ልዩ ሪፖርታዥ

Ethiopia Zare (ዓርብ ሚያዝያ 10 ቀን 2000 ዓ.ም. April 18, 2008)፦ “ምርጫ” የሚለው ቃል በኢትዮጵያውያኖች ዘንድ ሲነሳ ትውስታ የሚፈጥረው “ምርጫ 97” ነው። የምርጫ 97 ትዝታ ለሚቀጥሉት … ዓመታት ከኢትዮጵያውያኖች የትውስታ ሣጥን ይጠፋል ተብሎ አይታሰብም።

 

 

የአዲስ አበባ የካፌ በረንዳዎች በጋዜጣ አንባቢ የተጥለቀለቁበት፣ በኢትዮጵያ ፕሬስ ታሪክ ጋዜጦች ብዙ ሺህ ኮፒ (ከመቶ ሺህ በላይ) የሸጡበት፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በርካታ ተመልካች ያገኘበት፣ የታክሲና የጎዳና ላይ ውይይቶች የተሟሟቁበት፣ መስቀል አደባባይ ታላላቅ የሕዝብ ሰልፎችን ያስተናገደበት የውጭና የአገር ውስጥ ታዛቢዎች በመላ አገሪቱ ምርጫውን ለመታዘብ የተራወጡበት አስደማሚ ሁኔታ ነበር።

 

 

በወቅቱ ግንቦት 7 ቀን በመላ አገሪቱ በተደረገው ምርጫም የምርጫ ጣቢያዎች ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በሰልፍ የተጨናነቁበት፤ በቆጠራው ወቅትም ከታዛቢ ውጭ ያለው መራጭ ሕዝብ ጭምር አብሮ በማምሸት የቆጠረበት፣ በአጠቃላይ ሁሉን ያነቃቃና ያነቃነቀ ምርጫ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

 

 

ከውጤቱ በኋላ እስከ ሚያዝያ ወር 2000 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሟያ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የክፍለ ከተማ አስተዳደርና የቀበሌ አስተዳደር ምርጫ ድረስ አገሪቱ በርካታ ሁኔታዎችን ያስተናገደች ቢሆንም የዛሬው የ”ምርጫ” ዘገባችን በሚያዝያ 5 እና 12 ቀን ምርጫ ላይ ይሆናል።

 

 

በሚያዝያ ወር 2000 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሟያ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የክልልና የዞን፣ የወረዳ ምክር ቤቶች፣ የክፍለ ከተማና የቀበሌ አስተዳደር ምርጫ እንደሚደረግ በመንግሥት ሚዲያ መገለጹ የሰነበተ ወሬ ሲሆን፣ ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ ደግሞ ሕብረትና ኦፌዴን “ገና ከአሁኑ ወከባ እየደረሰብን ነው” ሲሉ መግለጫ ሲያወጡ ሰንብተዋል።

 

 

ቦርዱም ስለምርጫው በመንግሥት ሚዲያ ሲያስነግር ከቆየ በኋላ ለምርጫው ሁለት ቀናት ሲቀሩት፤ የተመዘገበው ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ እንዲመርጥ ጥሪ አስተላልፏል። 26 ሚሊዮን ሕዝብ በመራጭነት መመዝገቡን፣ 32 የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ 3 ሚሊዮን 119 ሺህ 194 ዕጩ ማቅረባቸውንም ይፋ አድርጓል።

 

 

ለመራጭነት የተመዘገበው ሕዝብ ያዋጣኛል የሚለውን በመለየት መሪውንና የሚያስተዳድረውን እንዲመርጥ ጥሪ አቅርቧል። እሁድ ዕለት ሚያዝያ 5 ቀን 2000 ዓ.ም. (April 13, 2008) የተደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሟያ ምርጫ 14 ወንበሮች ነበሩት። በምርጫ 97 በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 23 ወንበሮችን ቅንጅት አሸንፎ የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ዘጠኙ ፓርላማውን ሲቀላቀሉ 14ቱ ደግሞ ሳይገቡ ቀርተዋል።

 

 

በወቅቱ በምርጫ አሸንፈው ፓርላማውን ያልተቀላቀሉት የቅንጅት ተመራጮች፤ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል በወረዳ 23፣ ዶክተር ኃይሉ አርኣያ በወረዳ 10፣ ዶክተር ታዲዮስ ቦጋለ በወረዳ 4፣ ዶክተር ሽመልስ ተክለ ጻድቅ በወረዳ 19፣ ዶክተር ሙሉዓለም ታረቀኝ በወረዳ 12/13፣ አቶ ክፍሌ ጥግነህ በወረዳ 20፣ ሻለቃ አድማሱ መላኩ በወረዳ 18፣ ፓስተር ፀሐይ ታደሰ በወረዳ 15፣ አቶ አሥራት ጣሴ በወረዳ 16፣ አቶ ፈጠነ ተሾመ ወረዳ 2/4፣ አቶ በድሩ አደም ወረዳ 7 እና አቶ ታሪኩ ደመላሽ ገለታ በወረዳ 25 አሸናፊ የነበሩ አንድ ግለሰብ ናቸው። እነዚህ ተመራጮች ፓርላማውን ያልተቀላቀሉ በመሆናቸው በምትካቸው ማሟያ ምርጫ ተደርጓል። በምርጫ 97 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ከነበሩ 138 ወንበሮች በአንዱ ላይ ብቻ ዕጩ ባለመቅረቡ ወንበሩ በኢህአዴግ ዕጩ ከመያዙ በስተቀር 137 ወንበሮችን አሸንፎ የነበረው ቅንጅት የከተማውን ምክር ቤት ለመረከብ ባለመቻሉ በቦታው ምርጫው ተካሂዷል።

 

 

ለዚህ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሟያና ለከተማ አስተዳደር ምርጫ ዕጩ ያቀረቡ የ15ቱ ፓርቲ እጩዎች ቁጥር በድምሩ 406 ነው። ኢዴኃሕ (የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት) ለምርጫው ያቀረባቸውን 27 ዕጩዎች ይዞ በመውጣቱ 379 ዕጩዎች ለምርጫ ቀርበው ነበር። በኢህአዴግ በኩልም ጠቅላላ 152 ዕጩዎችን አቅርቧል። በተጨማሪም 28 ዕጩዎች የግል ተወዳዳሪ ሆነዋል።

 

 

በጠቅላላው 379 ዕጩዎችን ይዘው ከቀረቡት 15ቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከኢህአዴግ እኩል 152 ዕጩዎችን ያቀረበው መኢብን፤ የፓርቲው ሊቀመንበር ቤተሰቦች በዕጩነት መቅረባቸው ተዘግቧል።

 

 

“ህዳሴ” በተባለው የኢህአዴግ አዲስ አበባ ኮሚቴ በሚያዘጋጀው ጋዜጣ ላይ “ንክኪ የሌለው የቤተሰብ ፓርቲ!” በሚል ባስነበበው ጽሁፍ ላይ በአዲስ አበባ ለፓርላማ ማሟያ መኢብን ካቀረባቸው 14 ተወዳዳሪ ዕጩዎች መካከል አንዱ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ መስፍን ሽፈራው ሲሆኑ፣ ሦስቱ የአቶ መስፍን እህቶችና ሦስቱ ደግሞ የአቶ መስፍን የእህት ልጆች መሆናቸውን ነው።

 

 

አቶ መስፍን ሽፈራው ግዛው በወረዳ 12 እና 13፣ ወይዘሮ ይምጡ በዝና ሽፈራው ግዛው ወረዳ 24፣ ወይዘሮ ሐረገወይን ሽፈራው ግዛው ወረዳ 15 እና ወይዘሮ ምሥራቅ ሽፈራው ግዛው የወረዳ 12 ተወዳዳሪ፣ በአጠቃላይ አራት ወንድምና እህት ከአንድ ቤትና ከአንድ ፓርቲ ዕጩ መሆናቸውን ጋዜጣው አስፍሯል።

 

 

በተጨማሪም የአቶ መስፍን ሽፈራው የእህት ልጆች ወይዘሮ መሰለች ቶማስ ወረዳ 25፣ ወይዘሪት ሀገሬ ቶማስ ወረዳ 18 እና ወይዘሪት ሊሻን ቶማስ ወረዳ 19 ዕጩ ሆነው ቀርበዋል ሲል ጋዜጣው ያትታል።

 

 

ከላይ በተዘረዘረው ሁኔታ ዕጩ የቀረበበትን የሚያዝያ 5 ምርጫ በአዲስ አበባ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎችን ተዟዙረን ተመልክተን ነበር። የእሁድ ዕለቱን ምርጫ፤ ጠቅለል አድርጎ በአንድ አንቀጽ ማስቀመጥ ይቻላል - “ምርጫ ጣቢያው ሠላም የሰፈነበት፣ በፀጥታ የተሞላ፣ በርካታ ሰልፎችን ያላስተናገደ፣ ሲነጋጋ የጀመረ፣ ምርጫ ጣቢያዎችን ያላጨናነቀ፣ በጉጉት ያልተጠበቀና ፉክክር ያልታየበት ምርጫ ነበር።”

 

 

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ ግን ምርጫው በኢትዮጵያ ምርጫ ታሪክ ውስጥ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሠላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ እንደነበር አስታውቋል።

 

 

በሌላ በኩል እስካሁን በተደረጉ ምርጫዎች አቤቱታ እያሰማም ቢሆን ሲሳተፍ የቆየው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት (ኢዴኃሕ) ለመጀመሪያ ጊዜ ምርጫውን አቋርጦ ወጥቷል።

 

 

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ከምርጫው የወጡበት በርካታ ምክንያቶች እንዳሏቸው የገለጹ ቢሆንም ዋናውና በቂ ምክንያት ነው ያሉት “የኢህአዴግ አባላትና ኢህአዲገኞች የምርጫውን ደህንነት አደጋ ላይ ስለጣሉት ነው” ብለዋል።

 

 

“አምስት የምርጫ አስፈፃሚዎችና አምስት ምርጫ ታዛቢዎችን በአጠቃላይ 10 ታዛቢዎችን በጋራ ሊመረጥ ሲገባ አስሩም የኢህአዴግ ካድሬዎች እንዲሆኑ ከተደረገ በኋላ ከእኛም አንድ ከኢህአዴግም አንድ ታዛቢ እንዲኖረን ሲደረግ 11 ለአንድ ሆኖብናል። ትንቅንቁ ከአቅም በላይ በመሆኑም ምርጫውን ጥለን ለመውጣት ተገደናል” ብለዋል ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ።

 

 

ቦርዱ ለዚህ የሰጠው ምላሽ፤ “የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት (ኢዴኃሕ) ከፍተኛ አመራሮች ተጨባጭነት በሌላቸውና አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች ምርጫው ሁለት ቀናት ብቻ ሲቀሩት ከምርጫ ራሱን ማግለሉን መግለጹ ከአንድ ኃላፊነት ሊሰማው ከሚገባ የፖለቲካ ድርጅት ከፍተኛ አመራር የማይጠበቅ ነው” ብሎታል።

 

 

ፓርቲው ያቀርባቸው የነበሩት አቤቱታዎችና ክሶች ተጨባጭ ያልሆኑና በማስረጃ ያልተደገፉ መሆናቸውን ጠቅሶ እንደውም 10 ዓመት ያልሞላቸው ዕጩዎች ከሕግ አግባብ ውጪ እንዲመዘገቡለት ሲጠይቅ ውድቅ እንደተደረገበት እንዳውም ፓርቲው 10 ሺ 115 ዕጩዎችን በቅፅ 04 መዝገብ ላይ አስፍሮ “6 ሺህ ዕጩዎችን አስመዝግቤያለሁ” እያለ መግለጫ መስጠቱን ቦርዱ አብራርቷል።

 

 

ፓርቲው ራሱን ለማግለል ቀደም ሲል የተለያዩ ሰበቦችን ሲደረድር መቆየቱን ቦርዱ ጠቅሶ “በምርጫው ሂደት ላለመቀጠል ወስኛለሁ” ያለባቸው ምክንያቶችም ውስጣዊና ውጫዊ ድክመቶችን ለመሸፈን ዓላማ ያደረጉ ናቸው ሲል አስፍሯል።

 

 

ቦርዱ የሰጠውን አስተያየት በሚመለከት የሕብረቱ አመራሮች እንደመለሱት “አሁን ያለው ቦርድ ስብዕናውን ጥያቄ ውስጥ የሚከትበት ነው። እኛ ዕጩ ያስመዘገብነው ከ20 ሺህ በላይ ነው፣ ዝርዝር ስጡን ብለን አንድ ወር ደጅ ጠንተናል። በመጨረሻ መልስ የሚሰጠን ስናጣ በታዛቢዎቻችን አማካይነት በትግል ተመዝግበው ዝርዝራቸው እጃችን ላይ ያሉትን ነው የገለጽነው። ቦርዱ እንዲህ ዓይነት መግለጫ የሚሰጠው የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡን ለማምታታት ብለው ነው” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

 

 

“ምርጫን ጥሎ መውጣት” የትግል ስልት ነው ብሎ እንደማያምንና በምርጫው እስከመጨረሻ እንደሚሳተፍ ሲገልጽ የቆየው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) በሚያዝያ 5 ቀን ምርጫ ከተሳተፈ በኋላ ከሚያዝያ 12 ምርጫ ራሱን ማግለሉን ይፋ አድርጓል።

 

 

የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከምርጫ የወጡበትን ምክንያት እንደገለጹት በምርጫው ለመሳተፍ ከገቡ በኋላ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ጥለው ለመውጣት መገደዳቸውን ተናግረዋል።

 

 

“ከአቅማችን በላይ ነው” ያሉት ምኑን እንደሆነ ተጠይቀው ታዛቢዎቻቸውን የኢህአዴግ ካድሬዎች እንዳሰቃዩዋቸው፣ የምርጫ ቦርድ ባጅ (መለያ መታወቂያ) ይዘው ሲሄዱ ከድርጅታችሁ ደብዳቤ አምጡ እንደተባሉ፣ እሱን ለማምጣት ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ እንደፈጀባቸው፣ ሲመለሱ ደግሞ ኮሮጆዎች ሞልተው እንደጠበቋቸው፣ በዚያም ሲከራከሩ ወደ ሦስት የሚጠጉ ታዛቢዎቻቸውን እንዳሰሩባቸው አቶ ቡልቻ ተናግረዋል።

 

 

ቦርዱ ከትናንት በስቲያ ኦፌዴንን በሚመለከት ባወጣው መግለጫም፤ ኦፌዴን ደረሱብኝ የሚላቸውን ችግሮች በማስረጃ አስደግፎ በዝርዝር ማቅረብ አለመቻሉን፣ ፓርቲው ዘንድሮ በሚደረገው የማሟያ ምርጫ በጠቅላላው በመላ ሀገሪቱ 180 ዕጩዎችን፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ደግሞ 16 ዕጩዎችን ማቅረቡን ጠቅሷል።

 

 

ሚያዝያ 5 ቀን 2000 ዓ.ም. በተካሄደው የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ከተሳተፈ በኋላ ከሚያዝያ 12ቱ ምርጫ ራሱን ማግለሉ፤ እሁድ የተካሄደውን የአካባቢና የማሟያ ምርጫ ውጤት በወኪሎቻቸው አማካይነት ከገመገሙ በኋላ በቀጣይም ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የምርጫ ውጤት ከወዲሁ በመተንበይ፤ ለፕሮፖጋንዳ ሥራ ሲሉ ራሳቸውን አግልለዋል ሲል ቦርዱ መግለጫ ሰጥቷል።

 

 

የቀረበባቸውን የቦርዱን አስተያየት በሚመለከት አቶ ቡልቻ ተጠይቀው ሲመልሱ “ምርጫ ቦርድ 26 ሚሊዮን መራጭ ተመዘገበ ያለው ውሸት ነው። ከ4 እስከ 5 ሚሊዮን ቢሆን ነው። ለምርጫ የወጣውም የኢህአዴግ ካድሬ እንጂ ሕዝቡ አይደለም። ሕዝቡማ አኩርፎ ቤቱ ተቀምጧል። በአጠቃላይ እኛ በምርጫው መሳተፍ አቅቶናል ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ አይደለም” ብለዋል።

 

 

በሌላም በኩል የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወሕዴግ) ለምርጫ በቀረበበት 7 የምርጫ ጣቢያዎች በታዛቢነት ያቀረባቸው 14 ሰዎች ስለተባረሩበት ምርጫው እንደገና እንዲካሄድ ነው ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ አስገብቷል። እንደ ፓርቲው አቤቱታ ከሆነ በዳሞት ኮሬ ወረዳ በሰባቱም ምርጫ ጣቢያዎች በደል የፈጸሙበት የዳሞት ኮሬ ወረዳ የምርጫ አስፈጻሚ የሆኑ አንድ ግለሰብ ናቸው።

 

 

እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2000 ዓ.ም. በመላ አገሪቱ ከሚደረገው የክፍለ ከተማና የቀበሌ አስተዳደር ምርጫ የአዲስ አበባው የፓርቲዎች ዕጩ አሰላለፍ ምን ይመስላል የሚለውን ቦርዱ “ለውድድር የቀረቡ የፓርቲዎች ዝርዝር” በሚል ያሰራጨው መረጃ እንደሚያስረዳው፤ ምርጫው 29 ሺህ 700 ዕጩ ተወዳዳሪዎች ከ27 ዕጩ ተወዳዳሪዎች ጋር ይፋለማሉ።

 

 

ለአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ አስተዳደርና ለቀበሌ አስተዳደር 32 የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን በማቅረብ ተሳትፈዋል በሚል ቦርዱ በተደጋጋሚ መግለጫ ሲሰጥ ቆይቷል።

 

 

“በሚያዝያ ወር 2000 ዓ.ም. ለሚካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ማሟያና የክልልና የዞን፣ የወረዳ ምክር ቤቶች ምርጫ በአዲስ አበባ ከተማ ለውድድር የቀረቡ ፓርቲዎች ዝርዝር” በሚል ዝርዝር የቀረበው መረጃ እንደሚያስረዳው 16 ፓርቲዎችና በ17ኛ ደረጃ የግል ተወዳዳሪዎች ስም ተጠቅሷል።

 

 

ነገር ግን በክፍለ ከተማ አስተዳደርና ለቀበሌ አስተዳደር ከ12 የግል ተወዳዳሪዎች ዕጩ ያቀረቡት ፓርቲዎች ኢህአዴግ፣ ኢዴአፓ-መድኅን እና ኦፌዴን ሲሆኑ፣ ኦፌዴን ከዚህ ምርጫ ራሱን ማግለሉን ይፋ አድርጓል።

 

 

ኦፌዴን ከዚህ ምርጫ ራሱን በማግለሉ ምክንያት፣ የፊታችን እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2000 ዓ.ም. (April 20, 2008) የሚደረገው የክፍለ ከተማ አስተዳደር ምርጫ የሚኖረው የኢህአዴግና የኢዴአፓ-መድኅን ብቻ ይሆናል። ኢህአዴግ 2 ሺህ 970 ዕጩ ኢዴአፓ-መድኅን 13 ዕጩ አቅርበው ይፋለማሉ። ለቀበሌ አስተዳደር ምርጫም ኢህአዴግ በ29 ሺህ 700 ዕጩዎች ከፓርቲዎች ብቻውን ሆኖ 12 የግል ተወዳዳሪዎች ጋር ይወዳደራል።

 

 

በፊታችን እሁድ በሚደረገው የአዲስ አበባ ከተማ የክፍለ ከተማና የቀበሌ አስተዳደር ምርጫ ከኢህአዴግ ጋር ብቸኛ ተወዳዳሪ ፓርቲ የሆነውን የኢዴአፓ-መድኅን ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው ስለምርጫው ፉክክር ተጠይቀው፣ “እኛ ተፎካካሪ ፓርቲ አይደለንም። ቀደም ሲል በተለያየ ጊዜ ስንገልጸው እንደቆየነው በዚህ ምርጫ የተሳተፍነው ተወዳድረን ለማሸነፍና ተፎካካሪ ሆነን ለመቅረብ ሳይሆን ለምርጫ ያለንን አክብሮት ለመግለጽ ብለን ነው” ብለዋል።

 

 

አያይዘውም በዚህ ምርጫ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ 0.1 በመቶ በመሆኑ ቀድሞውንም ቢሆን ኢህአዴግ 99.9 በመቶ ያሸንፋል በሚል መግለጫ ሰጥተው እንደነበር ተናግረዋል።

 

 

እሁድ ሚያዚያ 12 ቀን በሚደረገው የክፍለ ከተማ አስተዳደርና የቀበሌ አስተዳደር ምርጫ ኢህአዴግ ባቀረባቸው 32 ሺ 670 ዕጩዎችና ከ12 የግል ተወዳዳሪዎች ጋር የምርጫ ፍልሚያ ያደርጋል።

 

 

ኢህአዴግ “ብቻውን” በሚያስብል ሁኔታ የሚደረግ ምርጫ እንዴት የ“ምርጫ” ስያሜ ይሰጠዋል? ሠላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዴት ሊባል ይችላል? በሚል ለቦርዱ ለቀረበለት ጥያቄ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መንገሻ ሲመልሱ፤ “… ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ወንበሮቹ ክፍት ሆነዋል የከለከላቸው አካል የለም። ኢህአዴግ የራሱን ዕጩ ከማቅረብ ውጪ ሌሎቹ እንዳያቀርቡ ያደረገው ተፅዕኖ የለም …” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

 

 

ዞሮ ዞሮ ኢህአዴግ ብቻውን የሚወዳደርበት ምርጫ እንዴት “ምርጫ” ሊባል ይችላል? በሚል ተጠይቀው፤ “አንድ ፓርቲ ያቀረባቸውን ዕጩ ተወዳዳሪዎች ሌላ ተፎካካሪ ኖረም አልኖረም የቀረበው ፓርቲን መቀበል አለመቀበሉን ሕዝብ በምርጫ ካርዱ ድምጹን ሰጥቶ ማረጋገጥ አለበት” ሲሉ አቶ ተስፋዬ መልስ ሰጥተዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ