በታላቁ ሩጫ «ኹከት ፈጥረዋል» የተባሉ ታስረው ተፈቱ
46 ሰዎች ታስረው 19ኙ ፍርድ ቤት ቀርበዋል
የቴዲ አፍሮን ምስል የያዘ ቲሸርት በመልበሳቸው የተያዙ ይገኙበታል
ድብዳባ እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል
Ethiopia Zare (ዓርብ ኅዳር 19 ቀን 2001 ዓ.ም. November 28, 2008)፦ በአዲስ አበባ ለስምንተኛ ጊዜ በተካሄደው ታላቁ ሩጫ ላይ በተሣታፊዎች መካከል የታዋቂውን አርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁንን (ቴዲ አፍሮን) ምስል የያዙ ቲሸርት የለበሱና፣ የቴዲ አፍሮን መፈታት የሚጠይቅ መፈክሮችን ያሰሙ ወጣቶች ለሁለት ቀናት ታስረው በዋስ መለቀቃቸውን ገለፁ። ያነጋገርናቸው ወጣቶች ድብደባ እንደደረሰባቸው ገልፀዋል።
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እነዚህ ወጣቶች እንደገለጹት፣ እሁድ ኅዳር 14 ቀን 2001 ዓ.ም. መነሻውንና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገው የታላቁ ሩጫ ተሳታፊ እንደነበሩና፣ ሩጫውን አጠናቅቀው ወደየቤታቸው ሲያመሩ፣ በፌደራል ፖሊስ ግዮን ሆቴል አካባቢ ወዳለ ሠዋራ ሥፍራ ተወስደው መደብደባቸውንና፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚገኘውና ካሳንችስ አካባቢ ባለው ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው መታሰራቸውን ገልፀው፤ የተወሰኑት ወዲያውኑ በጣቢያ ዋስ ሲለቀቁ፣ የተወሰኑት ወጣቶች በማግስቱ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ተናግረዋል።
ሰኞ ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ነክ ፍርድ ቤት ቀርበው፣ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በታላቁ ሩጫ ላይ በቡድን ተደራጅተው፣ የተለያዩ ስድብ ያዘሉ መፈክሮችን በማሰማት ሲያነሳሱ እንደነበር በመግለጽ የጊዜ ቀጠሮ እንደጠየቀባቸውና ፍርድ ቤቱም በ500 ብር ዋስትና እንዲለቀቁ መፍቀዱን ገልፀዋል።
ነገር ግን ወደ ጣቢያ ከተመለሱ በኋላ ፖሊስ ለአዲስ አበባ ከተማ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት፣ በዋስትናው ጉዳይ ላይ ይግባኝ እንዳቀረበባቸውና ፍርድ ቤቱ ይግባኙን ውድቅ አድርጎ በዋስ እንደለቀቃቸው ተናግረዋል።
ታላቁ ሩጫ በተካሄደበት ዕለት ቴዲ አፍሮ እንዲፈታ የሚጠይቁና ሌሎች ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር የተያያዙ የተለያዩ መፈክሮች መሰማታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ታስረው ፍርድ ቤት ከቀረቡት ወጣቶች መካከል "ቴዲ አፍሮ አይቀርም ታስሮ!" የሚል ጹሑፍ የታተመበትና፣ ምስሉ ያለበት ቲሸርት የለበሱ ወጣቶች ታይተዋል።
ወጣቶቹ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ በቡድን ያልተደራጁና ከተለያየ ቦታ ሩጫው ላይ ለመሳተፍ የመጡ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው በማመልከታቸው ማክሰኞ ኅዳር 16 ቀን ዋስትናው ተፈቅዶላቸዋል።
ወጣቶቹ እንደሚሉት በዕለቱ የተያዙት ወደ 46 እንደሚሆኑና፣ ፖሊስ ቃል እየተቀበለ የለቀቃቸው ስለነበሩ "በመጨረሻ ፍርድ ቤት የቀረብነው በግምት ወደ 19 ወጣቶች ነን" ሲሉ ጠቁመዋል።



