National Election Board of Ethiopia 2020 schedule

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ 2012 ዋና ዋና ቀናትና ተግባራት

ድምፅ መስጫው ቀን ነኀሴ 10 እንዲኾን ቦርዱ አቅዷል

ኢዛ (ረቡዕ ጥር ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 15, 2020)፦ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ለማካሔድ የሚያስችለውን ረቂቅ የምርጫ ሰሌዳውን ይፋ ሲያደርግ፤ የምርጫው ቀን ነኀሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚኾን አመላክቷል።

ይህ የምርጫ ቦርድ ረቂቅ የምርጫ ሰሌዳው በዛሬው ዕለት ውይይት እየተረገበት ነው። በቀጣዩ ምርጫ ተሳታፊ የሚኾኑና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየመከሩበት ያለው ረቂቅ የምርጫው አጠቃላይ መርኀግብርን የያዘ ነው።

የጊዜ ሰሌዳው ሕገመንግሥቱን መሠረት ባደረገ መልኩ ምርጫውን ለማስፈጸም ታቅዶ መሠናዳቱን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ገልጸዋል።

በዚህ ረቂቅ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ከታኅሣሥ 22 ቀን ጀምሮ በተያዘ ፕሮግራም እስከምርጫው ዕለት የሚኖሩ ፕሮግራሞችን ይዟል።

ምርጫ ቦርድ ባቀረበው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባ ከመጋቢት 29 - ሚያዝያ 28 ቀን፣ የእጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ከሚያዝያ 13 - ሚያዝያ 26 ቀን፣ የምረጩኝ ዘመቻ ከሚያዝያ 27 - ነኀሴ 5 ቀን፣ የእጩዎች ዝርዝር ይፋ ማድረጊያ ቀን ሰኔ 7፣ የምረጡኝ ዘመቻ የተከለከለበት ጊዜ ከነኀሴ 6 - ነኀሴ 9 ቀን፣ እንዲሁም ድምፅ መስጫ ቀን ብሎ ያቀደው ነኀሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. መኾናቸው ታውቋል።

በዚህ የጊዜ ሰሌዳ ላይ እየተደረገ ያለው ውይይት የተለያየ አስተያየት እየተሠጠበት ሲሆን፤ ምናልባትም የጊዜ ሰሌዳው ማሻሻያዎች ሊደረጉበት እንደሚችል ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ 2012 ዋና ዋና ቀናትና ተግባራት

በእስካሁኑ ውይይት ላይ የተለያዩ ሐሳቦች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ የመራጮች የምዝገባ ጊዜውና የእጩዎች የምዝገባ ጊዜ አንሷል፣ ምርጫው የሚደረግበት ወር በደጋ አካባቢዎች ነዋሪው ከቤት የማይወጣበት ጊዜ ነው የሚሉ ይገኙባቸዋል። ሌሎችም ጥያቄዎችና አስተያየቶች በመድረኩ እየቀረቡ ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ