Ato Kuma DemeksaEthiopia Zare (ማክሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2000 ዓ.ም. May 20, 2008)፦ ኢህአዴግ ባለፈው ሚያዝያ 5 እና 12 ቀን 2000 ዓ.ም. በተካሄዱት ምርጫዎች ብቻውን ተወዳድሮ ካሸነፈ በኋላ በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ምክር ቤት መስራች ጉባዔውን አካሂዶ ከንቲባውንና ቀሪዎቹን ባለሥልጣናት መምረጡን ከአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር ዘገበ።

 

ጉባዔው የአዲስ አበባ ከንቲባ አድርጎ የሾማቸው አቶ ኩማ ደመቅሳን ሲሆን፣ ለምክትል ከንቲባነት ሁነው የተሾሙት ደግሞ አቶ ከፍያለው አዘዘ መሆናቸው ታውቋል።

 

ከእነዚህም ሌላ ወ/ሮ ስንቅነሽ አጣለ የመስተዳድሩ አፈ ገባዔ ሆነው ሲሾሙ፣ አቶ ኤሊያስ ሰዒድ ደግሞ ምክትል አፈ ጉባዔ ሁነው መሾማቸውን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ይጠቁማል። የመስተዳድሩ ዋና ፀሐፊ ሆነው የተመረጡት ደግሞ ወ/ሮ ነገደ ለማ መሆናቸው ታውቋል።

 

አቶ ኩማ ደመቅሳ ቀደም ሲል የኦህዴድ (የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት) ሊቀመንበር፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር አይዘነጋም። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የሀገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር እንደሆኑ ይታወቃል።

 

የአዲስ አበባ ምክር ቤት 138 መቀመጫዎች ሲሆሩት፣ በሚያዝያ 5 በአዲስ አበባ በተደረገው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ 137ቱን ኢህአዴግ እንዳሸነፈና ቀሪውን አንዱን መቀመጫ ደግሞ ምርጫ ቦርድ የቅንጅትን ሕጋዊ እውቅና የሰጠው በአቶ አየለ ጫሚሶ የሚመራው ቅንጅት ሟች (በሕይወት የሌሉት) ተወዳዳሪ ወ/ሮ ቦድዲት አንተነህ ማሸነፋቸውን ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ አይዘነጋም።

 

በምርጫ 97 የአዲስ አበባ ምክር ቤትን 137 መቀመጫዎች ቅንጅት፣ አንዱን ደግሞ ኢህአዴግ ማሸነፋቸው አይነጋም። በወቅቱም ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የከተማዋ ከንቲባ ሁነው ተመርጠው ነበር። የቅንጅት አመራሮች ወደ እርስ ከተወረወሩ በኋላ የከተማዋ ባለአደራ ከንቲባ ተደርገው በጠ/ሚኒስትሩ ተሹመው ከተማዋን ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያስተዳድሩ የነበሩት አቶ ብርሃኔ ደሬሳ እንደነበሩ ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ