Fidel Castro

ኢትዮጵያ ዛሬ (ቅዳሜ ኅዳር ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Nov. 26, 2016)፦ የቀድሞው የኩባ ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮ በዘጠና ዓመታቸው ትናንት ማረፋቸው ተሰማ። ፊደል ካስትሮ ኩባን ለ፵፱ (49) ዓመታት ከመምራታቸውም ባሻገር በአብዮተኝነታቸውና በታጋይነታቸው በዓለም ላይ ታዋቂ የነበሩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ወዳጅና ረዳት እንደነበሩም ይታወሳል። ኩባ የቀድሞ ፕሬዝዳንትዋን ሕልፈተ ሕይወት አስመልክታ ለዘጠኝ ቀናት ብሔራዊ የኀዘን ቀን አውጃለች።

ፊደል ካስትሮ በ፲፱፻፶፱ (1959) እ.ኤ.አ. በኮምዩኒስት አብዮት ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ እስከ ፳፻፰ (2008) ኩባን ሲመሩ የቆዩ ሲሆን፣ በ፳፻፰ (2008) ሥልጣናቸውን ለታናሽ ወንድማቸው ለራዑል ካስትሮ አስተላልፈዋል። ፊደል ከዩናይት ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ጋር በነበራቸው አለመግባባት እና የርዕዮተ ዓለም ልዩነት፤ በተለይም ከአሜሪካ በኩል ለመቁጠር ለሚያዳግቱ ጊዜያት የተቃጡባቸውን የመግደል ሙከራዎች እንዳመለጡ ይታወሳል።

ትናንት ሌሊት የወቅቱ የኩባ ፕሬዝዳንትና የፊደል ካስትሮ ታናሽ ወንድም ራዑል በአገሪቱ ቴሌቭዥን ቀርበው፤ ”ጥልቅ ኀዘን ተሰምቶኝ በዚህ ሰዓት የቀረብኩት፣ ለሕዝባችን፣ በደቡብ አሜሪካና በዓለም ለምትገኙ ወዳጆቻችን፤ ዛሬ ኖቨምበር ፳፭ ቀን ፳፻፲፮ (25 November 2016) ከምሽቱ ፬፡፳፱ (10.29pm) የኩባ አብዮት መሪ ፊደል ካስቶ ከዚህ ዓለም እንደተለዩ ልነግራችሁ ነው” በማለት ለዓለም ተናግረዋል። ፊደል ለረዥም ዓመታት ጤናቸው ታውኮ ስለነበር የሕክምና ክትትል ሲደረግላቸው እንደነበር ይታወቃል።

ፊደል ካስትሮን ከዚህ ዓለም መለየት አስምልክቶ፤ የደቡብ አፍሪካው መሪ ጃኮብ ዙማ ፊደል አፓርታይድ ከደቡብ አፍሪካ እንዲወገድ ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን አስተላልፈዋል። የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ ”የምዕተ ዓመቱ የዘመናዊ ታሪክ ምልክት/አሻራ” ሲሉ ለፊደል ያላቸውን ክብር ከመግለጣቸውም ባሻገር፤ ”ፊደል ካስትሮ የራሽያ ጽኑ ወዳጅና ታጋይ ነበሩ” ብለዋል።

የእንግሊዙ ሌበር ፓርቲ መሪ የሆኑት ጀርሚ ኮርቢን፤ ”ካስትሮ በሕይወታችን ውስጥ ታላቅ ቦታ ያለው ሰው ነው” ያሉ ሲሆን፣ አክለውም ”ታላቅ ጀግና” በማለት አሞካሽተዋቸዋል። ከዚህም በላይ በዓለም ላይ የነበራቸውን ጉልህ ድርሻ እንዲሁም በኩባ የጤና እና የትምህርት ሥርዓት ላይ ላመጡት ታላቅ ለውጥ ያላቸውን አክብሮት ጀርሚ ኮርቢን አልሸሸጉም።

ፊደል ካስትሮ በዓለም ከሚታወቁባቸው ሥራዎቻቸውና አቋማቸው ውስጥ ፀረ-ቅኝ አገዛዝ አንዱና ዋንኛው እንደነበር ይታወቃል። በተለይም በአፍሪካና በደቡብ አሜሪካ በርካታ አገሮችን ከቅኝ ግዛትነት በማላቀቁም ሆነ ሶሻሊስታዊ አብዮቶችን በማገዝ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸው አይዘነጋም።

ደርግ አፄ ኃይለሥላሴን በኃይል ከሥልጣን ባወረደበትና ሥልጣኑን በተቆጣጠረበት ማግስት፣ በመሐመድ ሲያድ ባሬ መሪነት የሶማሊያ ጦር ኢትዮጵያን ወርሮ እንደነበር አይዘነጋም። በወቅቱ ኩባ የሲያድ ባሬ ወዳጅ የነበረች ሲሆን፣ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ፊደል አቋማቸውን በመቀየር ወዲያው ለኢትዮጵያ የወቅቱ መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወታደራዊ የምክርና የጦር እርዳታ መስጠታቸው ይታወሳል።

ከጦርነቱ ማብቃት በኋላም ኩባ የተለያዩ እርዳታዎችን ለኢትዮጵያ ስትሰጥ ከመቆየትዋም ባሻገር፤ በኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ወላጆቻቸውን ላጡ ሕፃናት ነጻ የትምህርት ዕድል በመስጠት በርካታ ሕፃናትን ኩባ በመውሰድ አሳድጋና አስተምራ ወደአገራቸው በመላክ የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ወዳጅ እንድትሆን ፊደል ካትሮ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸው አይዘነጋም።

በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል የፊደል ካስትሮ ወዳጅ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ትመኛለች።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ