ታላቁ ሩጫ ከአራት ዓመታት በኋላ ወደ መስቀል አደባባይ ተመለሰ

ኢትዮጵያ ዛሬ (እሁድ ኅዳር ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Nov. 20, 2016)፦ አንዴ በጸጥታ ችግር ሌላ ጊዜ በመንገድ ስራ ተሳቦ ላለፉት አራት ዓመታት ከህዝባዊው አደባባይ ርቆ የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ ዛሬ ወደ መስቀል አደባባይ ተመልሶ ተከናውኗል።
ከዚህ ቀደም ህዝባዊ ድምጾችና አቤቱታዎች የሚሰሙበት ይህ ዓመታዊ ሩጫ አሁን በሺህ የሚቆጠሩ የደህንነት ሰዎች አብረው በመሮጥ ዝምታ ለማስፈን እንደቻሉ በአካባቢው ያሉ ምንጮች ያስረዳሉ።
ዛሬ መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ አድርጎ በተካሄደው የዘንድሮ ታላቁ ሩጫ ውድድር ላይ 42 ሺህ ሰዎች ተሳታፊ ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪም በ2009 የቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 500 አትሌቶች የተወዳደሩ ሲሆን፣ ሁለት ኬንያዊያን አትሌቶችም ተሳትፈዋል።
በዚህም መሰረት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫውን በወንዶች አትሌት አቤ ጋሻሁን ከአማራ ማረሚያ ቤት አንደኛ በመሆን አጠናቋል። አትሌት አቤ ጋሻሁን ውድድሩን ለመጨረስ 28 ደቂቃ 53 ሴኮንድ ከ80 ማይክሮ ሴኮንድ ፈጅቶበታል። እንዲሁም ኬንያዊው አትሌት ጆሩም ሉምባሲ ሁለተኛ የወጣ ሲሆን፣ አትሌት አዱኛ ታከለ ከኦሮሚያ ፖሊስ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።
በሴቶች በተደረገ ውድድርም አትሌት ፎቴን ተስፋዬ ከመሰቦ ስፖርት ክለብ አንደኛ መበሆን ውድድሯን አጠናቃለች። ፎቴን ተስፋዬ በ33 ደቂቃ ከ09 ሴኮንድ በመግባት አሸናፊ ሆናለች። ከኦሮሚያ ፖሊስ አትሌት ሙልዬ ደቀቦ ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ያጠናቀቀች ሲሆን፣ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን ያጠናቀቀችው አትሌት ታደለች በዳሶ ከኦሮሚያ ማረሚያ ቤት ነች።
ውድድሩን ከአንድ እስከ ሦስተኛ ለወጡ አትሌቶች በሙሉ የዋንጫ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፣ በወንዶችና በሴቶች ውድድሩን በአንደኝነት ለጨረሱት አትሌቶች የ50 ሺህ ብር ሽልማት ተሰጥቷል። ሁለተኛ ለወጡት 25 ሺህ፣ በሦስተኛነት ላጠናቀቁት ደግሞ የ10 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የዘንድሮ ውድድር በታላቁ ሩጫ ታሪክ ክብረ ወሰን የሆነ 42 ሺህ ሰዎች የተሳተፉበት ሲሆን፣ በዚህ ውድድር የቀይና አረንጓዴ ቲሸርት ለባሾች የተለያየ መነሻዎችን በማድረግ ነው የተካሄደው። ቀይ ለብሰው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ከ1 ሰዓት በታች መግባት የሚችሉ ብቻ ሲሆኑ፣ አረንጓዴ የሚለብሱት ከ1 ሰዓት በላይ የሚገቡት መሆናቸው ታውቋል።
በውድድሩ ላይ ከ250 በላይ የሆኑ ከ20 በላይ የተለያዩ አገራት የውጭ አገር ዜጎች መሳተፋቸው ተገልጿል። የአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ሩጫ የዘንድሮ ዋና መልዕክት “መኖር ለዚህ አበቃኝ” በሚል ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር ተላልፏል።



