ኢንጂ. ኃይሉ ሻውል፣ አቶ ልደቱ አያሌው፣ አቶ አየለ ጫሚሶ፣ ፍትህ ሚኒስቴር፣ … ተወገዙ

9th Great Run 9ኛው ታላቁ ሩጫ

Ethiopia Zare (እሁድ ኅዳር 13 ቀን 2002 ዓ.ም. November 22, 2009)፦ በአትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚደረገው ዘጠነኛው ታላቁ ሩጫ በዛሬው ዕለት (ኅዳር 13 ቀን 2002 ዓ.ም.) 33 ሺህ ተሳታፊዎች በተካፈሉበት የተካሄደ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹ የአንድነት ፓርቲ መሪ ወ/ት ብርትኳን ሚደቅሳ እንድትፈታ በጩኸት ጠይቀዋል።

 

በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 4፡30 በአትሌት ኃይሌ እና በአትሌት ፓውላ አስጀማሪነት ከአብዮት (መስቀል) አደባባይ የተጀመረው ሩጫ በስታዲየም አድርጎ ወደ ልደታ በሚጎርፍበት የመጀመሪያዎች ደቂቃ ተሳታፊዎቹ፤ እጃቸውን በማስተላለፍ የመታሰር ምልክት እያሳዩ በአንድ ወቅት ከአርቲስት ቴዲ አፍሮ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቶ የነበረውን የራዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ “ሰይፉ መላጣ ያመጣው ጣጣ” በማለት ማጥላላት ጀመሩ።

 

አረንጓዴ ቀለም ያለው ቲሸርት የለበሱት ተሳታፊዎች በአንድ ላይ ወደፊት ሲሮጡ ለየት ያለ ውበት የሚፈጥሩ ሲሆን፣ በአንድ ድምፅ የሚያሰሙት የተቃውሞ ጩኸት ደግሞ ወኔን ይቀሰቅስ ነበር።

 

በየቡድኑ መካከል ግጥም የሚያወጣና የሚያስተባብር አካል ያለ ይመስል ወደፊት ባሉና ወደኋላ በቀሩ ቁጥር የሚሰማው ግጥም አንድ አይነት ነበር።

 

ሩጫው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታስራ የምትገኘው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጀግንነቷ በሁሉም ሰው ልብ ውስጥ መኖሩን የሚያረጋግጥ ነበር።

 

9th Great Run 9ኛው ታላቁ ሩጫበሰልፉ ላይ ስለወ/ት ብርቱካን የተደመጡ ግጥሞችም፦

“… እንነጋገር፤ እንነጋገር

የቡርቴን ነገር …”

 

“… እንዴት ይረሳል፤ እንዴት ይረሳል

የቡርቴ ጉዳይ …”

 

“… ቡርቱካን ማንዴላ

ልደቱ ሌባ …”

 

“… ቡርትዬ ጀግና፤

ልደቱ ሌባ …”

 

በሩጫው ላይ ወ/ት ብርትኳን ስትወደስ፣ ስትሞገስ “ብርትኳን ትፈታ” በሚል ከእስር መፈታቷ ሲጠየቅላት፤ አቶ ልደቱ በህዝብ ልብ ውስጥ የማይፋቅ ጥላቻ ማትረፋቸውን ያረጋገጠ ሰልፍ ነበር። ተጀምሮ እስኪጨረስ የአቶ ልደቱን “ሌባ” በማለት በዜማ የማያንጎራጉር፤ “ልደቱ ይሰቀል” በማለት ተሳታፊዎቹ ጥላቻቸውን ሲገልጹ ነበር።

 

በዛሬው ሩጫ ላይ ኢንጂንየር ኃይሉ ሻውልም ተቃውሞው አልቀረላቸውም ነበር። “ወኔ የሌለው፤ ኃይሉ ሻውል ነው” የሚሉ ግጥሞች ተደምጠዋል። የቅንጅትን ስም የወረሱት አቶ አየለ ጫሚሶም በአባታቸው ስም “ጫሚሶ ሌባ” የሚል ዘለፋ ደርሶባቸዋል።

 

ሯጩ ተሳታፊ ቤተመንግሥት በር ላይ ሲደርስ እየቆመ፤ “መሰናበቻ መሰናበቻ፣ ስድስት ወር ብቻ፣ … እንደፈራችሁ ደረስንባችሁ” በማለት በከፍተኛ ጩኸት ተቃውሞን ሲገልጽ ነበር። ፍትህ ሚኒስቴር በር ላይ ሲደርስ ደግሞ “ፍትህ የሌለው፣ ፍትህ ሚኒስቴር ነው” በማለት ሯጩ ህዝብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን አጣጥሎታል።

 

የመሮጫው ቲሸርት የተሸጠው አንዱ 50 ብር በመሆኑም “ሃምሳ ብራችን፣ ነፃነታችን” በማለት በ50 ብር ሰልፍ መውጣታቸውን ጠቆም አድርገው ለማለፍ ሞክረዋል።

 

በአጠቃላይ በዛሬው ዕለት በተደረገው ታላቁ ሩጫ ተሳታፊው ወ/ት ብርትኳን እንድተፈታ ጠይቆና ተቃውሞን ገልጾ በሠላም ወደየቤቱ ተበትኗል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ