰደደ

ተኩላው ለምድ ለብሶ ስንቱን አስማገደ።

በሕፃናቶች ደም የጨቀየው መሬት

ገና መች ደረቀ ሊገባ ምክር ቤት።

እንዴትስ ተረሱ ነብዩ … ሽብሬ

ትላንት የተሰዉት ለኢትዮጵያ ሀገሬ።

አሎሄ ኤሎሄ … አምላክ ተፋረደን

ድብቁ ይሁዳ በአደባባይ ሸጠን።

 

ይሁዲ ይሁዲ ይሁዳ

ሰተት ብሎ ገባ ከወያኔ ጓዳ።

 

ብርቱካን ስትለምን አደባባይ ወጥታ

ጋሼ፣ አባባ እያለች ስትጠይቅ ይቅርታ።

ጆሮ የነፈጋት ድብቁ ይሁዳ

ሰተት ብሎ ገባ ከገዳዮች ጓዳ።

የሽብሬ እናት እሪ በይ ለአምላክሽ

የነብዩ እናት አምላክ ይፍረድልሽ።

ዛሬ ተወዳጀ ይመራኛል ያልሽው

የልጆችሽን ደም ትናንት ካፈሰሰው።

አምላኩን የሸጠ በሠላሳ ብር

ከሃዲው ይሁዳ ወጣ ከመቃብር።

 

ይሁዲ ይሁዲ ይሁዳ

ሰተት ብሎ ገባ ከወያኔ ጓዳ።

 

የምን ማቆላመጥ የምን አንቱ አንቱ

ደግሞ ለይሁዳ ለዚህ የሰው ከንቱ።

እሱ መች ታሰረ መች ቃሊቲ ገባ

ሆስፒታል እያለ ሲወጣ ሲገባ

ታሪክ ምስክር ነው ስናየው ዞረን

ድብቁ ይሁዳ ስንቴ ገደለን?

ቅንጅት እንዳይፈርስ የሸመገላችሁ

ውጡና ንገሩን ማን አሳፈራችሁ?

ይቅር ለመባባል ልቡ የጨከነው

ዛሬ ከገዳይ ጋር ምን አንድ አደረገው?።

 

ይሁዲ ይሁዲ ይሁዳ

ሰተት ብሎ ገባ ከወያኔ ጓዳ።

 

ዛሬ ባይኖርም የተሰዋው አስራት

የመአህድ አባሎች ያላችሁ በሕይወት

መስክሩልን እንጂ የይሁዳን ገድል

ስንቴ እንደገደለ የኢትዮጵያን ህዝብ ትግል።

ታላቁ አስራታችን ሲሰዋ በክብር

እሱ መች ነበረ ከጓዱ መቃብር።

ዛሬ ተመልሰን ስንቃኝ ትናንትን

ይሁዳ ሰንብቷል እኛን ሲበታትን።

እውነትና ብርሃን ይጠራል እያደር

ድብቁ ይሁዳ ተገለጠ ለሀገር።

 

ይሁዲ ይሁዲ ይሁዳ

ሰተት ብሎ ገባ ከወያኔ ጓዳ።

 

በደም ሚነግዱ ለግል ጥቅማቸው

በሰማይ በምድር ምህረትም የላቸው።

አሉ ያደፈጡ ብዙ ይሁዲዎች።

ለምድ ያጠለቁ የሚመስሉ በጎች።

ተግባርና አፋቸው ፍፁም ማይጣጣም

ነቅተህ ጠብቃቸው ያቆስሉሃል ነገም።

አሁን ነው ጊዚያቱ የምንወስንበት

አማራጩን መንገድ ለውጥ ሚመጣበት

የነገን ኢትዮጵያ ዛሬ ለመገንባት

አንድ ነው መንገዱ በተግባር መነሳት።

 

ይሁዲ ይሁዲ ይሁዳ

ሰተት ብሎ ገባ ከወያኔ ጓዳ።

 

ኦሮሞ፣ ሱማሌ፣ የሲዳማ ኣርነት

የአርበኞች ግንባር፣ የአፋሮች ሕብረት

በምሥራቅ በምዕራብ በሰሜን ያላችሁ

በደቡብ ኢትዮጵያ ግፍ ያስመረራችሁ

ቆመናል ምትሉ ለህዝብ ነፃነት

ጊዜ አታባክኑ ይፋጠን ውይይት።

ስንት እንባ ፈሰሰ ስንት ደም ገበርን

ቅንጅት አጥተን ነው ወያኔ ሚፈጀን።

በእኛ ላይ ይቁም አይለፍ ለትውልድ

ለሁሉም የሚበጅ እናመቻች መንገድ።

 

ይሁዲ ይሁዲ ይሁዳ

ሰተት ብሎ ገባ ከወያኔ ጓዳ።


 

ሠላምታ 5 / selamta5 /

ከከረንት አፌርስ

በርን - ስዊዘርላንድ

ጥቅምት ፳፬ ቀን ፳፻፪ ዓ.ም. ኖቬምበር 03/2009

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ