በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅመዋል የተባሉት
    - ለ98 ሰዎች አሰቃቂ ሞት ተጠያቂ ናቸው፣
    -  አንዲት ሴት ለ16 ሆነው ደፍረዋል፣  
    - 300 የሚሆኑ ቤቶች አቃጥለዋል፣
    - በርካታ የቀንድና የጋማ ከብቶችን አልባሳትና እህል ዘርፈዋል በሚል ተከሰዋል

Ethiopia Zare (ዓርብ ጥቅምት 28 ቀን 2001 ዓ.ም. November 7, 2008)፦ ሦስት ረዳት ኢንስፔክተሮችና ሁለት ኮንስታብሎችን ጨምሮ፣ አድራሻቸው እንደሚገልፀው 147 የቤንሻጉል ክልል ነዋሪዎች፤ በብሔረሰብ አንድ የኾነን ህዝብ በሞላ ወይም በከፊል ለማጥፋት በማሰብ የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጅ በሆኑ አርሶ አደሮች ላይ ጉዳት በማድረስ የ98 ሰዎችን ህይወት አጥፍተዋል፣ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፣ አንዲት ሴት ለ16 በመኾን አስገድደው ደፍረዋል፣ 300 የሚኾኑ ቤቶች አቃጥለዋል፣ በርካታ የቀንድና፣ የጋማ ከብቶችን፣ አልባሳትና እህል ዘርፈል ባላቸው ተከሳሾች ላይ የፌደራል ዓቃቤ ሕግ ክስ መሠረተ።

 

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ተከፍቶ፣ በዳኛ አደም ኢብራሂም፣ በዳኛ አሰፋ አብርሃና በዳኛ ዘሪሁን ቦዳ እየታየ በሚገኘው የዓቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ፤ እንደሚያስረዳው በ147 ተከሳሾች ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ክሱም በአራት የተከፈለ ነው።

 

በተከሳሾቹ ላይ የቀረበው አንደኛው ክስ እንደሚያስረዳው፤ ከ1ኛ እስከ 66ኛ ተራ ቁጥር የተዘረዘሩ 66 ተከሳሾች፤ ከ67ኛ እስከ 82ኛ፣ ከ97ኛ እስከ 147ኛ የተዘረዘሩ 67 ተከሳሾች፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጅ በሆኑት አርሶ አደሮች ላይ አመፅ እንዲያነሳሱ በመቀስቀስ፣ በማደራጀትና በርካታ የጦር መሣሪያ በማከማቸትና በማስታጠቅ ከግንቦት 8 ቀን እስከ 23 ቀን 2000 ዓ.ም፣ በኦሮሚያና በቤንሻጉል ክልሎች አዋሳኝ በሆኑት ቦታዎች በአንገር ሸንኮራ፣ እንገዎች አንገር ሚጤ፣ ሳይዶልቻ፣ ሰኞ፣ ዲዲጋ ሆሮዎታ፣ ዶም ጠና አይዳ ቀበሌዎች ውስጥ፣ ሁሉም የጦር መሣሪያ ይዘው በመግባት፣ 105 የሚሆኑት ተከሳሾች የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጅ በሆኑት አርሶ አደሮች ላይ አመፅ በማነሳሳት፣ ቁጥራቸው 98 በሆኑ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አረጋውያን ላይ የጦር መሣሪያ በመተኮስና በጦር በመውጋት፣ ሕይወታቸው እንዲያልፍ በማድረግና የአካል ጉዳት አድርሰዋል ሲል ዓቃቤ ሕግ የተከሳሾቹን ማንነት በዝርዝር ጠቅሶ ክስ አቅርቧል።

 

በአንደኛው ክስ የተከሰሱትን ጨምሮ 36 ተከሳሾች፣ በሁለተኛ ክስ የተከሰሱ ሲሆን ግድያው በተፈፀመበት ዕለት ብዛታቸው 300 በሆኑ የሳር ክዳን ቤቶች ላይ እሳት በማቀጣጠል በውስጣቸው ካሉት በርካታ የቤት ቁሳቁሶች አልባሳት፣ ምግብና እህል ጋር በእሳት እንዲጋዩ በማድረጋቸው፣ … ክስ ማቅረቡን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አሥፍሯል።

 

በሦስተኛው ክስ ከ110ኛ እስከ 125ኛ ያሉ ተከሳሾች ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ በምሥራቅ ወለጋ ዞን በለሙ ወረዳ፣ ሳሲጋ ቀበሌ ውስጥ፣ ተከሳሾቹ፣ በአንደኛና በሁለተኛ ክስ የተጠቀሰባቸውን ሰው ገለውና ቤት አቃጥለው ሲያበቁ አንዲትን ሴት ወጣት በያዙት መሣሪያ በማስፈራራት እንዳትከላከል ካደረጓት በኋላ በመፈራረቅ ለ16 ግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጽመውባት ጤናዋ እንዲታወክ በማድረጋቸው፣ በግብረ አበርነት በፈፀሙት አስገድዶ መድፈር ወንጀል መከሰሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አሥፍሯል።

 

በአራተኛው የዓቃቤ ሕግ ክስ ከ97ኛ እስከ 109ኛ እና ከ126 እስከ 147ኛ ያሉ 35 ተከሳሾች የጦር መሣሪያ ይዘው በመደራጀት፣ የህዝብን ፀጥታ አደጋ ላይ በሚጥል ጭካኔ የተሞላበት ኃይል ተጠቅመው የሠላማዊ አርሶ አደሮች ንብረት የሆኑ በርካታ የቀንድና የጋማ ከብቶችን፣ ቁሳቁሶችን፣ አልባሳትና እህል በመዝረፋቸው በአጠቃላይ በግብረ አበርነት በፈፀሙት ወንጀል ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸዋል።

 

ተከሳሾቹ በእስር ከሚገኙበት ዴዴሳ ማሠልጠኛ፣ ቃሊቲ በሚገኘው አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ የተደረገ ሲሆን፣ ሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2001 ዓ.ም. በነበረው ቀጠሮ ከ147 እስረኞች 123ቱ ሲቀርቡ 23 እስረኞች ባለመቅረባቸው፣ ፖሊስ ተከታትሎ ይዞ እንዲያቀርብ ታዟል።

 

ተከሳሾቹ መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው በመጠየቃቸው፤ የተከላካይ ጠበቆች ጽ/ቤት ለተከሳሾች ጠበቃ እንዲያቆም ታዞ፣ ለኅዳር 8 ቀን 2001 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ