በደል ይረሳል ወይ? (ወለላዬ)
በደል ይረሳል ወይ?
ወለላዬ ከስዊድን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
በደል ይለመዳል? ግፍስ ይረሳል ወይ?
እናዳምጠው እስቲ ምን ይላል ተበዳይ
ምን ብሎ ይረሳል እንዴት ይለመዳል?
አይጠፋም ከአዕምሮ ክፉ እኮ ነው በደል።
የተወጋ አይረሳም! ቢረሳም የወጋ፣
አካል ተመርዞ ተቆጥቶ ሥጋ
ወያኔ ከመጣ ከገባ ጀምሮ፣
እንደክፉ ጠላት ሀገር ምድሩን ወሮ፣
አጋድሞ እየጋጠን፤ እየመጠጠ ደም፣
በገዛ ምድራችን አሳጥቶን ሠላም፣
ሀገር ቆርጦ ጥሎ በፊርማው አጽድቆ፣
እንዴት ይለመዳል? በደሉ ተንቆ።
ያደረሰው በደል አይረሳም ከቶ፣
ህዝብን አፈናቅሎ መኖሪያ አሳጥቶ።
አያሌ ምሁራን አባሯል ከሥራ፣
መች ያልቃል ጨርሶ በደሉ ቢወራ
በደል አይረሳም ግፍም አይለመድ!
የሀገር ጠላትን ተባብረን እናውርድ።
በደል ይረሳና ግፍ ይለመዳል ወይ?
ምን ይላል? እናዳምጥ ሌላውስ ተበዳይ
አይጠፋም ከአዕምሮ ክፉ እኮ ነው በደል።
ምን ብሎ ይረሳል! እንዴት ይለመዳል?
ከፋፍሎ እያባላ በቋንቋ በጎሣ፣
በደሉ ብዙ ነው አይችልም ሊረሳ
እንዴት ይለመዳል? ምኑ ደህና ሆኖ?
እንደዚህ አብግኖን አሳጥቶን መቅኖ
የፖለቲካ ሰው ነፃ ጋዜጠኛ፣
እየተጠበቀ በዓይነ ቁራኛ፣
ፍርድና ዳኝነት መብትና ነፃነት፣
ተገፎ ከህዝቡ ሲሰቃይ ሲያቃትት፣
ተረግጦ ሲገዛ ዓይኑ እያየ የግድ፣
እንደምን ይችላል? በደልን ሊለምድ?
ያሻውን ያረገን አስራ ዘጠኝ ዓመት፣
ወጣት ሽማግሌን የጣለን በጥይት፣
በሕይወት ያለ ሰው የፈለገው ፍጡር፣
መብት ያጣ የወጣ የተነፈገ ሀገር፣
መበደሉን ሊለምድ አይችልም ሊረሳ፣
እስትንፋሱ ቆሞ ካልተባለ ሬሳ።
ምናልባት ምናልባት ይሄንን የሚክድ፣
በደል የሚረሳ ግፍን የሚላመድ፣
ያደረ ብቻ ነው፤ የተገዛ በሆድ
በደል ይለመዳል? ግፍስ ይረሳል ወይ?
አንችስ ምን ትያለሽ? ሴቲቷ ተበዳይ
ምን ብሎ ይረሳል! እንዴት ይለመዳል?
አይጠፋም ከአዕምሮ ክፉ እኮ ነው በደል
እንኳንስ እንደዚህ ሀገር የበደለ፣
ሕግን አመካኝቶ ህዝብን የገደለ፣
ድንጋይም ትዝ ይላል ጥፍርን ከነቀለ።
መታሰር ይቅርና መገፋት መደብደብ፣
ከጩቤ ይብሳይ ይባል የል ወይ? ስድብ
በደል አይረሳም የለውም ጥያቄ፣
ግፍ አይለመድም እንዳበሻ አረቄ
ይልቅ ዋናው ነገር ትልቁ ቁም ነገር፣
በዳይን መጣል ነው ከራስ ላይ ማሽቀንጠር።
አለዛ ፍራቱ በደሉ እየባሰ፣
ያድራል በየቀኑ ሰው እየጨረሰ
በበደል ላይ በደል ደርቦ ደርቦ፣
አጥንት እንዳገኘ እንደ ጉንዳን ከቦ፣
ከጣመኝ ሕይወት ላይ አትንኩኝ ጨርሶ፣
እያለ ሊቀመጥ ዘላለሙን ነግሦ፣
ፈላጊ በዳይ ነው መበደል የሚለምድ፣
አናት ላይ ከወጣ ከሰፈረ እማይወርድ
ለሱ አይሰማውም መበደሉ ጭራሽ፣
አንዴ ከጀመረ ከሆነ ደም አፍሳሽ
እኛ ግን አንችልም በደልን ልንለምድ፣
ትንፋሻችን ቆሞ መቃብር ሳንወርድ።
እርስዎስ አባቴ ቁጭ ያሉት እዛ ላይ፣
በደል ይለመዳል? ግፍስ ይረሳል ወይ?
ምን ብሎ ይረሳል? እንዴት ይለመዳል?
አይጠፋም ከአዕምሮ ክፉ እኮ ነው በደል
በደኖና ወተር በቁም ገደል ከቶ፣
አርባጉጉ አቃጥሎ ሰውን በር ዘግቶ
ሥልጣን ይቀሙኛል ያላቸውን ሰዎች፣
እስር ቤት አጉሮ የኦሮሞ ልጆች፣
የአኝዋክን ጎሣ ከቀያቸው ዘልቆ፣
ጨፍጭፎ እየጣለ በደም አጨማልቆ፣
ገዳዮች አስታጥቆ ልኮ ከሲዳሞ፣
ንጹኀን የፈጀ መንገድ ላይ አቁሞ፣
ሻኪቾ ከፊቾ በግጭት አሳቦ፣
በአውቶማቲክ ጥይት የጣለን ደራርቦ፣
እስከነቤታቸው ኦጋዴን በዶዘር፣
የጨረሰን ጨካኝ እንዳይተርፉ ለዘር፣
ማንም ሰው ሊረሳ አይችልም ፈጽሞ፣
እስትፋስ ሳይከዳው ነፍስ እያለው ቆሞ።
አይገኝም ጭራሽ ይሄንን የሚለምድ፣
ይልቅስ ተባብረን አጥፊን እናስወግድ
በደል ይለመዳል? ግፍስ ይረሳል ወይ?
ምን ይመልሳሉ ዶክተር በዚህ ጉዳይ።
እንደምን ይረሳል? እንዴት ይለመዳል?
አይጠፋም ከአዕምሮ ክፉ እኮ ነው በደል
እንኳን ሰው ይቅርና የረገጠ ፈረስ፣
ሲረገም ይኖራል ጥፋቱ ሲታወስ
በደሉን አይረሳም ቂም ይይዛል ደሃ፣
ትኋኑን ያጠፋል አፍልቶ ሙቅ ውሃ
በቅማል በቅጫም ተወሮ ሲያስቸግር፣
ተላጭቶ ይጣላል የሚወዱት ፀጉር
እየጠዘጠዘ የፈጠረ አደጋ፣
አላስበላም ያለ አላሳኝክ ስጋ፣
ተነቅሎ ይጣላል የኖረ መንጋጋ።
መዘዟ የበዛ አልድን ያለችም ጣት፣
ተቆርጣ ከመጣል አትድንም ከቅጣት
ማን ብሏቸው ያውቃል ነፍሳቸውን ይማር፣
በደሉን እረስቶ ለነ አዶልፍ ሂትለር።
ምስኪን ሙሶሎኒ ብሎስ የሚያነሳ፣
ማን አለ ንገሩኝ በደሉን የረሳ
ያ ጀግና፤ ያ ቆራጥ፤ ደጉ ኢዲያሚን፣
የሚል አለ ቢባል አልችልም ለማመን።
በደል አይረሳም! ግፍ አይለመድም!
አፍ አውጥቶ እንደሰው ይጮሃል ንጹኅ ደም
ስለዚህ ሁላችን ሳንል ሴትና ወንድ፣
በደል እንቢ እንበል ግፍን እናስወግድ።
ወለላዬ ከስዊድን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ጥቅምት 26 ቀን 2002 ዓ.ም.
November 5, 2009



