የ23ቱን ስም ዝርዝር ይዘናል

Ethiopiaz Zare (ረቡዕ ግንቦት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. June 1, 2011)፦ በመጥፎነቱ የሚታወቀው በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግስት አመራሮች በእነ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለምሪያም ክስ መዝገብ ስር በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሰው የሞት ፍርድ የተወሰነባቸው የደርግ ባለስልጣናት የቅጣት ውሳኔ ወደ እድሜ ልክ መለወጡ ተገለጸ። 

 

ይሄው ዛሬ ረቡዕ በፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ይፋ የሆነው መግለጫ የቀድሞ ባለስልጣናት ምህረት ተደርጎላቸው የሞት ፍርዱ ወደ እድሜ ልክ እስራት እንደተለወጠ ተገልጧል። ምህረቱ በእስር የሚገኙትን 23ቱን እስረኞች የሚያካትት ሲሆን በዘግናኝ ጭፍጨፋዎች የሚታወቁትን መላኩ ተፈራንና ለገሰ አስፋውን የሚጨምር ከመሆኑም በላይ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ፍቅረስላሴ ወግደረስና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ፍስኃ ደስታ በምህረት ቅጣታቸው ዝቅ ከተደረገላቸው የቀድሞ ቱባ ባለ ስልጣናት መካከል እንደሚገኙ ይፋ ሆኗል።

 

የኢትዮጵያ የሚገኙ ሀይማኖት መሪዎች ባለስልጣናቱ በምህረት ይፈቱ ዘንድ ሙከራ በጀመሩ ሰአት በተለይ የቀይ ሽብር ኮሚቴ በመባል የሚታወቀውና የጭፍጨፋው ቀጥተኛ ተጠቂ የሆኑ ግለሰቦች ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው የሚታወቅ ሲሆን የምህረቱ ሂደት ችግር ገጥሞት እንደነበር ይታወሳል።

 

ወደ እድሜ ልክ የተለወጠውን የቅጣት ውሳኔ ለማስለወጥ የሀይማኖት መሪዎች ጥረት ማድረጋቸው ተገልጿል። ቅጣታቸው ዝቅ ከተደረገላቸውና ወደ እድሜልክ የተቀየረላቸው እስረኞች ፍቅረስላሴ ወግደረስ፣ ለገሰ አስፋው፣ መላኩ ተፈራ፣ ተስፋዬ ወልደስላሴ፣ ገስግስ ገ/መስቀል፣ ጀኔራል ለገሰ በላይነህ፣ አብዱቃድር መሀመድ፣ ጴጥሮስ ገብሬ፣ ስለሽ መንገሻ፣ ኮ/ል ናደው ዘካሪያስ፣ በጋሻው አታላይ፣ ሜ/ጄኔራል ውብሸት ደሴ፣ ኮ/ል ፍስሀ ደስታ፣ ኮ/ል እንዳለ ተሰማ፣ ኮ/ል ደበላ ዲንሳ፣ አርጋው ይመር፣ ደገኔ ወንድምአገኘው፣ እሸቱ ሸንቁጤ፣ ገሰሰ ወ/ኪዳን፣ ደሳለኝ በላይ፣ ልሳኑ ሞላ፣ አበበ እሸቱ፣ ብርሃኑ ማሞ እንደሆኑ ለማወቅ ችለናል።

 

የምህረት ሂደቱ ከግንቦት 20ቀን ጀምሮ የጸና እንደሚሆን ከመገለጹም በላይ በውሳኔው ተግባራዊነት መሰረት እስረኞቹ ባለስልጣናት በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ ከእስር ነጻ እንደሚወጡ ይገመታል።

 

በምህረቱና በቅጣት ማሰስተካከያው ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነነዘሩ ሲሆን በተለይ የቀድሞ ባለስልጣናቱ ቅጣት መሻሻል የለበትም በሚሉ ወገኖችና እስካሁን የቆዩበት የእስር ጊዜ በቂ ስለሆነ መለቀቀቅ አለባቸው በሚሉ ወገኖች መካከል የተለያዩ የማሳመኛ ነጥቦችን በመጥቀስ የሚከራከሩ እንዳሉ ለመረዳት ተችሏል። በፍትህና በምህረት ሂደቱ አንጻር እና የዋናው ተከሳሽ ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያምን በሚመለከት በሚያቀርቡ ጥያቄዎች ዙሪያ የህግ ባለሙያዎች ሙያዊ ትንታኔ በመስጠት ላይ ናቸው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ