ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወለጋ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ
ወለጋ ለኢትዮጵያ ነፃነት ሕልውና ተምሳሌት መኾኑን ገለጹ
ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 15, 2021)፦ “ወለጋ የኦሮሞ ሕዝብና ለኢትዮጵያ ነፃነትህ ሕልውና ተምሳሌት ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት የደምቢዶሎ-ሙጊ-ዶላ የአስፓልት መንገድ ግንባታን ትናንት ባስጀመሩበት ወቅት ነው።
ምዕራብ ኢትዮጵያ ብርቅዬ የማይጠገብ የፍቅርና የልማት አካባቢ ነው። ይህንን የማውቀው በወሬ ሳይኾን በተጨባጭ ኖሬበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወለጋ ለኦሮሞ ሕዝብና ለኢትዮጵያ ነፃነትና ሕልውና ተምሳሌት ነው በማለት ተናግረዋል።
አያይዘውም አብዲሳ አጋ ለኢትዮጵያ አንድነት ዋጋ የከፈለ በአካባቢው የተወለደ ጀግና ዘላለም ታሪክ የሚያስታውሰው መኾኑንም በመግለጽ፤ ቄስ ጉዲና ቱምሳ የኢትዮጵያው ማርቲን ሉተር ነው፤ ወለጋ የሌሎች ጀግኖች መፈጠሪያ እንደኾነም በዚሁ ንግግራቸው አመልክተዋል።
ወለጋ የነፃነት ታጋይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በመሠረተ ልማት ችግር ግን ሳይጠቀም እና የሚገባውን የልማት ድርሻ ሳይወጣ መቆየቱንም አስታውሰዋል። (ኢዛ)



