ግጭቱ የተነሳው በቤንሻንጉሎች እና በኦሮሞዎች መሃከል ነው

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2000 ዓ.ም. May 24, 2008)፦ ልክ የዛሬ ሣምንት ቅዳሜ ግንቦት ዘጠኝ ቀን 2000 ዓ.ም. በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሞዎች መካከል በተነሳ ግጭት ዘጠና ሦስት ሰዎች እንደሞቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለፁ።

 

ቀደም ሲል “ወለጋ እርሻ ልማት” ተብሎ ይጠራ የነበረውና ከነቀምት ወደ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው፤ አሁን ግን “አንገር” እየተባለ በሚጠራው ባለሀብቶች መሬቱን ገዝተው በሚያለሙበት ቦታ ነው ይህ ግጭት የተከሰተው።

 

ግጭቱ የተነሳባቸው ሥፍራዎች ‘አንገር አራተኛ’ እና ‘አንገር ስምንተኛ’ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል። የግጭቱ መነሻ ተብሎ የተጠረጠረው ከዚህ ቀደም በእርስ በርስ ፀብ የተነሳ ሁለት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ሰዎች ይሞታሉ። ገዳዮች ተብለው የተጠረጠሩት የኦሮሞ ተወላጆች ሲሆኑ፣ ተከስሰው እያለ የፍርዱ ሁኔታው ይጓተታል። ‘ፍርድ አላገኘንም’ የሚሉ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ሰዎች የግንቦት 9ኙን ግጭት እንደጀመሩትና ኦሮሞዎቹን ማጥቃት እንደጀመሩ ለማወቅ ተችሏል።

 

በአንገር አራተኛ እና በአንገር ስምንተኛ አብዛኞቹ ነዋሪዎች ኦሮሞዎች ሲሆኑ፣ በአንገር አንደኛ፣ በአንገር ሁለተኛ፣ በአንገር ሦስተኛ፣ በአንገር አምስተኛ፣ በአንገር ስድስተኛ፣ በአንገር ሰባተኛ የሚኖሩት ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ ናቸው። በግጭቱ ምክንያት አብዛኛው የአንገር ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው ወደ ነቀምት እና አካባቢው ወዳሉ ከተሞች ተሰድደዋል።

 

ከተሰደዱት ሰዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ለኢትዮጵያ ዛሬ እንደገለፁት ከሆነ ጠብመንጃ እየተተኮሰ፣ ቤታቸው ውስጥ እሳት ተለቅቆባቸው፣ በስለት መሣሪያዎች ነው ሰዎቹ የተገደሉት። ከአንገር አራተኛ ወደ ሰባ ሰባት ሰዎች እንደሞቱና ከአንገር ስምንተኛ አስራ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን እነዚሁ ለስደት የተዳረጉት የአንገር ነዋሪዎች ገልጸዋል። አንዳንዶቹ የሟቾቹን ቁጥር ከ93 ወደ 100 ያደርሱታል።

 

አንድ ግለሰብ ለሥራ ጉዳይ ነቀምት ደርሶ ወደ አንገር በመመለስ ላይ እያለ ግጭቱ ተከስቶ ስለነበር በያዘው መኪና አምስት ቁስለኞችን ወደ ነቀምት ሆስፒታል የወሰዳቸው ሲሆን፣ ከእነዚያ ውስጥ አንዱ ማረፉን ለማወቅ ችለናል።

 

ከማዕከላዊ መንግሥት አቶ አባዱላ ገመዳ ግጭቱን ለማረጋጋት መላካቸውንና እዚያ መሰንበታቸውን ለማወቅ ችለናል። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ያረጋል አሽሹም ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይከታተሉት የነበረውን ሥልጠና አቋርጠው ወደ ክልሉ አምርተዋል። እነኝሁ ሁለት ባለሥልጣናት ወደ ክልሉ ከሄዱ በኋላ፣ ግጭቱና ችግሩ በሀገር ሽማግሌዎች ይፈታ የሚል መደምደሚያ ላይ ሳይደረስ እንዳልቀረ ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጸዋል።

 

እስካሁን ድረስ አካባቢውን ጥለው የተሰደዱ ነዋሪዎችና ገበሬዎች ያልተመለሱ ሲሆን፣ የግንቦት ወር ሳያልቅ በፊት እህል ካልዘሩ ከአካባቢው በሚቀጥሉት አራት ወራት ውስጥ የሚጠበቀው ምርት እንደማይኖር ለመረዳት ችለናል።

 

ግጭቱን አስመልክቶ አንድ የአካባቢው ነዋሪ አዛውንት “ኢትዮጵያዊ መሆናችንን የጠላንበት ክስተት ነው። የኃይለሥላሴንና የደርግን መንግሥት አይቻለሁ። እንዲህ ያለ በብሔር ምክንያት የተከሰተ አሰቃቂ እልቂትና ችግር ግን ገጥሞኝም ሆነ ሰምቼም አላውቅም” ሲሉ በምሬት ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጸዋል።

 

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው አንድ መምህር ደግሞ “በዚህ ዓመት ብቻ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ወደ አራትና አምስት ጊዜ በጎሣ ግጭት እልቂት መከሰቱ ነው። ይሄንን በመመልከት ብቻ ‘እውነት ሀገሪቱን የሚገዛና የሚያስተዳድር መንግሥት አለን?’ ብዬ ለመጠየቅ ተገድጃለሁ” ብለውናል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ