በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ከ35 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ተስተጓጉለዋል
ፕ/ር ሒሩት ወልደማርያም
በግጭቶቹ እርምጃ የተወሰደባቸው ከ900 በላይ ናቸው
ኢዛ (ሐሙስ ጥር ፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 16, 2020)፦ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በደኅንነት ሥጋት ከ35 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ትምህርት ገበታቸው ላይ አለመኾናቸው ተመለከተ። ከ900 በላይ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ እርምጃ ስለመወሰዱም ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተፈጠሩ ችግሮችን እንዲመረምር የተቋቋመው ኮሚቴ በ22 ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ያደረገውን የክትትልና የድጋፍ እንቅስቃሴዎችን አስመልክቶ ባቀረበው ሪፖርት፤ ከደኅንነት ሥጋት ጋር ተያይዞ ትምህርት ገበታ ላይ የሌሉ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራ መኾኑንም ያመለክታል።
የኮሚቴው ሪፖርት ጨምሮ እንዳመለከተው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ባደረገው ቅኝት ተማሪዎች ሳያውቁም ይሁን አውቀውት ከብሔርተኝነት ጋር ተያይዞ ጎራ የመለየትና በአንድ ቡድን በመሰባሰብ ጽንፍ የመያዝ አዝማሚያ የሚታይባቸው ሁኔታዎችን መመልከቱን ነው።
ከዚህም ሌላ የዩኒቨርሲቲ አስተዳደር አለመናበብ፣ የአመራር ክፍተት፣ ተገቢውን እርምጃ አለመውሰድ፣ የክትትልና ድጋፍ ማነስ የሚታይ መኾኑንም በዚሁ ሪፖርት ጠቅሷል። በኮሚቴው ቅኝትና ሪፖርት መሠረት እንደ ችግር የተመለከተው በዩኒቨርሲቲዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እንዲባባሱ ሌላው ምክንያት ኾኖ የተቀመጠው ችግር ፈጣሪ ነበሩ የተባሉ ተማሪዎች መልሰው ወደ ትምህርት ገበታ ላይ እንዲመለሱ ማድረግ ነው።
ከዚህም ሌላ የአንዳንድ ትምህርት ተቋማት የአስተዳደር ሠራተኞች በዘመድ አዝማድ የተቀጠሩ መኾኑ ለችግሩ የራሱ አስተዋጽኦ እንደነበረውም የሚያመላክት ምልከታ በሪፖርቱ ተካቷል። የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች ለዩኒቨርሲቲዎች የሰላም እጦት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መኾናቸውም ተጠቅሷል።
ቅኝቱን አስመልክቶ ቀረበ የተባለው ሪፖርት እንደ መፍትሔ ያቀረባቸውም ነጥቦች ያሉ ሲሆን፤ እንደ መፍትሔ ካስቀመጣቸው ውስጥ የተማሪዎች አመዳደብ ስብጥር እንዲኖረው ማድረግ አንዱ ነው። በከፍተኛ በቴክኖሎጂ የታገዘ የጥበቃ እንዲተገበር ማድረግም ችግሩን ለመቆጣጠርና ለእርምጃ አወሳሰድም መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ከማኅበረሰቡ ጋር ማቀራረብና ጠንካራ አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ማድረግም ከቀረቡት የመፍትሔ ሐሳቦች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ከተደረጉ ጥረቶች ውስጥ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የተደረገው የኮሚቴው ምርመራ፣ 85 በመቶ ውጤታማ መኾኑን የሚያመለክት ነው ተብሏል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም ይህንኑ በማረጋገጥ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከተፈጠሩ ችግሮች ጋር ተያይዞ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ጠቁመው፤ ሚኒስትሯ ተወሰዱ የተባሉ እርምጃዎችንም በዝርዝር አቅርበዋል። እስካሁን ተወሰደ የተባለው እርምጃ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ሲሆን፤ በተለይ በተማሪዎች ላይ እስከ ማገድ የሚያደርስ እርምጃ ስለመወሰዱ ታውቋል።
ማስጠንቀቂያ የተሠጣቸው ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት ከትምህርት ይታገዱ የተባሉ ተማሪዎችም እንዳሉ ይጠቀሳል። ኮሚቴው ሪፖርቱን ይፋ ባደረገበት ወቅት በእርሱ ምክረ ሐሳብ እርምጃ መወሰዱ ተገልጿል። (ኢዛ)



