ለኢትዮጵያውን አትሌቶች ድምፅ ይስጡ!
ለ2008 የዓለም አትሌት ምርጫ ሦስት ኢትዮጵያውያን ታጭተዋል


Ethiopia Zare (ዓርብ ጥቅምት 14 ቀን 2001 ዓ.ም. October 24, 2008)፦ በያዝነው 2008 እ.ኤ.አ. በሞናኮ በሚዘጋጀው የዓለም የ2008 አትሌትን ለመምረጥ በኢንተርኔት የድምፅ አሰጣጥ እየተካሄደ ሲሆን፣ ለዚህ ከታጩት 20 የዓለም ምርጥ አትሌቶች ውስጥ ሦስቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው። እርስዎም ድምፅ በመስጠቱ መሳተፍ ይችላሉ።
የዓለም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማኅበር (IAAF) የ2008’ን የዓለም አትሌት ለመምረጥ እያደረገ ባለው ዝግጅት ላይ ለዓለምን ህዝብ ድምፅ በኢንተርኔት በሚደረግ ምርጫ ማሰባሰብ ጀምሯል።
የማኅበሩ ኤክስፐርቶች አሥር ወንድና አሥር ሴት የዓለም ምርጥ አትሌቶችን ለህዝብ ይፋ ያደረጉ ሲሆን፣ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ እንደተካተቱበት ለማወቅ ተችሏል።
በዚህ በኢንተርኔት ከዓለም ህዝብ በሚሰበሰበው ድምፅ መሠረት ከፍተኛውን ድምፅ ያገኙ ሦስት ምርጦች ለዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፋውንዴሽን ዳኞች ሥማቸው ይቀርባል። እናም ዳኞቹ የ2008 የዓለም አትሌት የሆነውን/ችውን ይመርጣሉ።
እነኝህ ዳኞች ምርጫውን የሚያደርጉት በቀጥታ ሥርጭት በሚተላለፍ መድረክ ላይ ፈረንሣይ ሀገር ሞናኮ ውስጥ ኖቨምበር 23 ቀን 2008 እ.ኤ.አ. (ኅዳር 14 ቀን 2001 ዓ.ም.) በሚካሄደው የ2008 የዓለም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማኅበር የዓለም አትሌቲክስ ጋላ መሆኑ ታውቋል።
እርስዎም በዚህ ድምፅ አሰጣጥ ላይ ለመሳተፍ የሚሹ ከሆነ እዚህ ይጫኑና በቀጥታ ወደ ድምፅ መስጫው ይወስድዎታል። ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ከወንዶች አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ4ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፣ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ደግሞ በ5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ ከሴቶች በ4ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ከሦስቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በድምፅ ብልጫ እየመራች የምትገኘው አትሌት ጥሩነሽ መሆንዋን ለማረጋገጥ ችለናል።



