“አትጥሪኝ! ... አልመጣም!” (ፊልጶስ)
“አትጥሪኝ! ... አልመጣም!”
ፊልጶስ - ከሆላንድ
እባክሽ፣ “አትጥሪኝ! ... አልመጣም!”
“ድረስልኝ!” አትበይ - አልደርስልሽም፤ …
ስደተኛው ልጅሽ ነኝና ባለዕዳ
አሳድሬዋለሁ ነፍሴን ለስጋዬ፣ ስጋዬን ለባዕዳ።
“ልጄም” አትበይ፣ የልጅ ወግ የለኝም
ያ’ንችን ማንነት በ’ኔ ላይ አታገኝውም፤
አየሽ እናታለም! …
ዕምነት - ነፃነቴንም፣ ሰርዤ - ደልዤ ሸጨዋለሁ
ሠለጠንኩ ስል “ሰይጥኘ” አወኩ ስል “ደንቁሬያለሁ”።
እርግጥ ነው … እንዲህ አንችንም የወላድ መካን አድርጌ
እኔም በቁሜ እየሞትኩ ከምኖር ሁሌም አደግድጌ፤
ማንነቴን አስገፍፊ፣ በተመፅዋችነት ከማድር
መሳለቂያ አድርጌሽ፣ ማዕረግሽን ከማስደፍር፤
ያኔ ካ’ብራክሽ ውስጥ ሳለሁ፣ ገና ደም እያለሁ
ይሻል ነበር … ሳልፀነስ “ውሀ” ሆኘ በቀረሁ።…
ወይም “ባስወረደሽ” ቀኔ ሳይደርስ
በተቀበርኩ … ሳላነጥስ - ሳላለቅስ፤
“እቅ” ብላ በተዘጋች እስትንፋሴ
ሞቴን ሳላውቅ ባለፈች ነፍሴ። …
ይኸም ቀርቶ …
ባይሆን ጣረ - ነፍሴ በዝቶ፤
ሰናይ ከእኩይ ሳለይ፣ በየዋህነቴ
ማተብ ሳታስሪ ለእምነቴ፣ ተስፋ ሳታደርጊ በልጅነቴ
ሳልጠራሽ ብዬ “እናቴ” … ያኔም ባለፈች ሕይወቴ።
ታዲያማ … ጊዜ የማያሳየው ምን ጉድ አለና
“የማይሆነው ሆነና፣ የሚሆነው ሳይሆን ቀረና”፤ …
የተራበን አብልቶ፣ የተጠማን አጠጥቶ
የታረዘን አልብሶ፣ የወደቀን አንስቶ
የደከመን አቃንቶ፣ የፈረሰን ገንብቶ፤
ላጠፋው ይቅርታ ጠይቆ፣ ለተበደለው ይቅርታ ሰ’ቶ
እንደ እሚያስከብር ወገኑን፣ በስሙ አስጠርቶ፤
እንደሚታገል ለሰው ልጆች እኩልነት
እንደሚቆም ሁሉ ለፍትህ - ለአንድነት፤ …
ልጅ ወልደሽ “ልጄ” ስትይኝ ሰምቼሽ
ያፍ ዳገት የለውምና እኔም “እናቴ” አልኩሽ።
ምነው ያኔ “እናቴ” ብዬ በአንደበቴ ስጠራሽ
እንደ ሎጥ ሚስት የድንጋይ ጨው ሁኘ በቀረውልሽ
እያለ የሌለ “ልጅ” ብለሽ፣ ከምትኖሪ ተስፋ አድርገሽ። …
እናማ ያኔ “እናቴ” ብዬ ስጠራሽ፣ ሸፍጠኝነቱ ጀመረኝ
ቃል ‘እየበሉ’ ማደጉ፣ ክህደትን መላበሱ ተዋኻደኝ።
ችግር አድርጎሽ ወደቡ፣ አዳራሹን ገንብቶብሽ
ከያቅጣጫው ከቦ ‘በደቦ’ ሲያዋክብሽ፤
እንደ እንቧይ ካብ ስትናጅ፣ እያደርሽ ስትፈራርሽ
ማንም እየተነሳ እንደ ሰንበቴ ዳቦ ሲቀራመትሽ
ከሀገር - ሀገር ሲያስተጋባ ጥሪ - ነጋሪትሽ፤
“ኤሎሄ! ኤሎሄ! … ላማ ሰበቅተኒ?” የልጅ ያለህ ስትይ
ስትማፀኝ - ስትማለይ፣ በምድር በሰማይ፤ …
መቼ ደረስኩ ለጥሪ - ለዋይታሽ?
መቼ በልጅ ወግ - ማዕረግ ታደኩሽ?
ኧረ! … ዛሬም ቀኑ ጨርሶ ሳይጨልም፣ ሲመሽ ነቅቼ
ጥሪሽን ሰምቼ፣ ከጉያሽ ተገኝቼ፤ …
“ሲገመድ መገነዣሽ፣ ሲቆፈር መቃብርሽ”
ደርሼ ባስታመምኩሽ፣ ሕመምሽን በታመምኩልሽ፤
ያንችን ውድቀት - እኔ በወደኩልሽ
‘ርሀብሽን - በተራብኩልሽ፣ ‘ርዛትሽን በታረዝኩልሽ
ስቃይሽን ተሰቃይቼ - ሞትሽን በሞትኩልሽ።
አለያም …
“ልጅ” ተብሎ እስካለ በዚ’ች ዓለም፤
ወገብ - አንጀቱን አስሮ፣ ጥሮ - ግሮ
አዕምሮውን ስሎ፣ ወጥሮ - ተወጣጥሮ፤
ግዴታ ኃላፊነቱን፣ የድርሻውን ተወ’ቶ
ልጅ ለእናቱ ያ’ቅሙን ሠርቶ፣ ግን ሳይሆን ቀርቶ፤ …
አስታሞ የቀበሩት …
አልቅሶ የሸኙት፤ …
ከምንም የማይሻል የለም፣ መቼም ይሻል ነበር
እኔ ግን ከምንም አይደለሁም፣ ልጅ አለኝ ስትይ በምድር።
አየሽ እናታለም! …
የአ’ች እኮ … ውድቀትሽ ብቻ አይደለም የሚያሳዝነው
ከውድቀትሽ ለማትረፍ የሚደረግ ጥረት አለመኖሩ ነው
ዓለምን አስደምሞ፣ እጅግ አድርጎ የሚያስገርመው።
“ላም ወልዳ እንዳትልሰው ፈጃት
እንዳትተወው ልጅ ሆነባት”፤ …
እንደሚባለው ሆኖ ምስጢሩ፣ እናት ሆነሽ ባይቆርጥልሽም
“ቁርጥ ያጠግባል” ቁርጡን ልንገርሽ እኔ አልጠቅምሽም።
እናም … እኔን ልጅ ብለሽ “ልጅ አለኝ” አትበይ በዚች ዓለም
እንደሙት እርሽኝ፣ አጠፋውሽ እንጅ አላለማውሽም።
ይልቅስ … ድንኳን ጣይ
ንፍሮ ቀቅይ፤ …
ጥሪ ጉረቤት፣ ዘመድ - አዝማድ
ደረት ይመታ ሙሾ ይወርድ። …
ሰልስተ - ሰባቴን፣ አርባ ሰማኒያየን
ደግሽ ድግስ፣ ፍሪዳ ጣይ፣ አውጭ ተስካሬን፤
ዲያቆናት - ካህናት፣ ቄሱ - ቀሳውስቱ
እየተማለዱ በታቦተ አርባ አራቱ፤
ላልደረስኩልሽ ለተማፅኖሽ፣ ላልታደኩሽ
ሁለተኛም የ’ኔን አይነት ልጅ እንዳይሰጥሽ
ፀሎት አስይዥ፣ ፍታት አስፈች ይፍቱልሽ። …
“የእሳት ልጅ አመድ” እንዲሉ
“ራሱን ያልሆነ፣ ፈረንጅ አምላኩ” እያሉ
ማህሌት ይቁሙ ይማልሉ። …
አየሽ እናቴ! …
እርም ስትበይ አትኑሪ፣ አውጭ እርምሽን
አድርጌሻለሁና ተምፅዋች፣ ተንበርካኪ ለባዕዳን።
ስለዚህም እናታለም! ... እኔን የፀነስሽባት ያች ቀን
ፃዲቁ ዕዮብ እንዳለው፣ “ከቀኖች ሁሉ የተረገምች ትሁን!”
ከቀመር ገብታ አትቆጠር፣ ትጨልም አትይ የቃንቄ ብርሃን። …
እናም … እባክሽ፣ “አትጥሪኝ! ... አልመጣም!”
“ድረስልኝ!” አትበይ - አልደርስልሽም፤ …
ስደተኛው ልጅሽ ነኝና ባለዕዳ
አሳድሬዋለሁ ነፍሴን ለስጋዬ፣ ስጋዬን ለባዕዳ።
እርግጥ ነው … አምላክሽ ፈፅሞ አይጥልሽም
ይዘገያል እንጅ፣ ይመጣል የአንች ዓለም።
ይብላኝ እንጅ ለ‘ኔ
ይስጠኝ እንጅ መጥኔ፤ …
እየሞትኩ! እየሞትኩ! እየሞትኩ! … ለምኖር
ለካድኩት ራሴን፣ በውርደት ለማደር።
አንችስ ይኖርሻል - ትወልጃለሽ ልጅም
ኑሮ እሚያስከብርሽ የሚሞት በአንች ስም።
የማያልፍ የለም፣ ይህም ያልፋልና
ይዘከር ይሆናል የአንችም ክብር ዝና።
አንድ ቀን! … አንድ ቀን!
ማን ያውቃል የነገን።
ፊልጶስ - ከሆላንድ
መስከረም 2002
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



