ጠ/ሚ መለስ የኢህአዴግን አቋም ማንም እንደማይቀይረው ገለጹ
"ሚዲያውን በሚመለከት በ1998 ዓ.ም በሰፊው ተተኩሷል፤ ያኔ ያልገደለን የሚዲያ ጥይት አሁን አይገድለንም" ጠ/ሚ መለስ
"የሰጡት አስተያየት የጠ/ሚኒስትሩን አምባገነንነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል" አስተያየት ሰጭዎች
Ethiopia Zare (ዓርብ ግንቦት 29 ቀን 2000 ዓ.ም. June 6, 2008)፦ "የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ረቂቅ ዐዋጅ" በሚል በተረቀቀው አዲሱ ረቂቅ ዐዋጅን በሚመለከት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉት ውይይት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አምባገነናዊ ምላሽ ምክንያት ሊሳካ አለመቻሉን ከአዲስ አበባ የደረሰን መረጃ ጠቆመ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ የኢህአዴግ አቋም በማናቸውም የዲፕሎማሲም ሆነ በውይይት ሊፈታ አይችልም ሲሉ ያስጠነቀቁ ሲሆን በረቂቅ ዐዋጁ ላይ ከተጠቀሱትና ተቃውሞ ከገጠማቸው አንቀጾች መካከል፣ ከ10 በመቶ በላይ ገቢያቸውን ከውጭ የሚያገኙ አገር በቀል ድርጅቶች፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ እንዳይሠሩና፣ እንደ ውጭ ድርጅት እንዲቆጠሩ የሚያደርገውን የሕጉ አካል ማንም የማያስቀይራቸው የመንግሥት መሠረታዊ አቋም እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠንክረው መናገራቸው ታውቋል።
ከትናንት በስቲያ ከቀኑ 8 ሰዓት ተኩል እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት፣ 300 የሚሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አዲስ የወጣውን ረቂቅ ዐዋጅ በሚመለከት፣ በ30 እና በዘጠኝ ገጽ ከፋፍለው እንዲሻሻልላቸው በጠየቁት አንቀጾች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ምንጮች ገልጸው፤ ውይይቱ ግን የተሳካ አልነበረም ብለዋል።
አዲሱ የማኅበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ረቂቅ ዐዋጅ፣ ሲቪል ማኅበራቱ "አፋኝ" ሲሉ በመቃወም፣ ከመጽደቁ በፊት ውይይት ተደርጎበት እንዲሻሻልላቸው መጠየቃቸው ይታወሳል።
ረቂቅ ዐዋጁ መያዶችን አያሠራም በሚል ከተነሱት ነጥቦች መካከል፣ አገር በቀል ድርጅቶች ከ10 በመቶ በላይ ገቢያቸውን ከውጭ በማግኘታቸው ብቻ እንደ ውጭ ድርጅቶች ተቆጥረው፤ በሰብዓዊ መብት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በግጭት መፍታት፣ በማኅበረሰብ ዕድገት እንዳይሠሩ መከልከሉ አብዛኞቹን በዚህ ሥራ የተሠማሩ ድርጅቶች እንዲዘጉ የሚያደርግ ነው።
ሕጉ ከሲንጋፖር ሕግ የተቀዳ መሆኑ፤ የሲንጋፖር ሕግ ደግሞ አገሪቷ በእንግሊዝ ቅኝ በምትገዛበት ጊዜ «ቻይንዝ ሴክሪት ሶሳይቲ» እንደ ሲንጋፖር ነፃ አውጭ ዓይነት የወንጀለኛ ድርጅትን ለመቆጣጠር የወጣ ጨቋኝ ሕግ መሆኑና፣ ሕጉ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ እንዲሠራ ሲደረግ መንግሥት የሚያቋቁመው ኤጄንሲ ማኅበራቱን እንደፈለገው ምዝገባ እንዲከለክል፣ እንዲሰርዝ፣ የድርጅት ኃላፊዎች እንዲመድብ፣ እንዲያነሣ እንዲሁም እንዲቀጣ ሰፊ ሥልጣን የሚሰጥ በመሆኑ፣ ድርጅቶች ለፍርድ ቤት ይግባኝ የማለት መብታቸውን የሚያስቀር በመሆኑ ተቃውሞ ገጥሞታል።
በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን መያዶች የመብት ተኮር የልማት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ማለትም ዜጎችን ስለ መብቶቻቸው እንዳያሳውቁ በመከልከል፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የሚያስገድድ ነው ሲሉ የሕግ ባለሞያዎች አስተያየት ይሰጣሉ። ይህም ዜጎች መብታቸውን አውቀው እንዳይጠይቁና በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት ተጠያቂ እንዳይሆኑ የሚያደርግ ነው ሲሉ የሕግ ባለሞያው አስተያየት ይሰጣሉ።
መያዶችን አያሠራም የተባለው ረቂቅ ዐዋጅ እነዚህ አንቀጾች እንዲሻሻሉ እንዲደረግ ለውይይት ቀርቦላቸው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ጠንከር ያለ ምላሽ እንደሰጡ ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
ለመያዶች የሰጡት ምላሽም፤ "ዜጎች የራሳቸውን መብት ለማስከበር ገንዘብ ሊከፈላቸው አይገባም። በኢትዮጵያም ሆነ በሌላ አገር ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ ሰብዓዊ መብት በጡጦ ሊጠባ አይችልም። ጡጦ ካላስፈለገው ባለ ጡጦም አያስፈልገውም። በውጭ ገንዘብና ሃሳብ ላይ የተመሠረተ የዴሞክራሲ ዕድገት በዕባብ እንቁላል ላይ የተመረተ የዶሮ ርቢ ማለት ነው" ብለዋል።
"በእኛ ገንዘብ በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ካልሆነ በአገራችሁ ዴሞክራሲ አይኖርም የሚባለው የአንዳንድ ለጋሽ ድርጅቶች አባባል አንድም ስድብ፣ አንድም ድንቁርና ነው። ይህ መንግሥት ሲቪክ ድርጅቶች እንዲዳብሩ ቢፈልግም ከዕባብ ዕንቁላል ዶሮ ይፈለፈላል ብሎ አያምንም" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
አያይዘውም የዛሬ 40 እና 50 ዓመት በተፈጠረው የተማሪዎች ንቅናቄ፣ ሕዝብ ለራሱ መብት የውጭ ገንዘብ እንደማያስፈልገው ማስረጃ ነው ንቅናቄው በቃል ሳይሆን በጥይት ታግሎ አሳይቷል።
ገንዘብ ከውጭ፣ ሰው ከአገር ውስጥ በመደባለቅ ኢትዮጵያዊ ሰብዓዊ መብቱን አያስከብርም፣ በጡጦ በሚንቆረቆር ገንዘብ ዴሞክራሲ አይኖርም፣ በፖለቲካ ነክ ዴሞክራሲ ላይ የሚሠማሩ ድርጅቶች በውጭ ገንዘብ መሥራት አይችሉም። በኢትዮጵያ ገንዘብ ለሚሠሩ ኢትዮጵያዊ ድርጅት የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው ፍርድ ቤት ነው።
ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ፍርድ ቤት ሄደው መንግሥትን የመክሰስ መብት አላቸው። ከ10 በመቶ በላይ ገንዘብ ከውጭ የሚያገኙ አገር በቀል ድርጅቶች ግን ፍርድ ቤት መሄድ አይችሉም፣ መንግሥት በ24 ሰዓት በአስተዳደራዊ ውሳኔ ሊያፈርሳቸው ይችላል።
ይህ አቋም መሠረታዊ የኢህአዴግ አቋም ነው። ማንም አያስቀይረንም፣ ከሕገ መንግሥት አኳያ ክፍተት እንዳይኖረው በሞያተኛ አስተያየት ጀርባችንን ፈትሸን የሠራነው ነው። በፖለቲካ አቋም ደረጃ፣ እኛነታችንን የሚወስን መሠረታዊ የድርጅት አቋም ነው ማለታቸው ታውቋል።
ተሰብሳቢዎቹ ቢያንስ ጊዜ እንዲሰጣቸውና እንዲወያዩበት የጠየቁ ሲሆን፤ አቋማችንን ማንም ሊያስቀይረንና ሊቀለብሰው አይችልም። ይህን በሚመለከት ከፍተኛ የሚዲያ ዘመቻ ተከፍቶብናል፤ የረሃብ ወሬውም መጋነኑ ከዘመቻዎቹ አንዱ ነው። ሚዲያውን በሚመለከት በ1998 ዓ.ም በሰፊው ተተኩሷል። ያኔ ያልገደለን የሚዲያ ጥይት አሁን አይገድለንም። ከ1998 ዓ.ም የባሰ የሚመጣብን ነገር የለም። 2000 ዓ.ም. አልፈናል። 2002ንም እናልፋለን።
ከለጋሾች ጋር በዲፕሎማሲ ጉዳይ ሰባት ጊዜ ተነጋግረናል። በዜጎችና በመንግሥት መካከል ማንም መግባት የለበትም። የዓይነ ሥውራን መብት በውጭ ጡጦ ብቻ ከሆነ የሚረጋገጠው ዓይነ ሥውራን ያ መብት አይገባቸውም። በጡጦ የተሰጠ መብት ሥጦታ እንጂ መብት አይደለም። ለመብት መታገል እንቅፋት የሚሆን ድህነት፣ ለራስ መብት መታገል የማያስችል ድህነት፣ የአካል ድህነት ሳይሆን የመንፈስ ድህነት ነው።
አቋማችንን በማስቀመጣችን የሚዘጋ ብር ካለ እንጦሮጦስ ይግባ፤ በገንዘብ ማሥፈራራት የሚቻለው መሸሽ የሚችልን ሰው ነው። መሸሽ የማይችልን ሰው ማስፈራራት አይቻልም። በዚህ ጉዳይ ከበስተጀርባ ግንብ አለ። የማይታለፍ አጥር አለ። መሸሽ አይቻልም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸው ታውቋል።
ተሰብሳቢዎቹ በድጋሚ ውይይቱ እንዲደረግ አበክረው የጠየቁ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ የሰጡት መልስ፤ ከከተማ የሰማሁት ወሬ አለ ተጨማሪ ጊዜ የምትጠይቁት መንግሥት ከዲፕሎማቶች በሚደርስበት ጫና ዐዋጁን ሊቀይር ይችላል ብላችሁ አስባችሁ መሆኑን ደርሰንበታል። መቼም ላንቀይረው ዐዋጁን የምናዘገይበት ምክንያት የለም ሲሉ ተናግረዋል።
ስትራቴጂክ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ በሎጂክ አሳማኝ ክርክር ቢቀርብ እንቀበላለን፤ በስትራቴጂክ ጉዳዮች ግን ዱላም ቢሆን አይሠራም ካሉ በኋላ ከሥራ ጓደኞቼ ጋር ተማክሬ፣ በዐዋጁ ላይ ውይይት ተደርጎ መጽደቁን በሚቀጥለው ዓመት ለማሸጋገር ይቻል እንደሆነ አሳውቃችኋለሁ በማለት፣ ስብሰባውን መበተናቸውን ምንጮች ገልጸውልናል።
ሁኔታውን የተከታተሉ በሰጡት አስተያየት "የጠ/ሚኒስትሩን አምባገነንነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።



