የሌለንን አለን አንበል (ትንሣዔ)
የሌለንን አለን አንበል
ትንሣዔ
በጥንቱ ዘመን ኩራት ... በሀሜት በአሉባልታ፣
በፈርቶ መኖር ብልጠት ... በመንደር ወሬ ውትወታ፤
ተሳሳትን ማለት ስለማንወድ ... መጯጯህ ነው ሁካታ።
ሁለት ስንሆን መናከስ ... ሦስት ስንሆን መጨፋጨፍ፣
ተማርን አልተማርን ... ትዕግስት እንደሁ የለን መተላለፍ።
አንዳች የለንም ብልህነት ... የግብረ ጉንዳንም ጉልበት፣
ረብሻና ግርግር ነን ... እምንቦጫጨቅ በሰፈርንበት።
ኩራት ደግ ቢሆንም ... ማግሳት እየተራቡ፤
የሆድን ሆድ ይፍጀው ... ብለው ገበና ባያስነብቡ፣
በተናጠል ትልቅ እንጂ ... በህብረት ግዙፍ አልሆንም፣
የሌለንን አለን አንበል ... ነበረን ያልነውን በመድገም።
ጥፋት በሀገራችን ... እንዲህ ሞልቶ ከተረፈ፣
አጠፋሁ ያለን ማነው ... እውነቱን ነግሮን ያለፈ?
ግር ብሎን ... ምን ከማን እንደሚጠየቅ፣
ለመጠየቅም ቸኩለን ... ተራ ደርሶም እንዳንጠየቅ፤
እንዲሁ የነገር ቅመም ... ስንደልዝ ስናሰጣ፣
እንደ ክረምት ወራት ስጥ ... ስናስገባ ስናወጣ፤
ደርቆ ላይደርቅ ነገራችን ... አብቅሎ ብቻ ሻጋታ፣
የኛ ነገር እንዲሁ ... ሁካታ ብቻ ነው ጫጫታ::
ውስጣችን ወና ሲሆን ... ምርኩዝ ካልሆነ እውቀቱ፣
ብቻውን ያወቀ የት ሊደርስ ... መባዘን ነው እኮ ከንቱ።
በተናጠል ትልቅ ብንሆን ... በህብረት ግዙፍ አልሆንም፣
የሌለንን አለን አንበል ... ለቁምነገር አልበቃንም።
ጀግኖችማ ሞልተውናል ... በተናጠል በነብስ ወከፍ፣
በህብረት ግን ፈሪዎች ነን … እርስ በርስ መጠላለፍ።
ጠቢብ እምንባል ተወድሰን ... ባዳ መሀል ነው ስንሰደድ፣
አዋቂ እምንባል ተሞግሰን ... በሰው ሀገር ነው እምንወደድ።
ቡድን ስንሆን ተጠላልፈን ... መቋሰል ብቻ መነካከስ፣
አንዱ የቋጠረውን ... ሌላኛው አድብቶ የሚበጥስ።
ከአምና ዘንድሮ ካልተሻለ ... የወረት ፍቅር ነግሶ፣
በውሀ ቅዳ ወሀ መልስ ... ያብቃለት እንዴ አገር ፈርሶ?
ኩራት ደግ ቢሆንም ... ማግሳት እየተራቡ፤
የሆድን ሆድ ይፍጀው ... ብለው ገበና ባያስነብቡ፣
በተናጠል ትልቅ እንጂ ... በህብረት ግዙፍ አልሆንም፣
የሌለንን አለን አንበል ... ነበረን ያልነውን በመድገም።
ባለንበት ነው የምንረግጥ ... ትንሽ እንኳ እልፍ አላልንም።
ትንሣዔ
ጥቅምት ፳፻፪



