የሚሸጠው ቴሌ ከእቅዱ በላይ ገቢ እያገኘ ነው
ኢትዮ ቴሌኮም
የስድስት ወር ገቢው ከ22.04 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል
ኢዛ (ሐሙስ ጥር ፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 16, 2020)፦ በሽያጭ ወደ ግል ይዛወራሉ ተብለው ከሚጠበቁት ግዙፎቹ የመንግሥት ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ የኾነው ኢትዮ ቴሌኮም በ2012 በጀት ዓመት በግማሽ ዓመት 22.04 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱንና ይህም በ2011 ዓ.ም. በተመሳሳይ ወቅት ካገኘው ገቢ የ32 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመለከተ።
የኢትዮ ቴሌኮም የስድስት ወሩን የሥራ አፈፃፀም ይፋ እንዳደረገው በግማሽ ዓመቱ ያገኘው ገቢ ከእቅዱ በላይ ነው። ይህም የእቅዱን 104 በመቶ እንደኾነም ተገልጿል።
ኢትዮ ቴሌኮም በስድስት ወር ውስጥ ካገኘው 22.04 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከሞባይል ድምፅ አገልግሎት ያገኘው 50.4 በመቶ ሲሆን፣ ከገቢው ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል። ከዳታና ኢንተርኔት 27.3 በመቶ፣ ከዓለም አቀፍ ንግድ ገቢ 9.8 በመቶ፣ እሴት ከሚጨምሩ አገልግሎት 8.5 በመቶ እንዲሁም ከሌሎች አገልግሎቶች ሦስት በመቶ መኾኑም ተገልጿል።
የደንበኞቹ ብዛት 45.6 ሚሊዮን ማድረሱን የሚገልጸው የኩባንያው መረጃ፣ ይህም በ2011 ከነበረው 12 በመቶ እድገት የታየበት ነው ተብሏል።
ቴሌ የስድስት ወር አፈፃፀሙን ካቀደው በላይ ሊያገኝ ከቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ በአገልግሎት አሠጣጡ ላይ የተለያዩ ማሻሻያዎች ማድረጉ እንደ ምሳሌ ተጠቅሷል። (ኢዛ)



