አጨቃጫቂው የመያዶች ሕግ ታገደ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2001 ዓ.ም. May 19, 2009)፦ ከአንድ ዓመት በፊት ተረቅቆ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውግዘት የደረሰበትና ሲያጨቃጭቅ የቆየው የበጐ አድራጐት ድርጅቶች እና ማኅበራት ሕግ በፓርላማ ፀድቆ በነጋሪት ጋዜጣ ከታተመ በኋላ ሰሞኑን ታግዶ በቀድሞው ሕግ ምዝገባ እንዲካሄድ መደረጉ ተገለጸ።
የፍትሕ ሚኒስቴር ባለፈው ሣምንት ይፋ እንዳደረገው አዲሱ ሕግ ታገዶ በቀድሞው ሕግ ምዝገባ እንዲካሄድና አዳዲስ መያዶች የበጐ አድራጐት ድርጅቶችና ማኅበራትን ሰብስቦ እንዳስታወቀው መያዶችንና ማኅበራትን የመመዝገብና የመከታተል ሥልጣን ያለው ኤጀንሲ ተቋቁሞ በአዋጁ መሠረት የምዝገባ እና የድጋሚ ምዝገባ ሥርዓት እስኪጀመር ድረስ በበፊቱ ሕግ መቀጠል ትችላላችሁ ብሏቸዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴርን መግለጫ በበጐ ዓይን ያላዩ ተቺዎች “ባገኘነው መድረክ ተጠቅመን ሕጉ እንዳይጸድቅና ጥናት እንዲደረግበት ስንከራከር በነበረ ጊዜ ’ጥቅማችሁ ስለተነካባችሁ ነው እናንተም የኪራይ ሰብሳቢነትን ሥራ ነው የምትሠሩት፣ ካሁን በኋላ ዶላር መዛቅ የለም’ ሲሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሲሳለቁብን፤ ዛሬ አዲስ ነገር ምን ተገኘና ነው?” በማለት ጥርጣሬ እንደገባቸው ገልጸዋል።
አንዳንድ ታዛቢዎች አገዛዙ ካለበት ከፍተኛ የምንዛሬ እጥረት ጋር በማያያዝ በቀድሞው ሕግ መቀጠሉ አዲሱን ሕግ የተቃወሙ በአብዛኛው የመያድ ድርጅቶች እምነት በማጣታቸው የምንዛሬ ገቢ አሳሳቢ በመሆኑ ነው ብለዋል።
ፖኔ ከተባለ መንግሥትዊ ያልሆነ ድርጅት አስተያየት የሰጡ አንድ ግለሰብ “መንግሥት ማጣፊያው አጥሮታል፤ አይደለም የበጐ አድራጐት ድርጅቶች አዋጅ ሌሎችም አዋጆች ፖርላማው ሳያውቀው በመመሪያ ይሻራሉ።” ሲሉ ተደምጠዋል።



