“የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መንግሥት ይሠራል” የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት
የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን
ጠ/ሚንስትሩን ጨምሮ ማናችንም ከኢትዮጵያ ሕግ በታች ነን፤ ማንም ሰው ከኢትዮጵያ ሕግ በታች ነው
ኢዛ (ሐሙስ ጥቅምት ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 31, 2019)፦ ወቅታዊውን የአገሪቱን ሁኔታ አስመልክቶ የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በሠጡት መግለጫ፤ በሰሞኑ ግጭት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 78 መኾኑንና ግጭቱን በመቀስቀስ የተጠረጠሩ 409 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዛሬ ገለጹ። ማንም ሰው ከኢትዮጵያ ሕግ በታች መኾኑንም በመግለጽ መጠየቅ ካለበት ይጠየቃል ብለዋል።
ዛሬ (ጥቅምት 20 ቀን 2012 ዓ.ም.) ከሰዓት በሠጡት መግለጫ፤ በግጭት ውስጥ የተሳተፉ በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ አካላት መሳተፋቸው እስከተረጋገጠ ድረስ የሚጠየቁ መኾኑንም ተናግረዋል።
የሰሞኑ ግጭት ቀስ በቀስ የብሔርና የሃይማኖት ግጭት እየታየበትና እየሰፋ የመሔድ ምልክት ታይቶበት እንደነበር አስታውሰዋል።
ኾኖም የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ አባገዳዎችና ምሁራን እንዲሁም የፀጥታ ኃይሉ ባደረጉት ጥረት ጥቃቱን የማስቆም ሥራ እንደሠሩም ከአቶ ንጉሡ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል። ይህ ባይኾን ጉዳቱ የከፋ ይሆን ነበርም ብለዋል።
በተለይ ሕግ ከማስከበር አንጻር የመንግሥትን አቋም በተመለከተ፤ አሁንም ቢኾን በየትኛውም ደረጃ ግንኙነት ያላቸው፣ ጥፋት ውስጥ የተሠማሩ፣ … በየትኛውም ደረጃ! … እየተጣራ የእርምት እርምጃ የሚወሰድና የሕግ የበላይነትን የማስከበር፣ የማረጋግጥ ሥራ የሚሠራ መኾኑን የገለጹበት ነበር። ከዚህም ጎን ለጎን የሕብረተሰቡን ሰላም የማስጠበቅ ሥራ በመንግሥት በኩል ከሁሉ ቅድሚያ ተሠጥቶት እንደሚሠራም በዚሁ መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
“በጉዳዩን ተሳታፊ የኾኑ ሕይወት ያጠፉ፣ አካል ያጎደሉ፣ ንብረት ያወደሙ ሕብረተሰቡ መረጃ የሠጠባቸው፣ በአጠቃላይ በዚህ ጉዳይ ላይ በአንድም በሌላ መልኩ ተሳትፎ ያላቸው የተጠረጠሩ 409 ያህል ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል” በማለት ገልጸዋል።
አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረቡ ጉዳይ ለድርድር እንደማይቀርብ ያመለክቱት ኃላፊው፤ “ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ ማናችንም ከኢትዮጵያ ሕግ በታች ነን። ማንም ሰው ከኢትዮጵያ ሕግ በታች ነው። ማንም ሰው ከኢትዮጵያ ሕግ በታች በመኾኑ በሕግ እንደሕጉ አግባብ ይጠይቃል” በማለት በሰሞኑ ጉዳይ መንግሥት ያለውን አቋም አንጸባርቀዋል። (ኢዛ)



