(ተጨማሪ ጥንቅር የታከለበት ዘገባ ስለሆነ ያንብቡት!!!)  

  • ይግባኛቸው ውድቅ ተደረገ
  • በሰበር ችሎት ይግባኝ ማለት ይችላሉ

Col. Mengistu Hailemariam

Ethiopia Zare (ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2000 ዓ.ም. May 26, 2008)፦ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ ሲታይ የነበረው የደርግ ባለሥልጣናት የፍርድ ሂደት በሃያዎቹ ላይ ሞት በመፍረድ ዛሬ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ ከላከው ሪፖርት ለመረዳት ችለናል።

 

ጥር 3 ቀን 1999 ዓ.ም. የፌዴራሉ የከፍተኛ ፍርድ ቤት በዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠርጥረው ተከስሰው በነበሩት የደርግ ባለሥልጣናት ላይ እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ድረስ የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎችን ከሰጠ በኋላ፤ ዓቃቤ ሕግ እና ተከሳሾቹ ይግባኝ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለው እንደነበር ይታወሳል። ዓቃቤ ሕግ “ቅጣቱ አንሷልና በሞት ፍርድ ይቀጡልኝ” ሲል፣ ተከሳሾቹ ደግሞ “በነፃ ልንሰናበት ይገባናል፤ አልያም ቅጣቱ በዝቶብናልና ይቀነስልን” ሲሉ ነበር በተለያዩ መዝገቦች ይግባኝ ብለው የነበሩት።

 

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ተለያይተው የቀረቡትን መዝገቦች በአንድ መዝገብ በማጠቃለል ሁለቱንም ወገኖች ሲያከራክርና ጉዳዩን ሲመረምር ቆይቶ በዛሬው ዕለት የመጨረሻ ውሳኔውን ለመስጠት ተስይሞ ነበር።

 

በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ተሰይሞ የነበረው ችሎት ዓቃቤ ሕግ በሞት እንዲቀጡለት በይግባኝ ካቀረባቸው 21 የደርግ ባለሥልጣናት ውስጥ በ20ዎቹ ላይ ሞት ሲፈርድ፣ በአንዱ ላይ የከፍተኛ ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቶለታል።

 

በዛሬው ዕለት በሞት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው፣

1) ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣

2) ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ፣

3) ሌ/ኮሎኔል ፍሰሃ ደስታ፣

4) ሻለቃ ብርሃኑ ባየህ፣

5) ሻምበል ለገሰ አስፋው፣

6) ጄኔራል ተስፋዬ ገ/ኪዳን፣

7) ካሳሁን ታፈሰ፣

8) ሻለቃ ታዴ ተድላ፣

9) ሌ/ኮሎኔል እንዳለ ተሰማ፣

10) ሻምበል ገሰሰ ወ/ኪዳን፣

Mengistu Trial

11) ሜ/ጄኔራል ውብሸት ደሴ፣

12) ሻለቃ ካሳዬ አራጋው፣

13) ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ፣

14) ሻምበል በጋሻው አታላይ፣

15) መቶ አለቃ ስለሺ መንገሻ፣

16) ሌ/ኮሎኔል ናደው ዘካሪያ፣

17) ም/መቶ አለቀ አራጋው ይመር፣

18) ሻለቃ ደጀኔ ወ/አገኘሁ፣

19) ም/መቶ አለቃ ደሳለኝ በላይ እና

20) ሻለቃ ሐዲስ ተድላ ናቸው።

 

ከነዚህ ውስጥ ካሳሁን ታፈሰ በማረሚያ ቤት ሕይወታቸው ስላለፈ ውሳኔው ያልተላለፈ ሲሆን፣ በመቶ አለቃ አክሊሉ በላይ ላይ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወሰነውን የዕድሜ ልክ እስራት ውሳኔ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አፅንቶታል።

 

በተጨማሪም ባለሥልጣናቱ በተመሳሳይ ሁኔታ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥር 3 ቀን 1999 ዓ.ም. የሰጠውን ውሳኔ ተቃውመው ይግባኝ አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት በዋለው የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ችሎት ይግባኛቸው ውድቅ ተደርጓል።

 

በደርግ ባለሥልጣናት ላይ ጥር 3 ቀን 1999 ዓ.ም. በከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ከሰጡት ሦስቱ ዳኞች መካከል አቶ ኑሩ ሰዒድ እና ሠለሞን እምሩ የተባሉት ሁለቱ ዳኞች በልዩነት የዕድሜ ልክ እስራት ሲወስኑ፤ አቶ መድህን ኪሮስ የተባሉት መሃል ዳኛ ደግሞ ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያምን ጨምሮ በ17 ባለሥልጣናት ላይ የሞት ፍርድ ውሳኔ አስተላልፈው ነበር።

 

ከነዚህ ዳኞች መካካል አቶ መድህን ኪሮስ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲያድጉ ሁለቱ ግን ወደ ክልል ከተሞችና አነስተኛ ጉዳዮች ወደሚታዩባቸው ችሎቶች ተዛውረዋል።

 

ነዋሪነታቸው በኢትዮጵያ የሆኑ አንድ የሕግ ባለሙያን በስልክ አነጋግረን “ዛሬ ውሳኔ የተሰጠባቸው ተከሳሾች ለሰበር ችሎት ይግባኝ ማለት ይችላሉ” ሲሉ ገልፀውልናል። አክለውም በሰጡት አስተያየት “ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ተብሎ ውሳኔ ለማግኘት አንድ ዓመት ከአምስት ወር አካባቢ ፈጅቷል። የሰበር ችሎቱ ደግሞ ምን ያህል ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችል መገመት ያስቸግራል። በዚህ ክስ የተከሰሱት ሰዎች የመጨረሻውን ውሳኔያቸውን ለማግኝት ሁለት አስርተ ዓመታት መጠበቃቸው አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ፣ የኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት ምን ያህል እየዘቀጠ መምጣቱን የሚያሳይ ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው” ብለዋል።

 

ኢህአዴግ ደርግን በጠብመንጃ አሸንፎ ሥልጣን ላይ የወጣበትን 17ኛ ዓመት ሊያከበር አንድ ቀን ተኩል ሲቀረው በዘር ማጥፋት የተከሰሱት የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ውስጥ 20ዎቹ በሞት ቅጣት እንዲቀጡ ተበይኖባቸዋል።

 

የዛሬውን የፍርድ ውሳኔ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ስልክ በመደወል እና በኢ-ሜይል ካሰባሰባቸው አስተያየቶች ውስጥ ጥቂቱን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።

 

“ውሳኔው አግባብ ነው። ቢያንስ የመቶ ሺህዎች ደም እንዲሁ በከንቱ እንዳልቀረ ለሌሎችም ትምህርት ሆኖ ያልፋል” - በቀይ ሽብር ወንድሟን ያጣች በስደት ነዋሪ

 

“ውሳኔው ትክክል ቢሆንም፤ እነኝህ ሰዎች ህዝብ ፈጅታችኋል፣ ገድላችኋል ተብለው በዘር ማጥፋት በኢህአዴግ መንግሥት የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው፤ ኢህአዴግም ሰዎች እየፈጀና እየገደለ ስለሆነ አጥፊዎቹና ተጠያቂዎቹ የዘመኑ ባለሥልጣናትም የሞት ፍርድ ሊፈረድባቸው ይገባል ማለት ነው። ከዚህ አንፃር መመልከቱም ይበጃል ባይ ነኝ” - በኢትዮጵያ የሚኖሩ አንድ የሕግ ባለሙያ (በስልክ)

 

“ሞት በቂ አይደለም! … በሺህዎች የሚቆጠሩን ህይወት አጥፍተዋልና ባጠፏቸው ልክ ሺህ ግዜ መሞት አለባቸው! …” - በጋሻው (ኢ-ሜይል)

 

“ውሳኔ ትክክል አይደለም! አብዛኞቹ ሰዎች አርጅተዋል። ከዚህ በኋላ፣ በተለይም ላለፉት 17 ዓመታት በእስር ሲማቅቁ ቆይተው፣ የገዛ ጓዶቻቸው ከአጠገባቸው በሞት ሲለዩዋቸውና ሲሸማቀቁ ስለኖሩና ስለተቀጡ፤ የሞት ቅጣት ቢፈፀምባቸው እነሱ የሟቾችን ሕይወት መመለስ አይቻልም። ወይንም የጠፋውን ጥፋት መመለስ በፍፁም አይቻልም። ይልቅስ አጋጣሚውን በመጠቀም ከበቀል ሊፀዳ የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸት ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ። …” - በአ.አ. የግል ባለሃብት

 

ለመረጃና ለግንዛቤ

ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ኢህአዴግ አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ ከፍተኛ የደርግ ባለሥልጣናቱን ጨምሮ በቀይ ሽብር እና በዘር ማጥፋት ይጠረጠሩ የነበሩ ግለሰቦችን ማሰር ጀመረ። በመቀጠልም ለዘር ማጥፋቱ ክስ ልዩ የዓቃቤ ሕግ አቋቋመ። ይህ የተቋቋመው ልዩ ዓቃቤ ሕግም እስከ ጥቅምት 1987 ዓ.ም. ድረስ ማስረጃዎችንና ምስክሮችን ሲሰበስብ ቆይቶ ጥቅምት 15 ቀን 1987 ዓ.ም. ክሱን መሰረተ።

 

በኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም መዝገብ ተከስሰው ከነበሩት ወደ 130 የሚጠጉ ግለሰቦች ውስጥ በሞትና በተለያዩ ምክንያቶች ቁጥራቸው ወደ 79 አካባቢ ደርሶ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ በብይን ወቅት አንድ ሰው ብቻ በነፃ መለቀቁ አይዘነጋም።

 

ጥር 3 ቀን 1999 ዓ.ም. ተሰይሞ የነበረው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ችሎት በሰጠው ፍርድ ከ23 ዓመት እስከ የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት መወሰኑ አይዘነጋም። ዳኞቹ ሁለት ለአንድ በሆነ ድምፅ ነበር ውሳኔውን የሰጡት። ዳኛ ኑር ሰዒድ እና ዳኛ ሠለሞን እምሩ በአንድ ወገን፤ በሌላ ወገን ደግሞ ዳኛ መድህን ኪሮስ።

 

ዳኛ ኑር እና ዳኛ ሠለሞን፤ ተከሳሾቹ ከ23 ዓመት እሰከ እዕሜ ልክ በሚደርሱ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሲወስኑ ለቅጣቱ ማቅለያ ያሰፈሩት ሃሳብ “የደርግ አባላቱ የበታች መኮንኖችና የወታደሮች ስብስብ የነበሩ ዝቅተኛ የትምህርት ችሎታ ያላቸው፣ የዝቅተኛ አመራር ላይ የነበሩት መንግሥትን ለመምራት የሚያስችል አቅም የነበራቸው ከዚህ በፊት በሕግ ያልተቀጡ፣ በወታደርነት አገራቸውን ያገለገሉ፣ በዕድሜ መግፋት በተለያዩ በሽታዎች በመሰቃየት ላይ የሚገኙና በፈፀሙት ድርጊት በመፀፀት ህዝቡን ይቅርታ ለመጠየቅ መድረክ እንዲዘጋጅላቸው መንግሥትን የጠየቁ መሆናቸውን” የሚል ነበር።

 

በዚህም መሠረት ፍርድ ቤቱም ቅጣቱ በቀል እንዳሆን የሚያርማቸውና በእስር ላይ ሆነው የተለያዩ ሙያዎች የቀሰሙና በቀሪ ዕድሜያቸው አዲስ ሕይወት ለመምራት የተዘጋጁ መሆናቸውን ችሎቱ የተገነዘበ በመሆኑ ከፍተኛውን የሞት ቅጣት አብላጫው ድምፅ የማይቀበለው መሆኑን በውሳኔው ግልጾ ነበር።

 

ከሁለቱ ዳኞች በሃሳብ የተለዩትና አንድ ድምፅ ብቻ የነበራቸው ዳኛ መድህን ኪሮስ ደግሞ “ተከሳሾቹ በፈፀሙት ወንጀል ያልተፀፀቱ፣ ወንጀሉን የፈፀሙት በከባድ ጥላቻና በሥልጣናቸው አለአግባብ በመገልገል ከ1967 ዓ.ም. እስከ 1972 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑ ሲታይ እና የጥፋተኝነት ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ የመፀፀት ሃሳብ መቅረቡ ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ሁለቱን ዳኞች ተቃውመው ነበር።

 

ዳኛ መድህን አክለውም “የዕውቀት ማነስና የዕድሜ መግፋት ሁኔታ በቅጣት ማቅለያነት ፍርድ ቤቱ ሊቀበለው አይገባም። በተከሳሾቹ ላይ ሊወሰንባቸው የሚገባው ከዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እስከሞት መሆኑን ሲኖርበት ወደ 23 ዓመት መውረዱ ሕጋዊ ምክንያት የለውም። በተከሳሾቹ ላይ ሊወሰን የሚገባው ቅጣት መለያየት የለበትም። ቅጣቱም እንደወንጀል ተሳትፏቸው መወሰን ይገባዋል” ሲሉ ከሁለቱ ዳኞች በሃሳብ ተለይተው ነበር።

 

ዳኛ መድህን በአዲስ አበባና የተለያዩ ክፍለ ሀገሮች ተከሳሶቹ ይመሯቸው የነበሩ በርካታ ተከሳሾች በዕድሜና ልክና በሞት የተቀጡ እንደ ደርግ አባላትነታቸው ወንጀሉ በስፋት እንዲፈፀም ያደረጉ መሆናቸውን አስተያየታቸውን በማቅረብ የፍርድ ቤቱ የቅጣት አወሳሰንም ወጥነት ባለው ሁኔታ መካሄድ አለበት ብለው ነበር።

 

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማሪያም አገሪቱን በሊቀመንበርነት በመምራት ላይ የነበረና የወንጀሉ አመንጪና ትዕዛዝ ሰጪ በመሆኑ ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ፣ ኮሎኔል ፍሰሃ ደስታ፣ ሻለቃ ብርሀኑ ባየህ፣ ሻምበል ለገሰ አስፋው፣ ሻለቃ ዲሽ ተድላ፣ ሻምበል ገሰሰ ወ/ኪዳን በነበራቸው የሥልጣን ኃላፊነትና የወንጀል ተሳትፎ በሞት መቀጣት አለባቸው ሲሉ ዳኛ መድህን ተቃውሟቸውን አስፍረው ነበር።

 

በመጨረሻም ቀሪዎቹ ተከሳሾችም የነበራቸውን የወንጀል ተሳትፎ ደረጃ በደረጃ በማስቀመጥ ከ25 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ፅኑ እስራት መቀጣት ነበረባቸው ሲሉ በድምፅ የተሸነፉት ዳኛ መድህን ኪሮስ ሃሳባቸውን ገልፀው ነበር።

 

ኢህአዴግ አዲስ አበባን የተቆጣጠረበትን 17ኛ ዓመት ሊያከብር ሁለት ቀን ያልሞላ ጊዜ ሲቀረው (ተነገወዲያ) የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተፈርዶባቸዋል። ከዚህም በኋላ ለሰበር ችሎት “ይግባኝ” የሚሉ ከሆነ የፍርድ ሂደቱ ምን ያህል ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል በእርግጥ የታወቀ ነገር የለም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ