ኢትዮ ቴሌኮም ከታክስ በፊት 28.1 ቢሊዮን ብር አተረፈ
ኢትዮ ቴሌኮም
ይህ ትርፍ ከሁሉም የመንግሥት ድርጅቶች ካገኙት ይበልጣል
ለውጭ እዳ 10.2 ቢሊዮን ብር ከፍሏል
15.3 ቢሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ አድርጓል
ኢዛ (ረቡዕ መስከረም ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 23, 2020)፦ በመንግሥት ይዞታ ሥር ከሚገኙት ግዙፍ ተቋማት መካከል አንዱ የኾነው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በተጠናቀቀው 2012 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 28.1 ቢሊዮን ብር ማትረፉን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው ዛሬ ረቡዕ መስከረም 13 ቀን 2013 ዓ.ም. የኢትዮ ቴሌኮም የ2012 አፈጻጸምን ከገመገመ በኋላ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ ኢትዮ ቴሌኮም በ2012 ከታክስ በፊት 28.7 ቢሊዮን ብር ለማትረፍ አቅዶ አፈጻጸሙ 28.1 ቢሊዮን ብር ኾኗል። ይህም የእቅዱን 98 በመቶ ማሳካቱን ያሳያል ተብሏል። ይህ የትርፍ መጠን በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ ትርፍ ያስገኘ የመንግሥት ድርጅት አድርጎታል። እስከዛሬው ዕለት ድረስ ትልቁን ትርፍ ያስመዘገበው የንግድ ባንክ የነበረ ሲሆን፣ ባንኩ 14 ቢሊዮን ብር ማትረፉ አይዘነጋም።
ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን ትርፍ ያገኘው ከተለያዩ አገልግሎት ካገኘው 47.7 ቢሊዮን ብር ውስጥ ነው። በበጀቱ ዓመቱ ያገኘው 47.7 ቢሊዮን ብር ከእቅዱ አንጻር ሲታይ አፈጻጸሙ 105 በመቶ ነው። በበጀት ዓመቱ አገኛለሁ ብሎ ያቀደው ገቢ 45.4 ቢሊዮን ብር እንደነበርም የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል።
ኢትዮ ቴሌኮም በ2012 በጀት ዓመት ከውጭ አበዳሪዎች ከነበረበት እዳ ከ10.2 ቢሊዮን ብር በላይ (318 ሚሊዮን ዶላር) እዳ ከፍሏል።
ለመንግሥትም በትርፍ ድርሻ በታክስ 15.3 ቢሊዮን ብር ገቢ ማድረጉንም ይኸው መረጃ ያስረዳል። (ኢዛ)



