የቀን መቁጠሪያ በማሳተማቸው የተከሰሱትን ፍ/ቤቱ በነፃ አሰናበታቸው
Ethiopia Zare (ኀሙስ መጋቢት 18 ቀን 2000 ዓ.ም. March 27,2008)፦ የቀን መቁጠሪያ በማሳተም አሰራጭተዋል በሚል ተከሰው የነበሩት የአውሮፓ ሕብረት የሕግ ባለሙያዋ፣ የፋንቱ ሱፐር ማርኬት ባለቤት ልጅና አንድ ሌላ ግለሰብ ትናንት በዋለው ችሎት ክሱ እንደተነሳላቸው የፍርድ ቤት ምንጮቻችን ከአዲስ አበባ ገለጡ።
በእስር ላይ የነበሩትን የቀድሞ የቅንጅት አመራሮች ከእስር እንዲፈቱ የሚጠይቅ የቀን መቁጠሪያ አሳትማችሁ ከነሐሴ 1 ቀን 1998 ዓ.ም. እስከ መስከረም 25 ቀን 1999 ዓ.ም. በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ሰዎች አስፈርመዋል በሚል ነበር ዓቃቤ ሕግ የክስ መሰረቱን የጣለው።
ትናንት የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 11ኛ ወንጀል ችሎት ዓቃቤ ሕግ ምስክር ለማሰማት ባስያዘው ቀጠሮ መሠረት ተሰይሞ የነበረ ቢሆንም፤ ምስክሮች ለዓቃቤ ሕጉ ሳይቀርቡለት ቀርተዋል። ዓቃቤ ሕግ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አማካኝነት ለምስክሮች የመጥሪያ ደብዳቤ ቢያስልክም ምስክሮቹን ማግኘት አለመቻሉን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
ተከሳሾቹ ወ/ት ያለምዘውድ በቀለ (የአውሮፓ ሕብረት የሕግ ባለሙያ የሆኑት)፣ አቶ አለማየሁ ፋንቱ (የፋንቱ ሱፐር ማርኬት ልጅ) እና አቶ አዳነ ሸዋ የዓቃቤ ሕጉ ምንም አይነት ምስክር ሊያቀርብባቸው ባለመቻሉ ክሱ እንዲነሳላቸው ጠይቀው፤ ፍርድ ቤቱ ክሱን አንስቶላቸዋል።
ሦስቱም ተከሳሾች ዓቃቤ ሕግ ከከሳቸው በኋላ ፍርድ ቤት ቀርበው የአምስት ሺህ ብር ዋስ እንዲጠሩ ተፈቅዶላቸው ገንዘቡን ካስያዙ በኋላ ጉዳያቸውን ከውጭ ሆነው ሲከታተሉ ነበር የቆዩት። ትናንት ፍርድ ቤቱ በነፃ ሲያሰናብታቸው ለዋስትና ያስያዙት ገንዘብ ተመላሽ እንዲሆንላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።



