አትሌት ጥሩነሽና ስለሺ የጋብቻቸውን ቀን ይፋ አደረጉ
Ethiopia Zare (ዓርብ ጥቅምት ፯ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም. October 17, 2008)፦ የጀግናዋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባና የስለሺ ስኅን የጋብቻ ሥነ ሥርዓት በሒልተን ሆቴል፣ በመስቀል አደባባይና በሼራተን አዲስ በደማቅ ሥነ ሥርዓት እንደሚከበር ተገለጸ።
ትናንት ሁለቱ ጀግኖች አትሌቶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል፣ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተጠቆመው፣ እሁድ ጥቅምት 16 ቀን 2001 ዓ.ም. የሚከናወነው የሁለቱ አትሌቶች የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት በሦስት ዐበይት መርኀ ግብሮች የተከፈለ ነው።
ከወጣው ፕሮግራም ለማወቅ እንደተቻለው የሠርጉ ሥነ-ሥርዓት አዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በሚደረገው የምሳ ግብዣ ይጀመራል። በሒልተን የሚካሄደው ሥነ-ሥርዓት እንዳበቃ ሙሽሮቹ ወደ መስቀል አደባባይ በመጓዝ በዚያ ከሚጠብቃቸው የአዲስ አበባ ነዋሪ ጋር የጋብቻቸውን ሥነ-ሥርዓት በጋራ ያከብራሉ።
በመስቀል አደባባይ የሚካሄደው ፕሮግራም እንዳበቃ፣ ሙሽሮቹ በሠረገላ ሆነው በማረሚያ ቤቶች የሙዚቃ ማርሽና በትራፊክ ፖሊስ ሞተረኞች በመታጀብ ወደ ሼራተን አዲስ ይጓዛሉ። በሼራተን የፎቶ ፕሮግራምና አንድ ሺህ ሰዎች የሚታደሙበት የእራት ግብዣ ይኖራቸዋል።
በትናንቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እነአትሌት ስለሺ የሠርጋቸውን ወጪ ሙሉ በሙሉ እራሳቸው እንደሚሸፍኑ ገልጸዋል።
በፍቅር ምን ያህል ግዜ እንዳሳለፉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ስለሺ “5 ዓመት ሆኖናል። እኔ እሷን ለማግኘት ትንሽ ለፍቻለሁ፣ ጥሩ ነገር ሳይለፋ አይገኝም” ብሏል።
ጥሩነሽ በበኩሏ “መጀመሪያ ስንገናኝ አንድ ነገር ቃል አስገብቼው ነበር፣ አንድ ወንድም ብቻ ስላለኝ ወንድሜን ሚዜው እንዲያደርገው፤ እሱም ቃሉን አክብሮ ሚዜው አድርጎታል” ብላለች።
የሷ ሚዜዎች እነማን እንደሆኑ ተጠይቃ፣ እህቶቿ እጅጋየሁ ዲባባ እና ገንዘቤ ዲባባ ከሚዜዎቿ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጻለች።
ጋዜጣዊው መግለጫውን ያዘጋጀው የኢኒግማ ስፖርት አድቨርት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤልሻዳይ ነጋሽ፣ በጥሩነሽ ዲባባ ስም www.tiruneshdibaba.net ድረ ገጽ መከፈቱ እና “የኔ ማህደር” በሚል ርዕስ ከተወለደችበት ቀን አንስቶ እስከ ቤጂንግ ኦሎምፒክ ድረስ ያለው የአትሌቷ ግለታሪክ መካተቱን አስታውቀዋል። የሠርጉ ሥነ-ሥርዓት በራሷ ስም በተከፈተው ድረ ገጽ እንደሚተላለፍ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
ኅዳር 2008 ሞናኮ ላይ የዓለም ምርጥ አትሌቶች ምርጫ ይካሄዳል። በዕጩነት ከቀረቡት አትሌቶች ውስጥ ጥሩነሽን ጨምሮ፣ ኃይሌ ገ/ሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ይገኙበታል። ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በምርጫው እንዲያሸንፉ በኢንተርኔት በሚደረገው የመራጮች የድምፅ አሰጣጥ ኢትዮጵያውያን በንቃት እንዲሳተፉ የመገናኛ ብዙኃን ማበረታታት እንዳለባቸው ተገልጧል። (ለዓለም 2008 ምርጥ አትሌቶች ድምፅዎን ለመስጠት እዚህ ይጫኑ!)



