የካራማራ ድል

የካራማራ ድል መታሰቢያ ሐውልት

የኢትዮጵያውያን የታሪክ አካል መኾኑንም ገለጹ

ኢዛ (ሐሙስ የካቲት ፳፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 5, 2020)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የካራማራን ድል በማስታወስና በማወደስ፤ የካራማራ ድል የሁላችንም የኢትዮጵያውያን የአልበገር ባይነትና ለአገር የመሥዋዕትነት የመክፈላችን አካል ነውም ሲሉ ገለጹ።

የካራማራ ድልን በዚህ ደረጃ እንዲታወስ በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት ባስተላለፉት መልእክታቸው፤ የአገርን ሉአላዊነትና ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የሚከፈሉ መሥዋዕትነቶች በየትኛውም ዘመን ቢፈጸሙ የአገራችን ታሪካዊ ኩራት ናቸውም ብለዋል።

በጄኔራል ሙሐመድ ዚያድ ባሬ ትመራ የነበረችው ሶማሊያ “ከአዋሽ በታች ያለው የኢትዮጵያ ግዛት የኔ ነው” በማለት ነበር መጀመሪያ በእጅ አዙሪ ከዚያም በይፋ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ያወጁት። በ1969 ዓ.ም. የዚያድ ባሬ ጦር በምሥራቅ ኢትዮጵያ 700 ኪሎ ሚትር ዘልቆ መግባት ችሎ ነበር። በዚያን ጊዜ የደርግ ሊቀመንበር ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወራሪውን ኃይል ለመመከት ታሪካዊውን የእናት አገር ጥሪ ሚያዝያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም. አቀረቡ። ኢትዮጵያውያንም ወረራውን ለመመከት ባደረጉት ርብርብ የዚያድ ባሬ ጦር ልክ የዛሬ 42 ዓመት፤ የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም. ካራማራ ላይ የመጨረሻ ጽዋውን ተጎነጨ። ኢትዮጵያውያንም በጠላት ላይ ድል ተቀዳጁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካራማራን ድል ያስታወሱበትን ሙሉ መልእክት እነኾ! (ኢዛ)

ከዚያድ ባሬ መራሹ የሶማሊያ ወራሪ ኃይል ጋር በነበረን ተጋድሎ ወሳኝ ድል ላስመዘገብንበት የካራማራ ድል በዓል እንኳን አደረሳችሁ።

የ1967ቱ የሶማሊያ ወረራ አገራችን ከአብዮት ፍንዳታው ጭጋግ ባልወጣችበትና የእርስ በርስ ግጭት ላይ በነበረችበት ጊዜ የተከሠተ ነው።

ኢትዮጵያን የወረሩ አብዛኞቹ ኃይሎች እንደሚሠሩት ስሕተት ዚያድ ባሬም ተሳሳተ። አገር የደከመች መስሎት ኢትዮጵያን የማሸነፊያ ጊዜ የደረሰለት መሰለው። በዚህ የተሳሳተ ስሌት ተመርቶ ወረራውን ፈጸመ። በመጀመሪያ አካባቢ እንዳሰበውም የጎላ መከላከል ሳይገጥመው ሰፊ የአገራችንን መሬት ማካለል ችሎ ነበር። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን እንደፍግ ተኝተው እንደ እቶን በተነሡ ጊዜ ምን እንደሚያደርጉ በዚህ ወረራ ጊዜ ታየ።

በአጭር ጊዜ “የእናት አገር ጥሪ” የተሰባሰቡ፣ በቂ የሥልጠናም ኾነ የዝግጅት ሁኔታ ያልነበራቸው፣ ነገር ግን ከየትም የማይበደሩት የአገር ፍቅርና የማሸነፍ ወኔ ያላቸው ውድ ኢትዮጵያውያን ወረራውን በስኬት መቀልበስ ቻሉ።

መንግሥታትን በአገር ውስጥ ክዋኔያቸው በአንድም በሌላም ልንመዝናቸው እንችላለን። ነገር ግን የአገርን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የሚከፈሉ መሥዋዕትነቶች በየትኛውም ዘመን ቢፈጸሙ የአገራችን ታሪካዊ ኩራት ናቸው።

የደርግ መንግሥትም በአጭር ጊዜ ጥሪ አቅርቦ፣ አሠልጥኖና አደረራጅቶ የአገርን ክብር ለማስመለስ ያደረገው ተጋድሎና ያስመዘገው ድል የሁላችንም የኢትዮጵያውያን የአልበገር ባይነትና ለአገር የመሥዋዕትነት የመክፈል ታሪካችን አካል ነው።

ሁሌም በውስጣችን ክፍተት ሲኖር የውጭ ጠላት እንጋብዛለን፤ ስንጠናከር ግን የታፈርንና የተከበርን እንኾናለን።

በዚህ አጋጣሚ ከኢትዮጵያውያን ጎን ተሠልፈው የተዋጉትንና ውድ ሕይወታቸውን የሠዉትን የኩባና የየመን ወታደሮችን ውለታ ታሪክ ሲዘክረው ይኖራል።

ክብር አገርን ለማቆየት ራሳቸውን መሥዋዕት ላደረጉ ኢትዮጵያውያን!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ