የብሮድባንድ ኢንተርኔት ዋጋ እስከ 72 በመቶ ቀነሰ
ኢትዮ ቴሌኮም
ኢትዮ ቴሌኮም በመኖሪያ ቤታቸው ለሚጠቀሙት ደንበኞቹ 69 በመቶ ቅናሽ አደረገ
ኢዛ (ሐሙስ የካቲት ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 27, 2020)፦ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቸኛው የቴሌኮም ድርጅት በመኾኑ የሚታወቀው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎቱ ላይ የዋጋ ቅናሽ እንዳደረገ አስታወቀ።
ኢትዮ ቴሌኮም ዛሬ የካቲት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት በሚሠጣቸው በተለያዩ አገልግሎቶችና የተገልጋዮች ዐይነት ያደረገው የዋጋ ቅናሽ እስከ 72 በመቶ ይደርሳል።
በብሮድባንድ ኢንተርኔት አገለግሎቱ ላይ የተደረገው የዋጋ ቅናሽ በተመለከት በተሠጠው ተጨማሪ ማብራሪያ፤ በመኖሪያ ቤቶቻቸው የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ለኾኑት ደንበኞቹ የተደረገው የዋጋ ቅናሽ የ69 በመቶ ነው። በኢንተርፕራይዝ ደረጃ ለሚጠቅሙት ደግሞ የተደረገው የዋጋ ቅናሽ 65 በመቶ ሲሆን፤ ለቨርቹዋል ፕራይቬት ኔትዎርክ ተጠቃሚዎች የተደረገው የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት የዋጋ ቅናሽ 72 በመቶ ስለመኾኑ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮምን ወደግል ለማዛወር እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ባለበት በዚህ ሰዓት የሥራ አፈፃጸሙ ከፍ እያለ ስለመምጣቱ እየታይ ሲሆን፤ የገቢ መጠኑንም እየጨመረና ይሠጣቸው የነበሩ አገልግሎቶቹን እያስፋፋ ይገኛል።
ሰሞኑን የስድስት ወር አፈፃጸሙን በተመለከተ እንዳስታወቀው፤ በግማሽ ዓመቱ 22.4 ቢሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል። ይህ የገቢ መጠን በ2011 በጀት ዓመት አግኝቶት ከነበረው የ32 በመቶ ብልጫ አለው።
ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ቴሌ በአገልግሎቶቹ ላይ የዋጋ ቅናሽ እያደረገ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በተለይ በነሐሴ 2010 ዓ.ም. በስልክ ኢንተርኔት አገልግሎት ላይ 43 በመቶ፣ በስልክ የድምፅ አገልግሎት ላይ ደግሞ የ40 በመቶና የሞባይል የጽሑፍ መልእክት ላይም 43 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ማድረጉ በጉልህ የሚጠቀስ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮ ቴሌኮምን ወደግል ለማዛወር እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ተከትሎ፤ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ይህንን ግዥ ለመፈጸም ፍላጎት እያሳዩ መኾኑ ይታወቃል። መንግሥት ከቴሌ 49 በመቶውን ድርሻ ለመሸጥ ማሰቡ ይታወሳል። (ኢዛ)



